የቴዲ አፍሮ አዲስ አልበም ፈጣን ተቀባይነት አገኘ

እኤአ በ2015ቱ የዓለም የአካባቢ ቀን የአሜሪካ ኤምባሲ ስፖንሰር ያደረገው የተማሪዎች ወርክሾፕ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረገው ቴዲ አፍሮ። ፎቶ የአሜሪካ ኤምባሲ፣ አዲስ አበባ CC BY-ND 2.0.

በአድናቂዎቹ በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የኢትዮጵያዊው ዘፋኝ ቴዎድሮስ ካሣሁን አልበም በሚያዝያ 2009 ተለቋል።

ቴዲ አፍሮ በሚለው መጠሪያው ይበልጥ የሚታወቀው ዘፋኝ በዚህ — አምስተኛ — አልበሙ 15 የመታሰቢያ እና የፍቅር ዘፈኖችን አጋርነት፣ እርቅ እና በብዝኃነት መሰባሰብን የሚዳስሱ ጉዳዮችን አካቷል። አልበሙ በአንዳንዶች አላግባብ የሚተቹትን ሰዎች የገለጸበት እንደሆነ ተደርገው የተቆጠሩ ቅኔዎችንም ይዟል።

በ1993 የበኩር አልበሙን ከለቀቀ በኋላ ቴዲ አፍሮ በኢትዮጵያ ቤተኛ ሥም ሆኗል። ተወዳጅ ዜመኛ እና ሥመ ጥር የዘፈን ግጥም ደራሲ ነው። “ኢትዮጵያ” የተሰኘው ነጠላ ዜማ ከመለቀቁ ዩቱዩብ ላይ ሚሊዮኖች ተመልክተውታል። አልበሙ፣ ከዚህ በፊት የትኛውም ኢትዮጵያዊ ዘፋኝ ያልተጠጋውን 15 ሚሊዮን ብር አውጥቷል። ይህም ስለዝናው ይናገራል።

በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ብቻ የቴዲ አፍሮ ነጠላ ዜማ 1·9 ሚሊዮን ተመልካች ዩቱዩብ ላይ አገኘ። እጅግ አስገራሚ!

- ሚክያስ – ኤፕሪል 25, 2017

የቴዲ አፍሮ አልበሞች ጭብጥ የሚያጠነጥነው የዘውግ ድንበሮችን የተሻገረ አገርዐቀፍ ኅብር፣ አንድነት እና ፍቅር ለማምጣት የመጣር አስፈላጊነት ላይ ያተኩራሉ።

ይህንን መሠረት በማስፋት አዲሱ አልበም በግጥሙ እና ጭብጡ መልዕክቱን ያጠናክራል። አልበሙ በዋነኝነት በአማርኛ ቋንቋ የተዘጋጀ ቢሆንም የዘፋኙን ፍልስፍና እና ዝንባሌ የሚያጠናክሩ የተወሰኑ ስንኞችን በኦሮምኛ፣ ትግርኛ እና ሲዳምኛ የመሳሰሉ ቋንቋዎች ቀይጧል።

በሬጌ የሚጫወታቸውን ዜማዎች ከኢትዮጵያ ምት፣ ቅኝት እና መሣሪያዎች ጋር ይቀይጣቸዋል። አማርኛ እና ኦሮምኛ ቀይጦ በሚዘፍንበት አንድ ዜማው አገርኛውን መሰንቆ ከአኮስቲክ ጊታር፣ ቤዝ ጊታር እንዲሁም ድራም ጋር አዋኅዶ የተጠቀመው አንድ ምሳሌ ነው።

አና ኛቱ – ለኔ ያርገው – ቴዲ አፍሮ አፋን ኦሮሞን ከሬጌ ጋር ቀይጦ ተጫወተው። ምርጥ!

- ብሥራት ተሾመ – ሜይ 2, 2017

ለቴዲ አፍሮ አልበም የተሰጠው ምላሽ ድብልቅልቅ ያለ ነው። አድናቂዎቹ እና ተቺዎቹ በዝናው፣ በግጥሞቹ እና ሌላው ቀርቶ በሲዲ ሽፋን ምስሉ ሳይቀር ወይ ውዳሴ ወይ ነቀፋ ሰንዝረዋል።

ወዳጆቹ ስለጉብዝናው ሲወዱት፣ ተቺዎቹ ግን ውስብስቡን የኢትዮጵያ ታሪክ በማቃለል ይከሱታል።

ሙዚቃና ፖለቲካ ሲጋቡ

ቴዲ አፍሮ ያለው ለፅንፍ የቀረበ አድናቆት — እና ተቃውሞ — በኢትዮጵያ የሙዚቃ ትችት ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ጋር አብሮ እንደተበየደ ያመላክታል።

“ኢትዮጵያ” የሚለው አልበሙ የዛሬ ሦስት ሳምንት ከተለቀቀ ወዲህ በማኅበራዊ ሚዲያዎች የተካሔደው አብዛኛው ክርክር ስለ ቴዲ የፖለቲካ ዘፈኖች ነበር። ወካይ ያልሆነ የኢትዮጵያ ታሪክ በመጻፍ እና የተለመዱ እና ትርጉም የማይሰጡ የዘፈን ግጥሞችን ጽፏል በሚል ያልተጠበቀ ትችት አስተናግዷል።

ከሙዚቃ ሥራው ጥራት ይልቅ የፖለቲካ ይዘቱ ትኩረት ስለተሰጠው የጥበብ ይዘቱ ብዙም ትኩረት አላገኘም። ሆኖም ዜማዎችን ከቀድሞ አልበሞች ደግሞ በመጠቀም እና ከሌሎች በመሥረቅ በሐሰት የወነጀሉት ግን አልጠፉም።

ኃይለኛ ግን ተጋላጭ

ቴዲ አፍሮ በጣም ተፅዕኖ ፈጣሪ አርቲስት የመሆኑን ያክል – ማኅበረፖለቲካዊ ንቃት የተላበሱ ዘፈኖችን በፖለቲካ አፋኝ ምኅዳር ውስጥ በመጫወቱ ተጋላጭም ነው። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የጋዜጠኝነትም ይሁን ባሕላዊ የፖለቲካ መልዕክቶችን በማፈን ይታወቃሉ።

ቴዲ የሚመለከታቸው አካላት ፈቃድ አንሰጥም በማለታቸው ኮንሰርት በዋና ከተማዋ እንዳያዘጋጅ ተከልክሏል። ለሌላ ኮንሰርት ወደ ውጭ አገር ሊጓዝ ሲል ተከልክሎም ያውቃል። በ2006፣ ባልታተመ ሳምንታዊ መጽሔት ላይ አድርጎታል በተባለ “ፖለቲካዊ አስከፊ” ንግግር ሳቢያ፣ የተወሰኑ ሰዎች አንድ የቢራ ኩባንያ የቴዲን ብሔራዊ የኮንሰርት ዕቅድ ስፖንሰር ከማድረግ እንዲቆጠብ ዘመቻ አድርገውበታል።

በ1997፣ ቴዲ አፍሮ ሁለተኛ አልበሙን ሲለቅ አምስት ዘፈኖቹ ፖለቲካዊ መልዕክት ስለነበራቸው ሥሙ ከተቃውሞ ፖለቲካ ጋር ተያይዟል። በተለይ “ጃ ያስተሰርያል” የተባለው አንዱ ገላጭ ዘፈኑ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ተቀናቃኞች መካከል የእርቅ ጥሪ የሚያደርግ፣ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴን የሚያወድስ ወይም ደግሞ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃሉን ባለመጠበቁ የሚወቅስ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ብዙዎች ይህንን ዜማ ከድኅረ 1997ቱ ምርጫ ቀውስ ጋር ስለሠመረላቸው የመንግሥት ተቃውሞ መዝሙራቸው አድርገውታል።

በ፪ ሺሕ ቴዲ አፍሮ በመኪና ገጭቶ በማምለጥ ወንጀል  ተከሶ ሁለት ዓመታት ገደማ እስር ተፈረደበት።  ቴዲ ክሱን አልተቀበለውም፤ ብዙ አድናቂዎቹም ክሱ የሐሰት እንደሆነና ፖለቲካዊ መግፍዔ እንዳመጣበት ነው የሚያምኑት።

ቴዲ ምንም እንኳን ሙሉ ለሙሉ የተቃውሞ ፖለቲካ ገጽታን ባይላበስም፣ ፖለቲካዊ ስርዓቱ እንዲስተካከል ግፊት ሳያደርግ የኢትዮጵያ ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና ማንነታዊ አሰባሳቢነት ተቀባይነት እንዲያገኝ ጫና ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ራዕይ

በኢትዮጵያ ታሪክ፣ ብዘዎች የሚቀበሉት ርዕዮተ ዓለም የባሕሎች ውኅድ፣ የዘውግ መደጋገፍ ያለበት 3000 ዓመታት የዘለቀ የዘመናዊነት ፕሮጀክት ብሔራዊ “አሰባሳቢ ታሪክ” ውጤት እንደሆነ ነው። ነገር ግን ይህ ፕሮጀክት በ1983፣ በእርስ በርስ ጦርነት እንዲቋረጥ ተደርጓል። የአሁኑ አገዛዝ “ማኅበረሰቦችን” በዘውግ ማንነታቸው በመበየን፣ እና በማዋቀር የኢትዮጵያ አገረ መንግሥትን ቅርፅ ካለፈው ታሪኳ እንዲህ የተቆራረጠ አስተዳደር እንዲሆን አድርጎታል።

ብዙዎች የጋራ ኢትዮጵያዊ ማንነት ስለመሸርሸሩ ይህንን አገዛዝ ይወቅሳሉ። ለዚህ መንግሥታዊ ዘውግ ተኮርነት ምላሽ በሚመስል መልኩ የቴዲ አፍሮ ዘፈኖች ላላፈው የኢትዮጵያ ሥልጣኔ፣ ታሪክ፣ እና ባሕል ዋጋ ሰጥተዋል። ብሔራዊ ጀግኖችን በማሞገስ እንደ ፈርቀዳጆች ቆጥሯቸዋል። በዚህ አልበሙ በ19ኛው ክፍለዘመን ከእንግሊዞች የተዋጉትን ዳግማዊ ቴዎድሮስ አሞግሷል። በአራተኛው አልበሙ ደግሞ በ1888 አድዋ ላይ ጣሊያኖችን ድል ላደረጉት ለዳግማዊ ምኒልክ ተመሳሳይ ነገር አድርጎ ነበር።

መንግሥት አሰባሳቢ ኢትዮጵያዊ ማንነት የለም ብሎ በካደበት በዚህ የዘውግ ፌዴራሊዝም ግዜ ስለ የጋራ ኢትዮጵያዊ ማንነት እና ኩራት በአፅንዖት መናገሩ ለመንግሥት አስጊ ነው።

ለመንግሥት ደጋፊዎች እና ለዘውግ ብሔርተኞች ቴዲ መሰሪ ሆኖ ነው የሚታያቸው። ላለፉት የኢትዮጵያ መሪዎች ያለው ክብር እና “ለፍቅር እና አንድነት” ያለው ቁርጠኝነት የቀድሞዋን ኢትዮጵያ የተሸነፈ ርዕዮተ ዓለም የሚወክል ነው።

ያም ሆነ ይህ፣ ለወጣቱ ትውልድ ያለው መግነጢሳዊ መስብህነት እና የአገሩ ሰዎች ላይ ያለው ሰፊ ተፅዕኖ ቀጥሏል። የተሸነፈ ርዕዮተ ዓለም ነው የሚወክለው ቢባልም፣ የቴዲ አልበሞች ሽያጭ ሪከርድ እያስመዘገቡ ነው። በዚያ ላይ አድናቂዎቹ በዘፈኖቹ ከጭቆና እረፍት እየወሰዱ እንደሆነ በሚገልጹ መልዕክቶቻቸው ኢንተርኔቱን እያጨናነቁት ነው።

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.