በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች እና ጦማሪዎች ለእስር እና ለሽብር ክስ ሲዳረጉ ቆይተዋል። ዘፋኞች ግን በአንፃሩ፣ እስከቅርብ ጊዜ ነጻ ነበሩ።
ባለፈው ዓመት፣ የመብት አራማጆች “የእምቢተኝነት ዘፈኖች” የሚሏቸው ዜማዎች የኢትዮጵያን የበሬ ግምባር የምታክል የበይነመረብ መስክ አጥለቅልቀዋታል። ነገር ግን የፖለቲካ ዘፈኖቹ የሕዝቡን ቀልብ በይነመረብ ላይ መሳባቸውን ሲመለከቱ፣ ባለሥልጣናቱም የተለያዩ የማፈኛ ዘዴዎችን ለተቃዋሚ ያደላሉ ያሏቸው ዘፋኞች ላይ አድርገዋል።
ከታኅሣሥ 2008 ጀምሮ ራሳቸውን በአገሪቱ ከተጋጋለው የተቃውሞ ንቅናቄ ጋር ያጠጋጉ ታዋቂ የኢትዮጵያ ዘፋኞች እየታደኑ ሲታሰሩ ነበር።. ባለፈው ሳምንት ተቀባይነቷ እያደገ የመጣላት ጀማሪ ዘፋኝ ሴና ሰሎሞን “የሚያነሳሱ” ግጥሞች ያሏቸውን የሙዚቃ ቪዲዮዎች በዩቱዩብ ላይ በመለጠፍ የሽብርተኝነት ክስ ተመሥርቶባታል።
በተንኳሹ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር የዚህ ዓይነቱ የእስር ዘመቻ የኢትዮጵያ መንግሥት የዋና ከተማይቱ አዲስ አበባን የማስፋፋት ዕቅዱን ያወጀ ሰሞን ተበራክቶ ነበር። በ2006 ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ አዲስ አበባን ወደአዋሳኟ እና በሕዝብ ብዛት ቀዳሚ የሆኑት የኦሮሞ ሕዝቦች ክልል፣ የኦሮምያ ገበሬዎች መሬት የማስፋፋት ዕቅዱን ተናግሮ ነበር።
ዕቅዱ መጠነ ሰፊ አመፅ የቀሰቀሰ ሲሆን የመንግሥት በኃይል የማስቆም ሙከራ ደግሞ የበርካቶችን ሕይወት ከመቅጠፉም ባሻገር፣ እስካሁን የዘለቀ አስቸኳይ ግዜ አዋጅን በጥቅምት 2009 እንዲታወጅ አድርጓል። አንዳንዶች በመጋቢት ለአራት ወራት የተራዘመው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ከሁለት ዓመታት ሕዝባዊ አመፅ በኋላ የተወሰነ ፀጥታ አምጥቷል ይላሉ።
የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ የአደባባይ ተቃውሞዎቹን ቢያስቆምም፣ የእምቢተኝነቱ ስሜት እና ትርክት ግን ሳይነካ አሁንም አለ። እናም (የአካባቢው የትልቁ ቋንቋ) የኦሮምኛ ዘፋኞች ጉልህ – እና ተደማጭ – የተቃውሞ ንቅናቄው ማነቃቂያ ሆነው እያንሰራሩ ነው።
ለኦሮሞዎች ‘የእምቢተኝነት ዘፈኖች’ የፖለቲካ ንቅናቄያቸው ልብ ከሆነ ሰነባብቷል። ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት ወራት፣ ‘የእምቢተኝነት ዘፈኖች’ እየጎሉና የቁጭት ድምፃቸውም እየበረታ ሲመጣ ከፍተኛ አድማጭም አፍርተዋል። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ የአማርኛ ዘፋኞችም የፖለቲካዊ ይዘት የተጫናቸውን ዘፈኖች በመጫወት የእምቢተኝነት ዘፈኖች አዝማቹን ተቀላቅለዋል። ታዋቂው የአማርኛ ዘፋኝ ይሁኔ በላይ የኢትዮጵያ መንግሥት ወታደሮች ዜጎችን መግደል እንዲያቆሙ የሚጠይቅ ተወዳጅ የአማርኛ ዘፈን ለቋል።
በርካታ የዩቱዩብ ቻናሎች እና የፌስቡክ ገጾች ተከፍተው የአመፁን ባሕላዊ ገጽታ እየመዘገቡ ነው። ድረገጾችና ጦማሮች የእምቢተኝነት ዘፈኖችን ያጋራሉ።
ዩቱዩብ ላይ፣ የአመፅ ምስሎች ተገጣጥመው ከእምቢተኝነት ዘፈኖቹ ጋር በቅንብር ሲቀርቡ፣ በየለቱ በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ተመልካቾችን ያገኛሉ።
በይነመረብ ለማይጠቀሙ ሰዎች የጎዳና ዳር ሲዲ ሻጮች እና አከራዮች ዋነኞቹ የእምቢተኝነት ዘፈኖቹ አሰራጮች ናቸው።
መንግሥት ‘የእምቢተኝነት ዘፈኖችን’ ሳንሱር ለማድረግ ሁሉንም ዘዴዎች ሞክሯል። ዘፋኞችን አስሯል፣ ኮንሰርት ከልክሏቸዋል፣ ከአገር አሰድዷቸዋል። ዩቱዩብ ቻናሎችን ዘግቷል። ዳያስፖራ ተቀማጭ የሳተላይት ቴሌቪዥኖችን አፍኗል።
ነገር ግን የመንግሥት ተቺ ዘፋኞችን የማፈን ሙከራ የዘፋኞቹን የእምቢተኝነት ዘፈኖች ተደማጭነት ከመጨመር ያለፈ ፋይዳ ያለው አይመስልም። ለምሳሌ ያክል ያ ጉለሌ ፊልም የተባለው የሴና ሰሎሞን እና ባልደረቦቿ የዩቱዩብ ቻናል፣ ከመታሰራቸው በፊት ከ3,525,996 ጊዜ በላይ ተመልካች አግኝቷል።