ኢትዮጵያ ‹ታይቶ ከማይታወቀው› የኢኮኖሚ ዕድገቷ በተፃራሪ ረኀብ ተጋርጦባታል

A drought affected farm in Ethiopia. A Public Domain image by Photographer: Kimberly Flowers/USAID.

ኢትዮጵያ በቅርብ ዓመታት ካስመዘገበችው የሁለት አሐዝ የኢኮኖሚ ዕድገት በተቃራኒ ከፍተኛ የምግብ ዕርዳታ ያስፈልጋታል፡፡ ታዛቢዎች እንደሚሉት የአሁኑ የምግብ ቀውስ በሠላሳ ዓመታት ውስጥ የከፋው ሲሆን የብዙ ሺሕዎችን ነፍስ ከቀጠፈው ከ1977ቱ ረሀብ ተመሳሳይ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የሰብኣዊ ጉዳዮች አስተባባሪ ቢሮ አንድ ሪፖርት እንደሚለው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በዚህ ወር 4.5 ሚሊዮን ጨምሯል፡፡

የመንግሥት ኃላፊዎች እንደገመቱት 10.1 ሚሊዮን ሰዎች እ.ኤ.አ. በ2016 ከፍተኛ የረኀብ ቀውስ ይገጥማቸዋል፡፡ ቁጥሩ 5.75 ሚሊዮን ሕፃናትን ይጨምራል፡፡

የአገሪቱ የረኀብ ቀውስ በኢትዮጵያ መንግሥት ዝቅ ተደርጎ ከመታየቱም ባሻገር መንግሥት የረኀቡን ሥም በመቀየር “የምግብ እጥረት” እንደሆነ ገልጧል፡

ከኢትዮጵያ ውስጥ በተገኘ መረጃ መሠረት፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች “ረኀብ፣ ችጋር ወይም ሞት” የሚሉ ቃላቶችን በምግብ ጥያቄዎቻቸው ውስጥ እንዳያካትቱ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም “ሕፃናት በየዕለቱ እየሞቱ ናቸው” ወይም ደግሞ “ሰፋ ያለ የረኀብ አደጋ” ወይም “የመንግሥት ፖሊሲ ለረኀቡ በከፊል ተጠያቂ ነው” የሚሉ ሐረጎችንም መጠቀም አልተፈቀደም፡፡ “ይህንን ረኀብ ከ1977ቱ ድርቅ ጋር ማነፃፀር”ም እንዲሁ አልተፈቀደላቸውም፡፡ እንዲሁ ብቻ “በኤል ኒኞ ምክንያት የተከሰተ የምግብ እጥረት” በሚል እንዲገልጹ ታዘዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተው “የምግብ እጥረት” ኤል ኒኞን ተከትሎ በመጣው ድርቅ ሳቢያ ነው ቢልም ዳዊት አየለ ኃይለማርያም የተባለ በፓሳው ዩንቨርስቲ የፖለቲካል ሳይንስ ማስተርስ ዲግሪ ተማሪ ግን በተቃራኒው ነው የሚያስበው:

ብዙ ባለሙያዎች የኢትዮጵያን የከፋ ረኀብ ዝናብ ላይ ጥገኛ የሆነ አነስተኛ የአስተራረስ ዘዴ፣ ድርቅ፣ ፈጣን የሕዝብ ዕድገት ወይም የእርሻ ገበያ መውደቅ ጋር ያገናኙታል፡፡ ምንም እንኳን እነዚህ ነገሮች በጉዳዩ ላይ የላቀ ሚና ቢኖራቸውም፣ በአገሪቱ ያለውን ዋነኛ የችጋር መንስኤ ግን ይሸሽጋሉ – እነዚህም የመብቶች አለመከበር እና ተጠያቂነት ያለበት መንግሥት እጦት ናቸው፡፡ […]

የረኀብ ታሪካዊ ዳራው ሲጠና በ20ኛው ክፍለ ዘመን 30 ትላልቅ ረኀቦች ተከስተዋል፡፡ ሁሉም የተከሰቱት በአምባገነን መንግሥታት ሥር ወይም በትጥቅ ትግል ውስጥ ባሉ አገሮች ውስጥ ነው፡፡ አራቱ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው የተከሰቱት […] አምባገነንነት ለምን ለረኀብ ይዳርጋል? ዋነኛው ምክንያት አምባገነኖች ረኀብን ለመከላከል በሚያዘጋጅ ሁኔታ ለሕዝባቸው አይጨነቁም፡፡ አምባገነኖች ሥልጣናቸውን የሚያስጠብቁት በኃይል እንጂ በሕዝባዊ ይሁንታ አይደለም፡፡ ሙግቱ በኢትዮጵያም ታይቶ እውነትነቱ ተረጋግጧል፡፡

ከሰሀራ በታች ካሉት አገራት 5ኛውን ትልቁን ኢኮኖሚ የያዘችው አገር የገጠማት የረኀብ ቀውስ፣ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ዘንድ የሞቀ መወያያ ሆኗል፡፡

አዲሱ ሀብቴ ዳያስፖራዎች የአገራቸው ዜጎች እየሞቱ ሳለ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ማውራታቸውን እንደነውር በመቁጠር በነገር ሸንቁጧቸዋል

ፊላደልፊያ ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምንም ሳያደርጉ ነገር ግን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እና ደንኪን ዶናትስ እና ሺሻ ቤቶች ውስጥ ፖለቲካ ሲያወሩ ኢትዮጵያውያን ግን እየተራቡ ነው […] ኢትዮጵያውያን በረኀብ ሲሞቱ ዝም ብለን አንይ፡፡

እንዳልካቸው ጫላ ደግሞ ይህን ጻፈ:

አዎ! ‹በፍጥነት አዳጊው› የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጉዱ ፈላ…

ቤተልሔም ኤፍሬም ኢትዮጵያውያን ጉዳዩን ፖለቲካ እንዳያደርጉት መክራለች:

ለአንዴ እንኳ ጉዳዩን ከፖለቲካ ተዋስኦዋችን ይልቅ ለመትረፍ ስለሚፍጨረጨሩት ሰዎች እናድርገው፡፡ በዚህ ቀውስ ወቅት በሕዝቦች ላይ አንቀልድ፡፡

አናንያ ሶሪ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ 4.5 ሚሊዮኖች ረኀብ ገጥሟቸዋል የሚለው ውስጥ የቁጥሩ ምንጭ ከየት እንደሆነ ሲጠይቅ ከአዲስ ስታንዳርድ የተሰጠው መልስ:

ውድ አናንያ ሶሪ፣ በሰፊው እንደሚታወቀው ቁጥሮች (በዚህ ጉዳይ) በመንግሥት እና የዕርዳታ ድርጅቶች መካከል (ወይም በዕድገት ጉዳይ) በመንግሥት እና የፋይናንስ ተቋማት መካከል የሚደረግ ድርድር ውጤት ነው፡፡ ነገር ግን በይፋ የታወቀ የምርት ውድቀት በአገሪቱ በተንሰራፋበት በዚህ ወቅት፣ ቁጥሩ የተጋነነ አይመስልም፡፡

ዜጎች መፀለይ አለባቸው ለሚለው ጥያቄ ሲመልስ፣ ቢያ ኦሮሚያ እንዲህ ብሏል:

በኢትዮጵያ ለተከሰተው ረኀብ ፀሎት እንዴት ነው መፍትሔ የሚሆነው? የተራቡ ሰዎች የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ እና መልካም የግብርና ፖሊሲ ከመልካም የፖለቲካ ፈቃደኝነት እና ዴሞክራሲ ጋር ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡ ረኀብ በኢትዮጵያም ሆነ ሌላ ቦታ ከእግዜር ጋር የሚያገናኘው አንዳች ነገር የለም፡፡ ረኀብ በስርዓቶች የፖሊሲ ውድቀት፣ የፖለቲካ ጭቆና እና የአየር ንብረት ለውጥ ድምር ውጤት የሚከሰት ነገር ነው፡፡ ጥሩ ምክር የሚሆነው ስርዓቱን ማስወገድ እንጂ እንድንፀልይ ማዘዝ አይደለም፡፡

ፍቅረየሱስ አምሀፅዮን የተባለ የአፍሪካ ልማት፣ ሰብኣዊ መብቶች እና ፖለቲካዊ ኢኮኖሚ ላይ የሚያተኩር የምሥራቅ አፍሪካ ምሁር ደግሞ የረኀብ ቀውሱን በተመለከተ ሌላ አስተዛዛቢ ጉዳይ ጠቁሟል:

ኢትዮጵያ የረኀብ ቀውስ ተጋርጦባት አስቸኳይ የምግብ ዕርዳታ እየጠየቀች እያለ ብዙ ቶን ምግብ ከአገሪቷ እየወጣ መሆኑ አስተዛዛቢ ነው፡፡ ይህ የማይገባ ልማት የተፈጠረው ደግሞ አዲስ አበባ የተቀመጠው መንግሥት ትልልቅ ለም መሬቶችን “መሬት መቀራመት” እየተባለ በተተቸ መንገድ ለውጭ ኢንቨስተሮች እና ኮርፖሬሽኖች በመቸብቸቡ ነው፡፡ ሒደቱ የአካባቢው ነዋሪዎችን ለትላልቅ የውጭ አልሚዎች ሲባል በግድ የማፈናቀልና “ሰፈራ”ን ያካትታል፡፡ የመብት ተቆርቋሪዎች ግድያዎች፣ ድብደባ፣ መደፈር፣ እስር፣ ማዋከብ እና ፖለቲካዊ ተፅዕኖን የሚያካትቱ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች በመንግሥት እና ባለሥልጣናት እንደተፈፀመ አጋልጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ የረኀብ ቀውስ አስቸኳይ ትኩረት የሚሻ ሰብኣዊ ጉዳይ ነው፡፡ ሁኔታውን በጥቅሉ ለመረዳት የአካባቢ ሁኔታ አንዱ ምክንያት እንደሆነ ቢታወቅም፣ በተጨማሪም ማኅበረ-ፖለቲካዊ እና የአስተዳደር ሁኔታው፣ ሙስና፣ የሕግ የበላይነት እጦት፣ የመልካም አስተዳደር አለመኖር፣ የረዥም ግዜ ዕቅድ ክሽፈት፣ የተሳሳተ ብሔራዊ እና የልማት ትኩረት ከፍተኛ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡

በመጨረሻም፣ የዓለምዐቀፉ የምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም፣ የልማት ስትራቴጂ እና አስተዳደር ክፍል ዳይሬክተር ፖል ዶሮሽ እና የተቋሙ የገበያ፣ ንግድ እና ተቋማት ክፍል የበላይ ተመራማሪ ሻሂዱር ራሺድ ድርቁ ወደ ረኀብ እንደማያመራ ተስፋ ያደርጋሉ:

የ2008ቱ ድርቅ እና የምርት መቀነስ በኢትዮጵያ ረኀብ አያስከትልም፡፡ ከቀድሞ ረኀቦች ትምህርት በመቅሰም መንግሥት እና ዓለምዐቀፍ ለጋሽ ማኅበረሰቦች ለሚያስፈልጋቸው የእህል አቅርቦት እና በገንዘብም ይሁን በቁስ የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ ቀድሞ ማዘጋጀቱን እና ምግብ ለሚያስፈልጋቸው መድረሱን ያረጋግጣሉ፡፡ ሌሎች የምግብ ፍላጎት መሟላት እና ተመጣጣኝ ምግብ ለሁሉም ግለሰቦች የመዳረሱ ጉዳይም ይቀረፋል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ በኢትዮጵያ ባለፉት 25 ዓመታት የታየው መሻሽል፣ ብልህ ፖሊሲ እና በወቅቱ የመድረስ ሙከራ ድርቁ ወደ ረኀብ እንዳያድግ ተስፋ ይሆናሉ፡፡

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.