ሕዳር 7 ቀን ከአንዱ ድርጅት በስተቀር የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ለመዋሐድ መስማማታቸውን አወጁ።
ከአባል ድርጅቶቹ ሁሉ አንጋፋው ሕወሓት ውሕደቱን በመቃወም እንዲዘገይ በማለት መድረኩን በ2010 ሥልጣን ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ሲቆጣጠሩ ወደ ጀመረው የፖለቲካ ትርምስ ለቋል።
ነገር ግን የውሕደቱ እርምጃ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በጥላቻ ንግግር፣ በመረጃ ማዛባት እና የተሳሳተ መረጃ መስጠት የተመሠረተውን የዘውግ ክፍፍል እና ነውጥ ለማለዘብ ይረዳል ተብሎ ይጠበቃል።
የውሕደቱ ዜና የታወጀው በሕዳር ወር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በአማራ ክልል በሚገኘው ወልዲያ ዩኒቨርሲቲዎች ሁለት የኦሮሞ ተማሪዎች በደቦ መገደላቸውን ተከትሎ የተዛባ መረጃ መሻኮቻ ሆነው ትኩረት በሳቡበት ወቅት ነበር።
“He checked mine and said, ‘he is Oromo.’ Then one of them hit me with a metal stick and the other one with a rock. I fell down and fainted. When I became conscious, I saw myself laying in pool of blood.” https://t.co/ILfzpRIMiv
— Tigist Geme (@TigGeme) November 13, 2019
“የኔንም ተመለከተና ‘ኦሮሞ ነው’ አለ። ከዚያ አንደኛው በብረት፣ ሌላኘው በድንጋይ መቱኝ። ከዛ ራሴን ሳትኩ። ስነቃ፣ ራሴን በደም ተነክሬ አገኘሁት።” https://t.co/ILfzpRIMiv
ጥቅምት 29፣ 2012 በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ ኦሮሞ እና አማራ ተማሪዎች መካከል ምንነቱ ያልታወቀ ግጭት መቀስቀሱ ተነግሮ ነበር። ከዚያ በማኅበራዊ ሚዲያዎች አንዱ ቡድን ሌላውን ቡድን እያጠቃ ነው የሚል አሉባልታ ተሰራጨ። ይህም በተለይ ከቀያቸው ርቀው የሚማሩ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ድንጋጤን ፈጠረ።
የመንግሥት ባለሥልጣናት መረጋጋት እንዲሰፍን ጠየቁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው የአሉባልታ መንዛቱን ነገር አውግዘው የአካባቢው ባለሥልጣናት በፍጥነት ሕግ በማስከበር ተማሪዎቹን ካላረጋጉ ዩኒቨርሲቲዎቹን እንደሚዘጉ በዛቻ አስጠነቀቁ።
በአገሪቱ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተዛመተው ድንጋጤ በኢትዮጵያ ስር የሰደደውን የዘውግ ውጥረት ከመቀስቀሱም ባሻገር ብዙ ጊዜ በኦሮሞ እና አማራ መካከል እንዳለ ግጭት ተደርጎ የሚቃለለውን ነገር ግን ነፍስ እየቀጠፈ ያለውን የኢሕአዴግ ውስጥ ለውስጥ ውስብስብ የሥልጣን ሽኩቻ የሚያሳይ ነበር።
ኢሕአዴግ የአራት ፓርቲዎች ግንባር ነው። አባላቱም፣ አዴፓ፣ ኦዴፓ፣ ደኢሕዴን እና ሕወሓት ሲሆኑ፣ አገሪቱን የሚመሩትም እነርሱው ናቸው። ከ1983 ወዲህ ኢሕአዴግ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ማዕከላዊ ተዋናይ ነበር። ይሁንና እስካሁን አገሪቷን እየመራ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ዓመታት፣ በተግባር እየከሰመ የመጣ ግንባር ነው።
ፓርቲው መቋጫ በሌለው ነፍስ እስከመቅጠፍ የዘለቀ የሥልጣን ሽኩቻ ተተብትቧል። በተለይ በአራቱ የዘውግ ቡድኖች ሥም በተደራጁት ፓርቲዎች ደጋፊዎች እና አባላት መካከል የማኅበራዊ ሚዲያ ግጭት አለ።
የግንባሩ አባላት፣ በተለይም አዴፓ፣ ኦዴፓ እና ሕወሓት በየክልሉ ካሉ ነውጠኛ ብሔርተኛ ተቃዋሚዎች ጋር በግልጽ ሲዳሩ ነው የከረሙት። ለተቃዋሚ ሚዲያዎች አሳፋሪ ታሪኮችን አሳልፈው እየሰጡ የወትሮው የተዛባ መረጃ ስርጭት ላይ ነዳጅ በማርከፍከፍ እርስ በርስ እየተናከሱ ነው።
የሚያሾልኳቸው መረጃዎች አንዳንዴ ሙሉ ለሙሉ ፈጠራ ናቸው። ከዚያም በላይ አሳሳች እና ወገንተኝነት የተጫናቸው መረጃዎች ናቸው። ዞሮ ዞሮ ተደምረው ለፓርቲ ውስጥ የሥልጣን ሽኩቻቸው አስተዋፅዖ ያደርጋሉ።
በጥቅምት ወር ለምሳሌ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ታዋቂ የሆነው ስዩም ተሾመ ለማመን የሚቸግሩ የኢሜይል ቅጂዎችን ከአንድ ከፍተኛ የሕወሓት ባለሥልጣን የተቀዳ ነው በሚል መለጠፍ ጀመረ። ስዩም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና ደጋፊ ሲሆን በ2009 እና በ2010 ባልታወቀ ምክንያት ሁለት ጊዜ ታስሯል።
የተጠለፉት ኢሜይሎች በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ አመፅ በመቀስቀስ ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ላይ እና በአገሪቱ የፀጥታ ሁኔታ ላይ እምነት እንዲያጡ ለማድረግ የሕወሓት አባላት እያቀዱ ነበር ይላል።
የጃዋር መሐመድ ‘የግድያ ሴራ'፡ የተዛባ መረጃ ጉዳይ
ጥቅምት 11፣ ቀደም ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አጋር የነበረው እና ታዋቂው የኦሮሞ ፖለቲካ ተሟጋች ጃዋር መሐመድ የፌስቡክ ገጹ ላይ በአዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ አካባቢ ያንዣበበ ሁኔታን ገልጿል። ጃዋር መልዕክቱን ያስተላለፈው በኦሮምኛ፣ አማርኛ እና እንግሊዝኛ ሲሆን፥ ጥቅል መልዕክቱ ከዕኩለ ሌሊት በኋላ ቤቱ የመጡ የፌዴራል ፖሊስ አባላት መንግሥት የቀጠረለትን የፀጥታ አካላት ጠቅልለው እንዲወጡ ማዘዛቸውን ነው።
ከሚያዝያ 2010 ጀምሮ መንግሥት ሚዲያ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ በማርገብ በፊት የታገዱ የተቃዋሚ መሪዎችን እና አክቲቪስቶችን ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ በማድረግ ጃዋርን ጨምሮ የጥበቃ ከለላ ሲያደርግላቸው ከርሟል።
የጃዋር መሐመድ የፌስቡክ ጽሑፍ. ስክሪንሾቱ የተወሰደው ጥቅምት 15, 2012 ነው። ጃዋር መሐመድ በዚህ ጽሑፉ ታጣቂዎቹ ለመጠጋት ከሞከሩ ጠባቂዎቹ ራሳቸውን እንደሚከላከሉ እና ደም ከፈሰሰ መንግሥትን ተጠያቂ እንደሚያደርግ ገልጿል።
ይህንን ጽሑፍ በጻፈ ጥቂት ሰዓታት ውስጥ፣ ጃዋር በደጋፊዎቹ እና ተቃዋሚዎቹ ሲጠበቅ እንደነበረው ሁሉ፣ ራሱ ባቋቋመው እና ዋና ዳይሬክተር ሆኖ በሚመራው ኦኤምኤን ቴሌቪዥን እና ፌስቡክ ላይቭ ቀርቦ ንግግር አድርጓል። በቪዲዮ መልዕክቱ ከመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር ያለውን ግጭት በማካበድ የግድያ ሴራ ነው በማለት ወቀሳ አቅርቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግን ወቀሳውን በመካድ ሊገድሉት ቢፈልጉ መጀመሪያውንም የደኅንነት ጥበቃ እንደማያቆሙለት ተናግረዋል።
የጃዋር ውንጀላ የግብረ ምላሽ ክስተቶችን አከታትሎ በመጫሩ ደጋፊዎቹ አዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ደጃፍ ተሰባስበው ነበር።
የአደባባይ ተቃውሞዎችም በተለያዩ ኦሮሚያ አካባቢዎች ተቀስቅሰዋል። ተቃውሞዎቹ አመፅ በማስከተላቸው ሚዲያዎች “የቡድን ግጭት” ያሉትን አስከትሏል።
የኦሮሚያ አስተዳደርን በአግላይነት የሚወቅሱት በአዳማ ያሉ ነዋሪዎች ተቃውሞ በማድረግ ተቃውሞው ነውጥ በማስከተል ለነፍስ መጥፋት መንሥኤ ሆኗል።
ከጥቅምት 11 እስከ 13፣ በዚህ ብዙ ነፍስ ከቀጠፉ ነውጦች መካከል አንዱ በሆነው የነውጥ አዙሪት ሳቢያ ቢያንስ 86 ሰዎች በኦሮሚያ የተገደሉ ሲሆን፣ ብዙዎችም ቆስለዋል።
ከነውጡ በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲዞሩ የነበሩ ምስሎች እና ቪዲዮዎች እንደሚያሳዩት፣ ኢትዮጵያውያን በሌሎች ኢትዮጵያውያን ላይ ፅንፍ የረገጠ ነውጥ እና ጭካኔን ማድረጋቸው ፍርሐት እና የቡድን ውጥረት አንሰራፍቷል።
ነውጡ በክልሉ ሲበረታ፣ ኢንተርኔት ላይ ደግሞ ትንታኔው እና ጥፋተኛውን የመበየን ግብግቡ ተጧጡፏል።
በዘውግ የተካረረው የኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚድያ ለነውጡ የተለያዩ ቅፅል ሥሞችን ሰጥተውታል። የአማራ ብሔርተኞች፣ የኢትዮጵያ ብሔርተኞች እና የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮች “የዘውግ ማፅዳት” እና “ጭፍጨፋ” እያሉ ሲገልጹት፣ የኦሮሞ እና ሲዳማ ብሔርተኞች ደግሞ “መንግሥት መር ነውጥ” ነው ብለውታል።
እነዚህ ትርጓሜዎች በተለይ በአማራ እና ኦሮሞ ልኂቃን መካከል በተዛባ እና በተሳሳተ መረጃ ሥም መለጣጠፎች አስከትሏል።
ጃዋርን በተጠያቂነት የሚፈርጁት ተቃዋሚዎቹ ጽሑፎችን፣ ምስሎችን እና ቀልዶችን በፌስቡክ፣ ትዊተር እና ዩቱዩብ በማሰራጨት ጃዋርን ተጠያቂ ሲያደርጉ ለነገ አይሉም። ለእነርሱ፣ ጃዋር የግድያ ሙከራ እንደተደረገበት በሐሰት በማስመሰል እና ብሔርተኛ ስሜትን ሆነ ብሎ በመቀስስ ነውጡን አስከትሏልተለ።
በተጨማሪም፣ አንዱ በስዩም ተሾመ ጥቅምት 15 የተለጠፈው እና ከተጠለፈ ኢሜይል ተገኘ ነው የተባለው መረጃ ጃዋር መሐመድ የኢሕአዴግን ውሕደት በመቃወም ከሐወሓት አባላት ጋር በኦሮሚያ አመፅ ለመቀስስ አብሮ እንደሠራ ያወራል።
ነውጡ እና እልቂቱ የተከሰተው በጃዋር መሐመድ የፌስቡክ ጽሑፎች ሳቢያ ነው የሚሉት ተቃዋሚዎቹ፥ ትዊተር ላይ “#October2019massacre” በሚል ሐሽታግ መልዕክቶቻቸውን አስተጋብተዋል። ብዙ ጊዜ ለጃዋር በመራራት ወይም ደግሞ በምሥጢር አብረውት በመሥራት ከሚከወቅሷቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ቁርጥ እርምጃ እንዲወሰድ ጥሪ አቅርበዋል።
የጃዋር ደጋፊዎች ደግሞ በበኩላቸው የኦሮሚያ ተቃውሞዎችን ጃዋርን ከግድያ ያተረፈ ድል አድርገው ሲያቀርቡ ሰልፈኞቹንም እንደጀግና ቆጥረዋቸዋል። እነርሱም በበኩላቸው ተጠያቂነቱን አማራ ብሔርተኞች እና ሌሎች የተቃዋሚ ድርጅቶች ላይ ለጥፈዋል።
ለጃዋር መሐመድ አጋርነታቸውን ያሳዩ ብዙ የኦሮሞ መብት ተሟጋቾች እና ፖለቲከኞች ኦሮሞዎች ብሶታቸውን ለመግለጽ ስበብ ሲፈልጉ እንደነበር እና የግድያ ሴራው የመጨረሻ ሰበብ እንደሆናቸው ሲገልጹ ነበር። በከፍተኛ ሁኔታ ከተሰራጩት የቪዲዮ መልዕክቶች በአንዱ ተቃዋሚዎች ዐቢይን “ሐበሻ” እያሉ ሲጠሯቸው ተስተውሏል። ሐበሻ የሚለን ቃል ኢትዮጵያውያንን ለመለየት የሚጠቅም ቢሆንም የኦሮሞ ብሔርተኞች ግን የኦሮሞን ጥቅም ኦሮሞ ላልሆኑ አሳልፎ የሚሰጥን ሰው ለመጥራት ይጠቀሙበታል።
ጃዋር በደጋፊው ማኅበረሰብ ውስጥ የተቃውሞ መሪ፣ የሚዲያ ኀላፊ እና የፖለቲካ ስልት ቀያሽ ተደርጎ ነው የሚታየው። ፌስቡክ ላይ ባሉት 1.8 ሚሊየን ተከታዮች አማካይነት የጎዳና ላይ ተቃውሞዎችን መርቷል፣ ገንዘብ አሰባስቧል፣ በአንድ ወቅት በኢሕአዴግ የበላይ የነበረውን እና ማኅበራዊ ሚዲያን ከመዝጋቱም ባሻገር ብሎገሮችን አስሮ ያሰቃየውን ሕወሓት ለመጣል ከውስጥ ሰዎች መረጃ አሰባስቦበታል።
ያኔም ቢሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ጃዋርን ጨምሮ ሌሎች ተቃዋሚዎችን በተዛባ መረጃ ለማጥቃት እና ድጋፍ ለማሰባሰብ ማኅበራዊ ሚዲያን ተጠቅሟል። በርግጥ በማኅበራዊ ሚዲያ ለአሁኑ የመረጃ መዛባት ባሕል መሠረት የተጣለው በ2006 ነበር።
ለበርካታ ዓመታት፣ ተከፋይ የኢንተርኔት አስተያየት ሰጪዎች ገዢው ፓርቲንና ፖሊሲዎቹን የሚደግፉ እና ተቃዋሚዎችን የሚያጠቁ ጽሑፎችን ሲያበረክቱ ነበር። እነዚህ አስተያየት ሰጪዎች ‘ኮተታም ካድሬ’ ወይም ሲጨመቅ ‘ኮካ’ የሚል ቅፅል ሥም ተሰጥቷቸው ነበር። ኮካዎች በኢሕአዴግ ግንባር አባላት ሕዝባዊ አስተያየትን ለመከርከም የተቀጠሩ ናቸው።
ኮካዎች በኢሕአዴግ በተዘጋጁ ጽሑፎች እና ቀልዶች ዙሪያ በቀላሉ ይተባበሩ ነበር። ለምሳሌ ያክል የሕወሓት አባሉ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ለዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር-ጄነራል ለመሆን ሲወዳደሩ ትልቅ ድጋፍ ያላቸው ለማስመሰል ፌስቡክ ላይ ያሉ ኮካዎችን አሰማርተዋል።
በተመሳሳይ፣ ጃዋር ኢሕአዴግ ውስጥ ተገልጦ ያላለቀውን መሬት አንቀጥቅጥ ለውጥ እየተጠቀመበት ነው። በራሱ እና የኦኤምኤን ፌስቡክ ገጽ፣ ከኢሕአዴግ ውስጥ ጥብቅ ምሥጢሮች እንደሚደርሱት በማቅረብ ጥንታኔ ያቀርባል። ጽሑፎቹን የሚያቀርበው ያለምንም ጊዜ ዕቅድ ነው። አንዳንዴ በቀን በርካታ መረጃዎችን ይለቃል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ምንም ሳይል ያልፋል። መረጃዎቹ የኦሮሞ ሕዝብን ፍላጎት፣ ብሶት እና ስጋት የሚያንፀባርቁ ናቸው ብሎ ያምናል።
የኦኤምኤን ፌስቡክ ገጽ አንድ ሚሊዮን ተከታዮች ያሉት ሲሆን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በፍጥነት በርካታ ተከታዮችን እያፈራ ካሉ ገጾች መካከል አንዱ ነው።
ጃዋር የእርሱ መሆኑ በተረጋገጠው እና 1.8 ሚሊዮን ተከታዮች ባለው ፌስቡክ ገጹ የትኛውም ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ሰው አይፎካከረውም።
ይህ ጽሑፍ የተዘጋጀው በሰባት አፍሪካ አገራት ማለትም አልጄሪያ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ፣ ናይጄሪያ፣ ቱኒዚያ፣ ዩጋንዳ እና ዚምባቡዌ ያለውን በኔትዎርክ ማቋረጥ እና መረጃ በማዛባት የሚፈፀሙ የዲጂታል መብቶች ገፈፋዎች የሚዘገቡባቸው ጽሑፎች ፕሮጀክት አካል ሆኖ ነው። ፕሮጀክቱ የሚደገፈው የThe Collaboration on International ICT Policy for East and Southern Africa (CIPESA) አካል በሆነው የአፍሪካ ዲጂታል ራይትስ ፈንድ ነው።