አዳዲሶቹን ‘የግሎባል ቮይስስ’ ከሰሃራ በታች አርታኢዎች – እንዳልክ ጫላ እና ኦማር ሞሐመድ ተዋወቁ

እንዳልክ ጫላ (ግራ) እና ኦማር ሞሐመድ (ቀኝ), አዲሶቹ ከሰሀራ በታች ያለ የአፍሪካ ጉዳዮች አርታኢዎች

ትልቅ መልካም ዜና አለን! ሁለት የማኅበረሰባችን አባላት – እንዳልክ ጫላ እና ኦማር ሞሐመድ በንዴሳንጆ ማቻ ተይዞ የነበረውን ከሰሀራ በታች ላለው የአፍሪካ ጉዳዮች የአርታኢነት ቦታ እየተረከቡ ነው።

እንዳልክ ነዋሪነቱ ኦሪገን፣ አሜሪካ ነው። የማኅበረሰባችን አባል የሆነው እኤአ በ2011 ጀምሮ ነው። ብዙዎቻችሁ ከዞን9 ጋር በተያያዘው የአራማጅነት እንቅስቃሴው ታውቁት ይሆናል። ሌሎቻችሁ ደግሞ ናይሮቢ ጉባዔያችን ላይ አግኝታችሁት ሊሆን ይችላል። እንዳልክ ባሁኑ ወቅት በኦሪገን ዩንቨርስቲ የዶክትሬት ትምህርቱን ይከታተላል። በኢትዮጵያ የዞን 9 ጦማርያን ስብስብ የጋራ መሥራች ነው። ከኮምፒዩተር ሰሌዳ ላይ ዓይኑን ሲያነሳ፣ 18 ወራት ከሞላት ልጁ ጋር ጊዜውን ለማሳለፍ ብሎ ነው። አሁን የዱክትርና ምርምሩን በኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሚዲያ ላይ እየሠራ ነው። እንዳልክ ባለፉት ዓመታት አንዳንድ ምርጥ ዘገባዎችን ለGV አበርክቷል። እስካሁን ካላነበባችሁት በኢትዮጵያ ስላለው የሙዚቃ ሳንሱር የጻፈውን እንጠቁማችኋለን።

ኦማር ነዋሪነቱ ዳሬሰላም፣ ታንዛኒያ ነው። የማኅበረሰባችን አባል የሆነው እኤአ ከ2013 ጀምሮ ነው። በአሁኑ ወቅት የብሉምበርግ ሪፖርተር ሲሆን፣ ኮድ ፎር ታንዛኒያን የሚመራው እሱ ነው። ለኳርትዝ አፍሪካ እና ‘ሀባ ና ሀባ’ (ጥቂት በጥቂቱ) የተሰኘ ሳምንታዊ የሬዲዮ ዜና መጽሔት በማቅረብ ለቢቢሲ ስዋህሊ ሠርቷል።  በአሪዞና ዩንቨርስቲ ዋልተር ክሮንካይት የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ውስጥ የፉብራይት ፌሎ ነበር። ከጋዜጠኝነት ሥራው ረፍት ሲወስድ እግር ኳስ እና ቅርጫት ኳስ መመልከት፣ ልቦለድ ማንበብ፣ ሙዚቃ ማድመጥ እና በቴሌቪዥን መመሰጥ ይወዳል። ኦማር አንድ ቀን ረዥም የስፖርት ጋዜጠኝነት ጽሑፍ ማበርከት ያልማል። የኦማር የመጨረሻ ሁለት ጽሑፎቹ በጣም መሳጭ ናቸው። አሜሪካ ያጣችው ፍቅር እና  የታንዛኒያ የእግር ኳስ ፍቅር የሚሉትን ተመልከቱ።

እባካችሁ ኦማር እና እንዳልክን ከእኛ ጋር በመሆን እንኳን ደስ አላችሁ በሏቸው!

ንዴሳንጆን በዓመቱ መጀመሪያ ላይ ተሰናብተነዋል። ነገር ግን አንድ ሞቅ ያለ ስንብት ይቀረናል። አሁንም ድረስ ከዐሥር ዓመታት በላይ የመራውን የግሎባል ቮይስስ ከሳሃራ በታች ያለው የአፍሪካ ክፍል ጉዳይ ቅሪቶቹን እያስተካከለ ነው።

ንዴሳንጆ ከGV ቤተሰብ ጋር ከጅምሩ አንስቶ ነበር። መጀመሪያ እንደበጎ ፈቃደኛ ጸሐፊ፣ ቀጥሎ ከሰሃራ በታች ላለው አፍሪካ እንደአርታኢ በመሆን። ከዐሥር ዓመት በኋላ እሱ ሲወርድ ልክ የአንድ ዘመን ማብቃት ያህል ነው። እኤአ ከ2006 ጀምሮ ንዴሳንጆ ንቁ፣ ብቁ እና መልካም የሆነ ማኅበረሰብ ሰፊ፣ ውስብስብ ከሆነውና በተሳሳተ መልኩ ከሚገለጸው ይህ አካባቢ አፍልቆ መገንባት ችሏል። የንዴሳንጆ አካባቢያዊ ኃላፊነት ግዙፍ ቢሆንም በብልሐትና በጥንቃቄ ከመወጣቱም ባሻገር ባለፉት ዐሥር ዓመታት ከ4,500 በላይ ትርክቶችን ለግሎባል ቮይስስ መጻፍ ችሏል። ንዴሳንጆ፣ አሁንም ቢሆን ልብህ የተሰጠለትን የመጻፍ ክኅሎትህን በግሎባል ቮይስስ ላይ ለማየት እናማትራለን።

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.