የኖቤል የሰላም ሽልማት ለኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ያለወቅቱ የተበረከተ ነበርን ?

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ አዲስ አበባ በተካሄደ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ፤ ታህሳስ 19፣ 2018 (እ.ኤ.አ)፡፡ ፎቶ፡- አሮን ስሜነህ (CC0)

እ.ኤ.አ ጥቅምት 12፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ አሊ የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ከተሸለሙ 24 ሰዓታት ሊሞላቸው ጥቂት ሲቀራቸው፣ የሰላማዊ ሰልፍ አስተባባሪዎች ታስረው፣ አዲስ አበባ ውስጥ ጋዜጣዊ መግለጫ ከመስጠት ታግደው ነበር፡፡  

የቀድሞው የእስር ጓደኛዬ – ናትናኤል የዓለምዘውድ፣ የእስክንድር ነጋ፣ ባልደራስ ምክር ቤት የጠራውን ሰልፍ በማስተባበሩ ምክንያት መታሰሩን ተረድቼአለሁ፡፡ ይህ የተከሰተው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ አሊ የኖቤል ሽልማት ድርጅት ለ2019ኙ የኖቤል የሰላም ሽልማት ከመረጣቸው፣ 24 ሰዓታት ሳይሞላ ነው፡፡

 ‹‹በኦሮሞ ፖለቲከኞች አዲስ አበባ ላይ የሚቀርበው የባለቤትነት ጥያቄ››ን እና የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሲቪል ማህበረሰቡ ‹‹ጭቆናን›› በመቃወም ለጥቅምት 13 የሃገሪቱ ርዕሰ-መዲና ውስጥ መስቀል አደባባይ ላይ ለማካሄድ የታሰበው ሰልፍ የተሰናዳው በባላደራው ምክር ቤት ንቅናቄ ነበር፡፡ የባላደራ ምክር ቤት  ለበርካታ ጊዜያት የተለያዩ ክሶች እየቀረቡበት በመንግስት ሲታሰር በነበረው፣ ኢትዮጵያዊው ጋዜጠኛ እና ጦማሪ እስክንድር ነጋ ይመራል፡፡

ብዙዎች እንደፈሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ መንግስት አዲስ አበባ ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ የማድርግ መብትን የማስጠበቅ ፈተናን የመጀመሪያው ድህረ-የኖቤል ሽልማት ላይ ወድቋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፍ በጥድፊያ ሲፈቀድ፣ ቀደም ተብሎ የታቀደው ሰልፍ ግን ታግዷል፡፡ ይህ ያልተጠበቀ፣ አደገኛ የኦዴፓ ባለስልጣናት አካሄድ ነው፡፡

አቢይ፤ ግርማ ሞገስ ያላቸው ወጣት መሪ

የኖርዌዩ የኖቤል ኮሚቴ፣ ጥቅምት 11 የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊ ሲታወቅ፣ የዶክተር አቢይ አህመድ አሊ ‹‹ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የነበረውን የድንበር ግጭት ለመፍታት የወሰዱት ወሳኝ ተነሳሽነት›› ተጠቅሶ ነበር፡፡ 

ከታላቁ የኢትዮጵያ ህዝብ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ጋር የ2019ኙ የኖቤል የሰላም ሽልማት አሸናፊነት ምክንያት፣ ከቀሪው የአፍሪካ እና የዓለም ህዝብ ጋር ደስታውን ለመካፈል ተቀላቅያለሁ፡፡ የላይቤሪያ መንግስት እና ህዝብ የላቀ ደስታቸውን ለኖቤል ሽልማት አሸናፊው ይገልጣሉ፡፡

ዜናው በደስታ ተቀባይነትን ሲያገኝ፣ በተወሰነ ጥርጣሬም የተቀበለ ወገን አልጠፋም፡፡

የ43 ዓመቱ የቀድሞ የድህንነት ሃላፊ፣ አቢይ በመጋቢት 2፣ 2018 አራተኛው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በቅተዋል፡፡ ወዲያውኑ ባልተገመተ ሁኔታ ብቻ ሳይሆን፣ ከአምስት ዓመት በፊት ሊሆኑ የማይችሉ ተከታታይ ለውጦችን ጀምረዋል፡፡

የእርሳቸው ቀዳሚ የሆኑት፣ ሃይለማርያም ደሳለኝ ኢትዮጵያን በብረት ጡጫ በመግዛት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን በማፈን፣ የተቃዋሚ መሪዎችን እና ፖለቲካዊ ተቃውሞዎችን በሃይል በመጨፍለቅ ነበር ያስተዳደሯት፡፡

ከ80 በላይ ብሔረሰቦች ቢኖሩም፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ብሔር-ተኮር ግጭቶች አዲስ አይደሉም፡፡ ነገር ግን አለመረጋጋቶች እና ተቃውሞዎች፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ሁለት ትላልቅ ክልሎች፣ ኦሮሚያ እና አማራ፣ የአማራ ክልል ወደ ኦሮሚያ ክልል በመስፋፋት ሰበብ ተነስተው የምስራቅ አፍሪካዋን ሃገር ከ2015 እስከ 2018 መባቻ ድረስ ለሁለት ሰንጥቋት፣ ሃይለማርያምን ‹‹ላልተጠበቀ›› የስልጣን መልቀቅ፣ መጋቢት 2018 ላይ አብቅቷቸዋል፡፡   

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ከመከላከያ ሚኒስትሩ ለማ መገርሳ ጋር ተቀምጠው፤ ታህሳስ 24፣ 2017፤ ፎቶ፡- Odaw via Wikimedia Commons CC BY 4.0.

አቢይ የገዢውን – የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ)ን ምርጫዎች - ከ180 ድምፆች፣ 108 ድምፆችን በማግኘት አሸንፈው፣ ሃይለማርያምን ተክተው የፓርቲው ሊቀ-መንበር፣ ከዛም የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን በቅተዋል፡፡

የኦሮሞ ብሔር አባልነታቸው ከክርስቲያን እና ሙስሊም መነሻቸው ጋር፣ በወትድርና ልምዳቸው እና በወታደራዊ ስለላ ባለሙያነታቸው፣ አቢይ ሃገሪቷ ውስጥ ያለውን ውጥረት ሊያረግቡ እንደሚችሉ መሪ ታይተው ነበር፡፡ አንድ የቻተኸም ሃውስ ተንታኝ፣ ‹‹ምስጢራዊው እና ውስብስቡ የትብብር ውቅር›› የሆነው ኢህአዴግ ውስጥ በተካሄዱ ምርጫዎች ድል ስላገኙት አቢይ ሲፅፍ፣ ‹‹እርሳቸው ከመጀመሪያውኑ ብዙዎችን ለሃገሪቱ መረጋጋት፣ አንድነት እና ለውጥን እንደሚያመጡ አሳምነው ነበር፡፡›› ብሏል፡፡

በአንፃራዊ አጭር አካሄድ፣ አቢይ በባለፈው አስተዳደር ወቅት አለመረጋጋቶችን ለመደምሰስ የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማንሳት፣ በሺህዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን አስለቅቀዋል፡፡ በፍጥነት የሚቀያየረው የፖለቲካ ምህዳር ብዙ ስደተኛ ተቃዋሚዎች እንዲመለሱ እና በመቶዎች የሚታሰቡ ድረ-ገፆች እና የቲቪ ጣቢያዎች ከአፈና እንዲላቀቁ አድርጓል፡፡ እንደሚታወቀው፣ አቢይ ጨካኙን የፖለቲካ መጨቆኛ መሳሪያን – የኢትዮጵያ የፀረ-ሽብርተኛነት ህግ አሻሽለዋል፡፡

ግን የእርሳቸው በጣም የሚጠቀሰው ስኬት፣ ለ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት ያሳጫቸው ተግባር ከጎረቤት ኤርትራ ጋር የፈጠሩት ታሪካዊ የሰላም ስምምነት ነው፣

Abiy Ahmed quickly worked out the principles of a peace agreement to end the long “no peace, no war” stalemate between the two countries. These principles are set out in the declarations that Prime Minister Abiy and President Afwerki signed in Asmara and Jeddah last July and September. An important premise for the breakthrough was Abiy Ahmed’s unconditional willingness to accept the arbitration ruling of an international boundary commission in 2002.

አቢይ አህመድ የሁለቱን ሃገራት ‹‹ሰላምም – ጦርነትም-አልባ›› ቅርቃር አስወግደው የሰላም ስምምነቱ መርኆች እንዲተገበሩ በፍጥነት ሰርተዋል፡፡ እነዚህ መርኆች ተረቅቀው፣ በጠቅላይ ሚኒስተር አቢይ እና ፕሬዝደንት ኢሳይያስ፣ ባለፉት ነሃሴ እና መስከረም ወራት አስመራ እና ጅዳ ላይ ተፈርመዋል፡፡ ለዚህ ስኬት ዋነኛው ምክንያት አቢይ አህመድ በ2002 (እ.ኤ.አ) ዓለም-አቀፍ የድንበር ኮሚሽን የተወሰነውን ውሳኔ ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ ለመቀበል በመፍቀዳቸው ነበር፡፡

ነገር ግን የአቢይ የለውጥ ስራዎች ያለተቃውሞ ወደፊት መጓዝ አልቻሉም፡፡ ሰኔ 2018 ትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደ የፖለቲካ ሰለማዊ ሰልፍ ላይ ከተፈጠረ ፍንዳታ እርሳቸው ሲተርፉ፣ ሌሎች ሁለት ሰዎች ተገድለዋል፡፡ እንደታንዛኒያዊው የፓርላማ አባል ጃኑዋሪ ማካምባ – የአቢይ ዘመን አጋር፣ በፃፉት አወዳሽ የትዊተር መልዕክት እንደጠቀሱት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከባድ እና ውስብስብ ሃገር ነች፡፡›› ብለዋል፡፡

የብሔር ግጭቶች 2.9 ሚሊዮን ተፈናቃዮችን 2018 ላይ ሲያስከትሉ፣ ያለፈው ሰኔ ወር አማራ ክልል ውስጥ የከሸፈው መፈንቅለ-መንግስት የሚቀጥለው ዓመት የታቀደው ብሔራዊ ምርጫን ሊገዳደሩ የሚችሉ የፀጥታ ስጋቶች ሆነው አልፈዋል፡፡ በተጨማሪም፣ ኢትዮጵያ እስከአሁን ድረስ ከፍተኛ የድህነት መጠን ያለባት ሃገር መሆኗን፣ በጠንካራ የኢኮኖሚ መዘርዝሮች የተጠቀሰ ነው፡፡ የአቢይ ‹‹ሊብራላዊ ለውጥ-አምጭነት›› ምስል የሚወሰነው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን በመቀየር አቅማቸው ላይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ – በአብይ ቁጥጥር ስር – የኢንተርኔት አገልግሎት መዘጋት መቀጠሉ፣ የተፈጠሩት መቀያየሮች ‹‹ከፖለቲካ ለውጦች በፊት ይልቅ በጣም እየተወሳሰቡ ስለመጡ›› ለማርገብ ነው፡፡ ሃገር-አቀፉ የኢንተርኔት መዘጋት ከሰኔ 11 – 14 የነበረ ሲሆን፣ የአጭር ፅሁፍ መልዕክት አገልግሎቶችም ተዘግተው ነበር፡፡

መስከረም 26 ላይ የኢትዮጵያው የፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶክተር ጌታሁን መኩሪያን የወከሉት የምርታማነት ጭመራ ሴክተር ባለስልጣን አቶ ጀማል በከር ውይይት የኢንተርኔት ነፃነት በአፍሪካ (FIFAfrica) ስብሰባ ላይ እንደተናገሩት፣ ‹‹መንግስት የሃገሪቱን ዲጂታል ቦታ ክፍት ቢያደርግም፣ አሁንም በተለያዩ ዘዴዎች የኢንተርኔት ነፃነትን የሚያውኩ የጥላቻ ንግግሮች እና ሃሰተኛ ዜናዎችን ለመቆጣጠር መሰራት አለበት፡፡›› ብለዋል፡፡

በዚህ ፅሁፍ መጀመሪያ ላይ እንደተገለፀው ዓይነት ሁነት፣ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ እና የፖለቲካ ተቃውሞን የማንፀባረቅ መብት በምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር በተበጣሽ ገመድ ላይ የሚረማመድ ይመስላል፡፡

ጊዜውን የጠበቀ? ወይስ የሚገባቸው?

ኢትዮጵያን ያስጨነቁ ችግሮች አሁንም ቢቀጥሉም፣ ለምን አቢይ ልክ እንደንፁህ አየር ጥሩ አቀባበል ያገኙበትን ምክንያት በቀላሉ ማስተዋል ይቻላል፡፡ አብዛኛዎቹ ገዢዎች ሽማግሌ የሆኑ እና አንዳንዴ አጋር መሪዎች በሚገዙባት አህጉር፣ ነፃው የ43 ዓመት ወጣት ከሽማግሌዎቹ ገዢዎች፣ በብዙ ሁኔታዎች አፈንግጠው ወደ ስልጣን መውጣታቸው የሚያስገርም ነው፡፡

የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ከጂቡቲው ፕሬዝደንት ኢስማኤል ኦማር ጉሌህ ጋር፤ ፎቶ፡- Odaw via Wikimedia Commons (CC BY-SA 4.0).

የዩጋንዳው የ75 ዓመት ባለፀጋው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ካጉታ ሙሴቬኒ፣ 1986 ላይ ስልጣን እንደያዙ በፅናት የእርሳቸው አመራር የተቃወሟቸውን በመደምሰስ፣ የምስራቅ አፍሪካዊቷን ሃገር የፖለቲካ ምህዳር አጥብበውታል፡፡

የጆን ማጉፉሊዋ ታንዛኒያ በፖሊሳዊ አያያዝ ስር ያለች ሲሆን፣ የተቃውሞ ፖለቲካ፣ ሰብዓዊ መብቶች እና የፕሬስ ነፃነትን በቅርቡ – በሃይል እርምጃ አፍናለች፡፡

የ76 ዓመቱ የናይጄሪያው ፕሬዝደንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ለሰብዓዊ መብቶችሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት እና የፖለቲካ ተቃውሞ ያላቸው ትኩረት ያነሰ ነው፡፡

ግን ከቀረቡት ድክመቶች ጋር ስናወዳድረው፣ ለአቢይ በርካታ ውዳሴዎች መቅረባቸው በጣም የቀደመ ሆኖ ይታያል ወይ?

እኛ በዕውነት ማንኛውንም የአፍሪካ መሪ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ እና ሰብዓዊ መብቶች ላይ የጠለሸ ስም ከሌለው በውዳሴ እና በምስጋና መያዝ እንችላለን፡፡

መቼም ፍፁም አይደለንም!

የእኛ ትልቁ ችግር አብዛኛዎቹ የእኛ መሪዎች፣ ንቁ እና ተገቢ ያልሆኑ በመሆናቸው ወደ ጨቋኝነት ይቀየራሉ፡፡

ስለዚህ የእኛ ቁጥር 1 መፈተኛ ነፃነት መሆን አለበት፡፡

የ2009ኙ የኖቤል የሰላም ሽልማት ለባራክ ኦባማ በመጀመሪያወቹ የስልጣን ቀናት ከተበረከተ በኋላ፣ ማንም ሰው እንደሚረዳው፣ የኖቤል ኮሚቴ የተሾመን ፕሬዝደንት ወዲያወኑ ጥንቁቅ ሆኗል፡፡ ለአብነት ያህል፣ ኦባማ ሊቢያ ውስጥ ሰላም አላመጡም፡፡ ይልቅስ እስካሁን ሊረግቡ ያልቻሉ ችግሮች እንዲፈጠሩ አድርገዋል፡፡

ሌሎች ተሸላሚ ሎሬቶችም የገቡትን ቃል መፈፀም አልቻሉም፡፡ በዋናነት የሚጠቀሱት፣ የማይናማሯ ፖለቲከኛ ኡንግ ሳን ሱ ኪ፣ የቁም እስር ላይ እያሉ ሽልማቱን ቢያሸንፉም፣ የሃገሪቱ መንግስት ዋና መሪ ከሆኑ በኋላ ግን በሮሂኒጊያ ሙስሊምች ላይ የተፈፀመውን የዘር ጭፍጨፋ መርተዋል፡፡

የሰሜን ቬይትናም መሪ ሊ ዱች ቶ፣ ሃገራቸው ሰላም አጥታ ባልተረጋጋችበት ወቅት ከሄኔሪ ኬሲንገር ጋር 1973 የቀረበላቸውን ሽልማት አለመቀበላቸው በደንብ ይታወቃል፡፡

የኖቤል ኮሚቴ ከ‹‹ኢትዮጵያ የፀደይ ወቅት›› ዘልሎ ወጥቷል፤ የሰላም ዋጋ ለአቢይ አህመድ!

እርሳቸው ብዙ ለውጦችን በፍጥነት ፈፅመዋል፡፡ ግን ነገሮች የተበታተኑ እየሆኑ ነው፡፡ እናም፣ ኮሚቴው በዚህ ጉዳይ ከመፀፀቱ በፊት፣ በርካታ መንገዶች አሉት፡፡

ማንም ሰው እንደሚረዳው፣ ኮሚቴው እንዲህ ያሉ ሽልማቶችን የሚያበረክተው፣ ተሸላሚው ቃል በገባው አካሄድ እንዲቀጥል በተስፈኛነት ለማበረታታት አስቦ ነው፡፡ ነገር ግን ሽልማቱ ትርጉም የሚሰጠው እስከ አስተዳደሩ መጨረሻ ተቆይቶ፣ ግለሰቡ ቃላቸውን መኖራቸው እና ሽልማቱ የሚገባቸው መሆኑን አስተውሎ መስጠቱ ነው የሚጠቅመው፡፡ 

ለመጠንቀቅ የሚቀርበው ሌላኛው ምክንያት፣ ከላይ የተጠቀሱት አብዛኛዎቹ የአፍሪካ መሪዎች አነሳሳቸው ጨቋኝ ሆነው አለመታየታቸው ነው፡፡ ሙሴቬኒ ተፋልመው፣ ነፍሰ-ገዳዩን ኤዲ አሚንን ከስልጣናቸው አባርረዋል፡፡ ማግፉሊ ስልጣን በያዙበት ወቅት፣ የግልፅነት እና ወጪ ቆጣቢ አመራር አቀንቃኝ ነበሩ፡፡ ቡሃሪ ለአንድነት እና ለሙስና ያላቸው ትዕግስት-አልባነት፣ ናይጄሪያ ለረዥም ጊዜ የጠበቀቻቸው ‹‹መሲህ›› አስመስሏቸው ነበር፡፡ በቅርቡ ያረፉት ሮበርት ሙጋቤ እንኳ፣ የአፍሪካ አንጋፋ የነፃነት ታጋይ ነበሩ፤ ስልጣናቸው ከ37 ፈታኝ ዓመታት በኋላ ያለምህረት ቢፈነቀሉም፡፡ 

ተቺዎች ጨምረው እንደሚናገሩት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ለውጡን ለመምራት በተክለ-ሰብዕናቸው ላይ ተንተርሰዋል››፤ መንግስታዊ ተቋማትን ከማዋቀር ይልቅ፡፡ ይህ የመንግስት ቢሮክራሲን ለመቀነስ የተሟላ እና ጠቃሚ ሊሆን ቢችልም፣ አስተማማኝ የረዥም ጊዜ ለውጦችን መሰረት ለመጣል አያስፈልግም፡፡

አቢይ ከሌሎች ተለይተው፣ በሰላም እና የለውጥ መንገድ ላይ መጓዛቸውን ይቀጥላሉ? ወይስ የእርሳቸው የአህጉር ዘመነኛዎች በተጓዙበት የታወቀ መንገድ ይከተላሉ? ለኢትዮጵያ እና አፍሪካ አክራሞት፣ ቀዳሚው ይሆናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ 

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.