የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ እንዴት ነውጥ ቀሰቀሰ (ክፍል አንድ)

ሀጫሉ ሁንዴሳ ከኦኤምኤን ጋር ያደረገው ቃለ ምልልስ በFiraabeek Entertainment / CC BY 3.0.


የአርታኢ ማስታወሻ፦ ይህ ባለ ሁለት ክፍል ትንታኔ የታዋቂው ኦሮሞ ሙዚቀኛ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ የተቀሰቀሰው የብሔረሃይማኖት ነውጥ በመረጃ ማዛባት እንዴት እንደተቀጣጠለ ያሳያል። ክፍል ሁለትን እዚህ ያንብቡ!  
ታዋቂው ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ሀጫሉ ሁንዴሳ የፈጠራ ተሰጥኦውን ተጠቅሞ የኦሮሞ ሕዝብን በማነቃቃቱ ዝናን አትርፏል። አርቲስቱ ሰኔ 22 ቀን፣ በአዲስ አበባ ዳርቻ ባለ የመኖሪያ ስፍራ ተገድሏል
የዛን ዕለት ምሽት 3፡30 ላይ ጥላሁን ይልማ ነው የተባለ ሰው ሀጫሉ ከመኪናው እየወረደ ሳለ፣ ደረቱን በጥይት ተኩሶ መታው። በቅርብ ወደ ሚገኘው ሆስፒታል ቢወሰድም ከሞት ሊተርፍ አልቻለም። ጥይቱ የውስጥ የሰውነት አካሉ ላይ ጉዳት እንዳደረሰ በኋላ ተገልጿል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ሁለት ሰዎች ተጠርጥረው መታሰራቸውን አሳውቋል። ከሁለት ቀን በኋላ፣ ባለሥልጣናቱ ከሌሎች ሁለት ሌሎች አባሪዎቹ ጋር ተጠርጣሪውን ነፍሰ ገዳይ ክስ መሥርተውበታል።
የግድያው ዜና ከተሰማ በኋላ አገሪቱ ተከትሎ የመጣውን ነውጥ ለመጋፈጥ ተገድዳለች። የሀጫሉ ግድያ እውነታ ገና ሳይጠራ፣ ፖለቲከኞች እና አራማጆች ግምታቸውን በመናገር ለረዥም ጊዜ በውጥረት ውስጥ የኖሩትን በኢትዮጵያ ሁለት ብዙኃን ብሔሮች ማለትም አማራ እና ኦሮሞ ልኂቃን መካከል ያለ ውጥረት አባባሱት
የዛኑ ዕለት ሐዘንተኞች የአዲስ አበባን እና የኦሮሚያን ከተሞች አጥለቀለቋቸው። በማግስቱ፣ ሀጫሉ የመጨረሻ አወዛጋቢ የነበረ ቃለ ምልልሱን የሰጠበት የሳተላይት ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) የአርቲስቱ አስከሬን ከአዲስ አበባ ወደ ትውልድ ስፍራው አምቦ አሸኛኘት በቀጥታ እያስተላለፈ ነበር
በቴሌቪዥን እየተላለፈ የነበረው ይህ አሸኛኘት ሀጫሉ የት ነው መቀበር ያለበት በሚል የባለሥልጣናት እና የተቃዋሚ ፖለቲከኞች ደም አፋሳሽ ትግል መድረክነት ተቀየረ። የኦኤምኤን ስርጭት የአስከሬን መኪናው ወደ አዲስ አበባ ሲዞር ተቋረጠ። ያኔ በአዲስ አበባ ቢያንስ ዐሥር ሰዎች ሲገደሉ በርካቶች ደግሞ ጉዳት ደረሰባቸው። 
ግርግሩ የኦኤምኤን የቀድሞ መሪ ጃዋር መሐመድንና በቀለ ገርባን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞችን እስር ግጭቱን ቀስቀሰዋል በሚል አስከተለ።
ግራ መጋባቱ መንግሥት የሀጫሉን አስከሬን በሄሊኮፍተር ወደ አንቦ ከወሰደው በኋላም ቀጠለ። ተቀናቃኞቹ ግጭታቸው በመቀጠሉ ቤተሰቦቹ ተገቢውን የቀብር ስርዓት ለማድረግ ተቸግረዋል።
ይህ በእንዲህ እያለ ግርግሩ እና ነውጡ ቀጥሏል። የሦስት ቀናት ነውጥ በኦሮሚያ እና አዲስ አበባ ቀጥሎ  ብዙ ዋጋ አስከፈለ፦ 239 ሰዎች ሞቱ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሌሎች ተጎዱ፣ ከ7,000 በላይ ሰዎች ደግሞ ነውጥ በማስነሳት እና በሚሊዮን ብሮች የሚቆጠር የንብረት ጉዳት በማድረስ ተጠርጥረው ታሰሩ። 
ሰኔ 23 ቀን፣ መንግሥት ነውጦችን ለመከላከል በሚል ኢንተርኔት ተዘግቶ ለሦስት ሳምንት እንዲቆይ አደረገ።
በርካታ ሰዎች በመንግሥት ጥይት ተመትተው ተገድለዋል። ሆኖም  የአሜሪካ ድምፅ እና አዲስ ስታንዳርድን ጨምሮ፣ በርካታ የዜና አውታሮች በኦሮሚያ ብዝኀ-ብሔር እና ብዝኀ-እምነት ከተሞች ውስጥ የተፈፀሙ ኦሮሞ ያልሆኑ እና ሙስሊም ያልሆኑ ቤተሰቦች ላይ በደቡብ ምሥራቅ ኦሮሚያ የደረሰውን ጥቃት ዘገቡ።
ብዙዎቹ ነውጦች በአማራ-ኦሮሞ መሥመር የተጠመዱ ይሁኑ እንጂ ሃይማኖት ውስብስብና መንደርተኛ በሆነ የብሔር አረዳድ ሳቢያ ማዕከላዊ ሚና ሳይጫወት አልቀረም፦ የደቡብ ምሥራቅ ኦሮሞ ማኅበረሰብ ማንነት ሁኔታ በእስልምና አማኝነት እና በአፋን ኦሮሞ ቋንቋ ተናጋሪነት ጥምር የሚገለጽ ነው። አንድ የአካባቢው ነዋሪ የሀጫሉን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ትውፊት የተዘጋጀ የቀብር ሥነ ስርዓት በቴሌቪዥን ከተመለከተ በኋላ “እኛ እኮ ሀጫሉ ኦሮሞ መስሎን ነበር” ብሏል ተብሏል።
የተለያዩ ዘገባዎች እንደገለጹት፣ ብዙዎቹ የዘግናኝ ነውጥ ጥቃት ሰለባዎች አነስተኛ ብዛት ያላቸው ክርስቲያን አማራዎች፣ ክርስቲያን ኦሮሞዎች እና ጉራጌዎች ነበሩ። የዓይን እማኞች እንደተናገሩት በደቦ የወጡ ሰዎች ንብረቶችን አቃጥለው አውድመዋል፣ በአደባባይ ስቅላት ፈፅመዋል፣ እንዲሁም አንገት ቀልተዋል፣ ብሎም ሰውነት ቆራርጠዋል

አሳዛኙ ቃለ መጠይቅ

የሀጫሉ ግድያ እንደተሰማ የዳያስፖራ ሚዲያ አውታሮች፣ ግድያውን ከግድያው ሳምነት ቀድሞ አርቲስቱ ለኦኤምኤን ጋዜጠኛ ጉዮ ዋሪዮ ከሰጠው  ቃለ ምልልስ ጋር አያያዙት።
በቃለ ምልልሱ ወቅት፣ ጉዮ ሀጫሉን በተደጋጋሚ ለገዢው ፓርቲ ያለውን ድጋፍ የተመለከተ ጥያቄዎች ሲጠይቀውና መልሱን እያቋረጠ ሲሞግተው ነበር።
ሀጫሉ ለገዢው ፓርቲ ድጋፍ አለህ የተባለውን ያስተባበለ ሲሆን፣ በኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች መካከል ያለውን መከፋፈልም በመተቸት እንደሙዚቀኛ እና አሳቢ ገለልተኛ መሆኑን ለማሳየት ሞክሯል – ይህ ባሕሪው እስከ ግድያው ድረስ የበይነመረብ ላይ መዘባበቻ አድርጎ አሰንብቶት ነበር።
በዚህ መሐል ጉዮ ሀጫሉን የዘመናዊት ኢትዮጵያን በመገንባት ረገድ ጉልህ ሚና የተጫወቱትን የ19ኛው ክፍለ ዘመን ዐጤ ዳግማዊ ምኒልክ ኦሮሞ ላይ አድርሰውታል ስለሚባለው ኢፍትሐዊነት ጠይቆት ነበር።
ሀጫሉ በአዲስ አበባ የሚገኘው የምኒልክ ሀውልት ላይ የሚታየው የሚጋልቡት ፈረስ የእርሳቸው ሳይሆን ሲዳ ደበሌ የተባለ የኦሮሞ ገበሬ ፈረስ ዘርፈው እንደሆነ በመናገር ብዙዎችን አስድንግጦ ነበር።

ይህ አስተያየቱ ተቺዎችም፣ አወዳሾችም ፌስቡክ ላይ እንዲስተወዋሉ አድርጓል።
ሀጫሉ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሲገደል፣ ብዙ የኦሮሞ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት ወዲያውኑ የዳግማዊ ምኒልክ ፈረስን አስመልክቶ የሰነዘረው ትችት በዐጤያዊቷ ኢትዮጵያ ደጋፊዎች አስገድሎታል ብለው ግምታቸውን አሳለፉ።
በማኅበራዊ ሚዲያ፣ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሀጫሉ ምኒልክ ላይ የተሰነዘረ ትችት ላይ የሙጥኝ ብለው ቢያተኩሩምና ወደ ተዛባ መረጃ ቢያሳድጉትም፣ ሌሎቹ የቃለ ምልልሱ ይዘቶች በኦሮሞ ማኅበረሰቦች ውስጥ ስላሉ ክፍፍሎችና ተቃርኖዎች በብዛት የሚያተኩሩ ነበሩ።
በቃለ ምልልሱ ውስጥ፣ ጉዮ ሀጫሉን በአገሪቱ ውስጥ እየተስተዋለ ባለው ፖለቲካዊ ለውጥ ላይ፣ በተለይም ራሳቸው ኦሮሞ በሆኑት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉዳይ እና የ2010ሩ ለውጥ ከመጣ ወዲህ የኦሮሞ ሕዝብ የሚጠብቀውን አግኝቷል ወይ እያለ መንግሥትን በሚያብጠለጥል ስሜት አስተያየት እንዲሰጥ ሲወተውተው ነበር።
ሀጫሉ በኦሮሞ ፖለቲካ ክፍፍል ውስጥ ለማንም ላለመወገን ጥረት ቢያደርግም፣ የዐቢይ አሕመድን ኦሮሞ ማንነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገቡ ሰዎችን ግን ተችቶ አልፏል።
ሀጫሉ በአንድ ወቅት ኢሕአዴግ ውስጥ በመሆን ኢትዮጵያን በበላይነት ሲመራ የነበረው ሕወሓት ጋር የሚፈጠሩ አጋርነቶች ላይ ያለውን የተቃውሞ አቋም አጠናክሯል። ሕወሓት ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ኢሕአዴግን ሲያፈርሱ ተቃዋሚ መሆኑ ይታወቃል።
ሀጫሉ በኦሮሚያ የተከሰተውን የፖለቲካ ነውጥም በተመለከተ በማንሳት የመንግሥት ባለሥልጣናትን እና በተለምዶ ኦነግ-ሸኔ በመባል የሚታወቀው፣ የኦነግ ወታደራዊ ቀኝ-ዘመም ክንፍ የነበረውን ትችትም ሰንዘሮ ነበር።
የሀጫሉን ግድያ ተከትሎ፣ መንግሥት የቃለ ምልልሱን ሙሉ 71 ደቂቃ በማግኘት ለዕይታ አቅርቦታል። የተቆረጠው ክፍል ሀጫሉ ኦነግ ሸኔ በንቃት ይንቀሳቀሳል ከሚባልበት ምዕራብ ኦሮሚያ የግድያ ዛቻ ይቀርብበት የነበረ መሆኑን የገለጸበት ክፍል ይገኛል። ሀጫሉ ኦነግ-ሸኔን ቢያወድስ ኖሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ይደርስበት የነበረው ጥቃት ላይደርስበት ይችል እንደነበር ገልጿል።

በሕወሓት ጊዜ የኢትዮፕያ ደኅንነት ኃላፊ ከነበረው ጌታቸው አሰፋ ጋር የነበረውን ግጭትም አንስቷል።
ጉዮ፣ ይህንን ቃለ ምልልስ በፌስቡክ “የግድ መታየት ያለበት” በሚል ከስርጭቱ በፊት ሲያስተዋውቅ ነበር። አሁን ጉዮ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፥ ሙሉ የ71 ደቂቃ ቃለ ምልልሱ ከሀጫሉ ግድያ ጋር የተያያዘ መረጃ ይገኝበት እንደሁ በሚል እየተመረመረ ነው።
የሀጫሉ ግድያ ያስከተለውን ጦስ በተመለከተ ክፍል ሁለትን ያንብቡ።

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.