See all those languages up there? We translate Global Voices stories to make the world's citizen media available to everyone.

ስለ እኛ

‘የዓለም ድምጾች’ (Global Voices) በዓለም ዙሪያ ለእናንተ ሪፖርቶችን እና የዜጎችን መገናኛ ብዙሐን ከየስፍራው ለማድረስ በአንድነት የሚሰሩ፣ ትኩረቱን በተለይ በመደበኛው መገናኛ ብዙሐን ተደማጭነት ባጡ ድምጾች ላይ ያደረገ ከ1400 በላይ ጦማሪዎችን እና ተርጓሚዎችን የያዘ ማኅበራዊ ስብስብ ነው፡፡

‘የዓለም ድምጾች’ የመስመር ላይ ውይይቶችን ማጠቃለል፣ ግልጽ ማድረግ እና ማስጮኽ ይፈልጋል – ሌሎች መገናኛ ብዙሐን ችላ የሚሏቸው ሰዎችና ቦታዎች ላይ በማተኮር፡፡ በየትኛውም ቦታ ያሉ ድምጾች እንዲደመጡ አማራጮችን፣ ተቋማትን እና ግንኙነታቸውን ለማጠናከር እንሰራለን፡፡

እልፍ ሰዎች እየጦመሩ፣ ጡመራውን እያስተጋቡ እና ፎቶና ቪዲዮዎችን ጨምሮ ሌሎችንም መረጃዎች በዓለም ዙሪያ በመበተን ላይ ይገኛሉ፡፡ ነገር ግን የት እንደሚገኙ ለማያውቅ ሰው የተከበረውን እና ትክክለኛውን ድምጽ ወይም መረጃ የት ማግኘት አስቸጋሪ ነው፡፡ የዓለም አቀፉ በጎ ፈቃደኞች ጸሐፊ ቡድናችን እና የትርፍ ሰዓት አርታኢዎቻችን ‘የዓለም ድምጾች’ ላይ በሚያሰፍሯቸው ጉዳዮች ዙሪያ ያሉ የጡመራ መድረኮች ንቁ ተሳታፊ ናቸው፡፡

‘የዓለም ድምጾች’ በኔዘርላንድ Stichting Global Voices የተባለ ትርፋማ ያልሆነ ድርጅት አባል ነው፡፡ ቢሮ የለንም፣ ነገር ግን ምናባዊ የበይነመረብ ማኅበረሰብ ፈጥረን በብዙ የሰዓት ዞኖች ልዩነት ውስጥ አብረን እየሰራን ነው፤ በአካል የምንገናኘው ሁኔታዎች ሲፈቅዱ ብቻ ነው (ብዙ ጊዜ በስብሰባ)፡፡ የምንተማመነው ወጪያችንን ለመሸፈን በሚሰጡን ድጎማዎች፣ ስፖንሰር አድራጊዎ፣ አርትኦት ኮሚሽኖች እና ልገሳዎች ነው፡፡

ፕሮጀክቶቻችን

‘የዓለም ድምጾች’ በበጎ ፈቃደኛ ተርጓሚዎች ከ30 በላይ በሚሆኑ የዓለም ቋንቋዎች ተተርጉመዋል፡፡ እነዚህ ተርጓሚዎች ሊንጉዋ የሚባል ፕሮጀክት መስርተዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ‘የዓለም ድምጾች’ በመስመር ላይ የሚያሰሙት ድምጽ ለሚታፈንባቸው ሕዝቦች የለውጥ ወትዋች(Advocacy) ድረአምባም አለው፡፡ በማንሰራራት ላይ ያሉ ድምጾች (Rising Voices) የምንለውም፣ በተለይ በታዳጊ አገራት ላይ ያተኮረ፣ አፈናና ተጽዕኖ እየደረሰባቸው ያሉ ዜጎች ድምጻቸው እንዲሰማ የምንሰራበት ፕሮጀክትም አለን፡፡

ስለፕሮጀክቶቻችን እዚህ ጠቅ በማድረግ ብዙ ማንበብ ትችላላችሁ፡፡

ታሪካችን

‘የዓለም ድምጾች’ እ.ኤ.አ. በ2005፣ በቀድሞው የCNN ቤጂንግ እና ቶክዮ ቢሮ ኃላፊ፣ ሬቤካ ማክኪኖን እና በቴክኖሎጂስቱ እና አፍሪካ ኤክስፐርቱ ኢታን ዙከርማን አማካይነት የሐርቫርድ ዩንቨርስቲ፣ በርክማን የበይነመረብ ማኅበረሰብ ማዕከል ፌሎዎች ሳሉ የመሰረቱት ማኅበረሰብ ነው፡፡ ሐሳቡ የመነጨው እ.ኤ.አ. በ2004 በሐርቫርድ በተካሄደው የዓለምአቀፍ ጦማሪዎች ስብሰባ ላይ ሲሆን እንደ አንድ ነጠላ ጦማር ነበር የተጀመረው፡፡ (የስብሰባው  የጽሑፍ ሪፖርትቀጣይ ሒደቶችን እዚህ ማግኘት ይቻላል፡፡)

ለበርክማን ማዕከል፣ ለሮይተርስ፣ ለማክአርተር ፋውንዴሽን ድጋፍ እና ለጸሐፊዎቻችን ወኔ እና ፈጠራ ምስጋና ይግባቸውና ‘የዓለም ድምጾች’ በፍጥነት ለማደግ በቅቷል፡፡

መነሻ ግቦቻችን

የእንግሊዝኛው መገናኛ ብዙሐን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የዓለም ዜጎችን ድምጾች ችላ በሚልበት ጊዜ፣ ‘የዓለም ድምጾች’ የዜጎችን መገናኛ ብዙሐን በማጠናከር የድምጽ እኩልነት ለመፍጠር ዓልሞ ይሰራል፡፡ ሐሳብን በመግለጽ ነፃነት እና ሕዝቦችን የሚከፋፍሏቸውን ሰላጤዎች በመድፈን እናምናለን፡፡

የምንመኘው:

  • ዜጎች የሚጽፏቸውን ጽሑፎች፣ ፎቶዎች፣ ቪዲዮዎች፣ በተደጋጋሚ የሚያጋሯቸውን ጉዳዮች፣ እና ሌሎችም እያደጉ የመጡ፣ መሰረታዊ የዜጎች የመወያያ ርዕሶች እና አመለካከቶች ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጣቸው ማድረግ፡፡
  • አዳዲስ የዜጎች ድምጾችን በስልጠና፣ በመስመር ላይ ማስተማሪያ መሳሪያዎች፣ የነፃ አገልግሎ እና መሳሪያዎችን በማስተዋወቅ እና በማቅረብም ጭምር ዜጎች ራሳቸውን መግለጽ የሚችሉበትን ዕድል ማበረታታት፡፡
  • በዓለም ዙሪያ የዜጎችን ሐሳብን የመግለፅ ነፃነት ማበረታታት እና የዜግነት ጋዜጠኞች ያለፍርሃት እና ቅድመ ምርመራና ክስ ሪፖርት ማድረግ እንዲችሉ ጥበቃ ማድረግ፡፡

እባካችሁ፣ ለተጨማሪ መረጃ ለተደጋጋሚ ጥያቄዎች ያስቀመጥነውን መልስ አንብቡ፡፡