የኦሮሞ ሙዚቀኞችን የማፈን አሳፋሪ ገመና

Oromo singer Hawi. Photo from her official Facebook page.

ጋዜጠኞችና ጦማሪዎች የመንግሥት አፈና ግንባር ቀደም ተጠቂዎች በሆኑባት ኢትዮጵያ፣ ከመንግሥት ፕሮፓጋንዳ የማይገጥሙ ሙዚቀኞችም ትኩሳቱን እየተቀላቀሉ ነው፡፡

ሐዊ ተዘራ፣ የኦሮሞ ዘፋኝ ስትሆን በኢትዮጵያ ትልቁ ክልል ኦሮሚያ ውስጥ እየተካሄደ ካለው የአደባባይ ተቃውሞ ጋር ግንኙነት አለሽ በሚል በፖሊስ ተደብድባ ከታሰረች በኋላ ተፈትታ በሰባት ቀን ጊዜ ውስጥ መልሳ በድጋሚ እንደታሰረች ሪፖርት ተደርጓል፡፡

ሁለት ሥማቸው ለደኅንነታቸው ሲባል እንዳይገለጽ የፈለጉ የኦሮምኛ ዘፋኞችም፣ ለዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ሕዳር ወር ላይ የአደባባይ ተቃውሞው ከተጀመረ ወዲህ በጥብቅ ክትትል ውስጥ እንደሚገኙ ነግረውታል፡፡

አንድ ግምታዊ ስሌት እንደሚያመላክተው፣ የዋና ከተማዋ አዲስ አበባ፣ የኢትዮጵያን ሲሦ ያክል ሕዝብ ያለው የኦሮሞ ብሔር ወደሚኖርበት አካባቢ ለማስፋፋት የተዘጋጀውን የመንግሥት ዕቅድ በመቃወም በተነሳው የአደባባይ ተቃውሞ ከመቶ በላይ ሰልፈኞች ሞተዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዐሥርት ዓመታት፣ ወደ ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ አራማጅነት ያደሉ የኦሮምኛ ዘፋኞች ለውክቢያ፣ ጠለፋ እና ስቃይ እየተዳረጉ ነው፡፡

በኢትዮጵያ ከሁሉም ዋና-ዋና ሕዝቦች በጣም ብዙ ሙዚቀኞች የተሰደዱት የኦሮምኛ ቋንቋ ዘፋኞች ናቸው፡፡

ከዚህ ቀዝቃዛ ዘመቻ ዕውቅ ሰለባዎች አንዱ ተወዳጁ ኢቢሳ አዱኛ ሲሆን፣ ሲቪል አራማጆች በ1988 የተገደለው በመንግሥት ኃይሎች ነው ብለው ያምናሉ፡፡

ዳዊት መኮንን፣ በ1980ዎቹ የኦሮምኛ ትውፊታዊ ዜማዎችን ከዘመናዊ ሙዚቃ ጋር እያዋሃደ በመጫወት የሚታወቅ ዘፋኝ ሲሆን፣ ለስደት የተዳረገው በ1990ው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጦርሜዳ ላሉ ወታደሮች እንዲዘፍን ተጠይቆ ባለመስማማቱ ነው፡፡

የኦሮምኛ የምን ግዜም ምርጥ ሴት ድምፃዊት ናት የሚባልላት እልፍነሽ ኬኖ ወደ ኖርዌይ ለመሰደድ በተገደደችበት ተመሳሳይ ጊዜ፣ ዳዊት በተሰደደበት ወቅት የተሰደደው ድምፃዊ ሂርጳ ጋንፉሬም ተገዶ በተሰደደባት ስካንዲኔቪያዊቷ አገር ዘፈኖችን አውጥቷል፡፡

እነዚህ ጥቂት በይፋ የሚታወቁ ብቻ የኦሮሞ ሙዚቀኞች ላይ እየደረሰ ያለው አፈና ማሳያዎች ናቸው፡፡

አዲስ የሳንሱር ማዕበል?

በኢትዮጵያ ከመንግሥት መሥመር በተቃራኒ የሚቆሙ ሙዚቀኞች የኋላ ማንነታቸው ማንም ይሁን ምን በኢትዮጵያ ሬድዮ ጣቢያዎች የአየር ሰዐት ማግኘትም ይሁን በመድረክ ላይ ሥራዎቻቸውን ማቅረብ ይቸገራሉ፡፡

ባለፈው ዓመት ሊያቀርባቸው የነበሩ ሁለት ኮንሰርቶች በመጨረሻዋ ደቂቃ የተሰረዙበት ዕውቅ የአማርኛ ዘፋኝ እና የዜማ ጸሐፊ ቴዲ አፍሮ አንዱ ምሳሌ ነው፡፡ ቴዲ ትልቅ ሕዝባዊ ተቀባይነት ያለው እና በእጅጉ ስኬታማ መሆን የቻለ ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ነው፡፡

ቴዲ፣ እሱ እስካሁን ባላመነው ገጭቶ የማምለጥ ክስ ታስሮ በ2001 ከተፈታ በኋላ ባለፈው ዓመት መስከረም ወር ላይ ሊያቀርባቸው የነበሩ ኮንሰርቶች፣ ምክንያቱ ሳይገለጽ ፈቃድ መከልከላቸውን ተናግሯል፡፡

የኮንሰርቶቹ መሰረዝ ቴዲ ከመታሰሩ ሦስት ዓመት ቀደም ብሎ፣ በ1997 ከለቀቃቸው መንግሥትን የሚተቹ ዘፈኖች በኋላ የቀጠለ የአፈና ዘመቻ ይመስላል፡፡

ይሁን እንጂ አፈናው በኢትዮጵያ ብዙ ሕዝብ ባለውና ከሰሜናዊው የሕዳጣን ትግራይ ክልል ውስጥ ለወጡት የመንግሥት ፖለቲካ አመራሮች ተቀናቃኝ ይሆናሉ የሚባሉት ኦሮሞዎች ዘፋኞች ላይ እንደሚበረታ ይስተዋላል፡፡

አንዳንድ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት፣ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን ግጥሞቻቸው “የብሔርተኝነት አዝማሚያ” አላቸው ተብለው የሚታሰቡ ቢያንስ 17 የኦሮሞ ዘፋኞች ዘፈኖችን እንዳይሰራጩ አግዷል፡፡

የኦሮሞ ዘፋኞች ብዙውን ጊዜ ብሔራዊ ማንነትን እና ባሕላዊ ቅርሶችን የሚያወድሱ ዜማዎች በግጥሞች ወይም በባሕላዊ መሣሪያዎች እና ዜማዎችን በመጠቀም ይጫወታሉ፡፡

የቅርብ ጊዜ እገዳው ደግሞ ብሔርተኛ ከሆኑ ሙዚቃዎችም ውጪ ሆኗል፡፡ ይህ እገዳ ከላይ የተጠቀሱት ሁለት ድምፃውያን ዘፈኖችን ይጨምራል፡፡

ይህ የሚያሳየው መደበኛ የባሕላዊ መገለጫዎችንም መንግሥት ማፈን መጀመሩን ነው፡፡

የማጨናገፍ ፖሊሲ

ማይክል ሻውን ሞለንሀወር የተባሉ ምሁር ለዶክትሬት ዲግሪያቸው ሟሟያ በሠሩት ጥናት ላይ የኦሮሞ ባሕል ላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለሚደረግ ሳንሱር በጻፉት ጽሑፍ፣ አሁን ያለው መንግሥት የሚፈልገውን ዓይነት የባሕል ብዝኃነት የሚያሳዩለትን የኦሮሞ ሙዚቀኞች እየተጠቀመ ነጻና ገለልተኛዎቹን ዘፋኞች ግን በዘዴ ለውክቢያ እና እስር ይዳርጋቸዋል፡፡

የሐዊ ተዘራ ታሪክ መንግሥት የደረሰበት ራስን የመግለጽ ነጻነትን የማፈን ደረጃ ምን ያክል ይበልጥ እንደጠበቀ እና ሙዚቃንም ጭምር እስከማፈን እንደወረደ ማሳያ ነው፡፡

ነገር ግን፣ እርምጃው የሚፈለገውን ውጤት እያመጣ አይደለም፡፡

እንዲያውም፣ የመንግሥት ሳንሱርን ለመስበር አማራጭ ይዞ የመጣውን ኢንተርኔት በመጠቀም፣ በዚህ ጽሑፍ ጸሐፊ ዩቱዩብ እና ፌስቡክ ላይ በተደረገ ቆጠራ ብቻ ከ300 በላይ ፖለቲካ ነክ ዘፈኖች ከ2006 ወዲህ የተለቀቁ መሆኑ የፖለቲካ ዘፈኖች መነሳሳት አለ ብሎ ለማለት ያስችላል፡፡

የሙዚቃ ሳንሱሩ የፈየደው ነገር ቢኖር የኦሮሞ ብሔርተኝነትን መጨመሩ ነው፡፡

ብዙኃን ኦሮሞዎች አሁን ማንነታቸው አላግባብ እንደተጠቃ ይሰማቸዋል፤ የፖለቲካ ተቃውሟቸው ላይ በመንግሥት እየተሰነዘረ ያለው ጥብቅ ጥቃትም ብዙዎቹን ወደጠርዝ እየገፋቸው ነው፡፡

ይህ ጽሑፍ በዓለማችን ላሉ ሙዚቀኞች ቀዳሚ ተሟጋች በሆነው በፍሪምዩዝ እና የዓለም ድምፆችጥበብ ነጻነት ኮሚሽን ተደርጓል፡፡ መጣጥፉ በሌሎች የንግድ ባልሆኑ ብዙኃን መገናኛዎች የጸሐፊው ሥም እንዳልክ፣ ፍሪምዩዝ እና የዓለም ድምፆች ተጠቅሰው እና የመጀመሪያው ጽሑፍ ሊንክ ተያይዞ ሊታተም ይችላል፡፡

1 አስተያየት

ንግግሩን ይቀላቀሉ

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.