የ‘ወንድም ጋሼ’ አፍሪካዋ ቤቲ ላይ የባሕል እሴት ጥያቄ ተቀሰቀሰባት

የ‘ወንድም ጋሼ’ አፍሪካ (Big Brother Africa)  የተሰኘው የእውነተኛ የኤቴሌቪዥን ትዕይንት የዘንድሮው (እ.ኤ.አ. 2013) ኢትዮጵያዊት ተሳታፊዋ መምህርት ቤቲ (Betty) ከሴራሊዮናዊው ተሳታፊ ቦልት (Bolt) ጋር ወሲብ ፈፅማለች የሚለው ዜና ከወጣ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በሁለት ወገን የጦፈ የባሕል እና የሞራል ጥያቄዎችን በማንሳት እየተሟጎቱ ነው፡፡

ዮሐንስ ሞላ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ቤቲ አደረገች የተባለው ነገር ፍፁም ከኢትዮጵያዊ የማይጠበቅ ነውር እንደሆነ ለመግለጽ ሞክሯል፡-

‹‹… በመደበኛውና ልማዳዊው አካሄድ ሰውዬው/ሴትዮዋ ላይ፥ ልብ ፈቅዶ፥… ተጣጥቦና ተጣጥኖ፣ ቤት ተገብቶ… ከቤትም መኝታ ቤት ተገብቶ…ከመኝታ ቤትም ደበቅ የሚለውና፥ ግድግዳው ላይ ሽንቁር የሌለው (ቢቻል ከጎረቤት ጋር በቀጥታ የማይዋሰነው) ተመርጦ… ከዚያም በኋላ መብራት ተጠፍቶ…. በጨለማ የሚፈፀም ነው። በዚያም ጨለማውን ሁሉ ፈልቅቆ ገላልጦ፣ ያስረሳልና በነፃነትና በፍፁም መፈቃቀድ ሲፈፀም፥ ‘ወሲብ ብርሃን’ ነው እንላለን። ብርሃንነቱም ከእርካታና ከወንድና ሴት አካላዊ ስምረት ባሻገር የመንፈስ ቅርርብንና ዝምድናን ይፈጥራል። ወዳጆቹ ከተዘጋጁና ለፍሬ ካለው ደግሞ ራሳቸውን ይተኩበታል።

…በእኔ መረዳት ወሲብና ሴሰኝነት በጣም ይለያያሉ። ጤናማ ወሲብ ውስጥ ሴሰኝነት የለም፤ ሴሰኝነት ውስጥ ግን ወሲብ አለ። ወሲብ ማንነትንም ሆነ ማህበረሰብን በማይረብሽ፣ ጤናማና ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ የሚፈፀምና፣ በውጤቱም ከቅፅበታዊ የስሜት እርካታ ባለፈ የሰው ልጅን የመሰለ ክቡር ኗሪ የሚተካበት የተዋበ መንገድ ነው። ሰው የሚፈበረክበት፣ ሰው የሚሰራበት፣ አብራክ የሚከፈልበት፣ ራስ የሚተካበት… አስደናቂ መንገድ ስለሆነ እንዲሁ የግብር ይውጣ አይደረግም። እንደዚያ ሲደረግ መሴሰን ይባላል። […]

ለእኔ ቤቲ ምጣድ እንደጣደች ሴት ነበረች። ለያውም ለአገር ስም የሚጠበቅ እንጀራ በዓለም ፊት እንድታበስል የተወከለችና እያንዳንዷ እንቅስቃሴዋ ሁሉ በinfrarad ካሜራ እየተቀረፀ፣ “ኢትዮጵያ” የሚል ስም እየተለጠፈበት የሚገመገም። ግን አልገባትም። ወይም አልቻለችበትም። ወይም ጀብድ መስሏታል። እኔን ግን አሸማቀቀችኝ።…››

 

ጁኒየር ዲ የተባለ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ ከዮሐንስ ሞላ ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ አንፀባርቋል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ኢትዮጵያ የጨዋዎቹም የመረኖቹም አገር ነች፡፡

ቤቲ (ምንጭ:- ቢግ ብራዘር አፍሪካ ድረገጽ)

ቤቲ (ምንጭ:- ቢግ ብራዘር አፍሪካ ድረገጽ)

‹‹…በቢግ ብራዘር አምፕሊፋይድ 2013 ላይ የተሳተፈችው ቤቲ ወሲብ ፈፀመች ተብሎ ወግ አጥባቂዎች ዋይ ዋይ እያሉ ነው:: ለማስታወስ ያህል [ኢትዮጵያ]

* ወግ አጥባቂ ሃይማኖተኞች እንዲሁም መንፈሳውያን ያሉባት ሃገር ብቻ ሳይሆን እነቺቺንያ እና መስቀል ፍላወር ሰፊውን ሕዝብ በወሲብ ንግድ የሚያገለግሉ ጉብሎች ያሉባት ሃገር ናት፣

* ቆሎ እየቆረጠሙ የሚጸልዩ የዋልድባ መነኮሳት ብቻ ሳይሆኑ ዶላር እየቆረጠሙ ራቁት ዳንስ በመሸታ ቤትም ሆነ በግለሰብ አፓርትመንት የሚደንሱ ቆነጃጅት ያሉባት ሃገር ናት፣

[…]

እንግዲህ ሁሉም የዚህች አገር ሰዎች ናቸው:: እየመረጡ መኩራት እየመረጡ ማፈር አይቻልም:: ቤቲ የሰንበት ተማሪዎችን ወክላ አይደለም የሄደችው:: እራሷን ሆና ነው:: መብላት መጠጣት ጤነኛ ሰው ሁሉ የሚያደርገውን ነገር ማድረግ ነው የሾዉ ዓላማ:: በቤቲ አፈርን የምትሉ ሁሉ ምክንያታችሁን ጠይቁ:: ሕፀፅ ይበዛዋል ብይናችሁ፡፡››

 

ኃይሉ ጌታቸው የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩሉ ቤቲ ኢትዮጵያን ትወክላለች በሚል ‹‹የወግ አጥባቂዎች›› ክርክር ልጅቷ ላይ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስ ያለውን ስጋት ገልጽዋል፡-

‹‹ቤቲ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለድች ግለሰብ ነች እንጂ ኢትዮጵያ ቤቲ ውስጥ አልተፀነሰችም!
ከዓመታት በፊት በምድረ ፒያዛ፣ ጥንዶቹ ወጣቶች እንደቀልድ ራሳቸውን በወሲብ ውስጥ በሞባይል ቀድተው እንደሰደድ እሳት የተዛመተው ምስል አሳዛኝ ታሪክ አስከትሎ አልፏል። ልጅቷ በአካባቢው ማኅበረሰብ የደረሰባትን ጫና መሸከም አቅቷት እራሷን አጠፋች። አሁንም big brother afirca ላይ እየተሳተፈች ባለችው በቤቲ ላይ እየትሰነዘረ ያለው የሞት ገመድ በእሷ ዙሪያ ብዙዎችን ሊጠልፍ ይችላል።የኢትዮጵያ ወግ አጥባቂ ነኝ ባዮች፣ መለኮስ እንጂ ማጥፋቱን የሚያውቁበት አልመስልህ ብሎኛል፡፡ ይሄ ቁልል ፊደል ሊገመድ እንደሚችል መረዳት መቻል አለብን።

ዓለም ስትታመስ እና የብዙዎች ነፍስ እንደ ገለባ ብን ብሎ የረገፈው፣ እየረገፈም ያለው በነዚህ ወግ አጥባቂ ነን ባዮች እሳቤ ምክንያት ነው። ምክንያቱም መሠረታቸው ሰፊው ደንቆሮ ሕዝብ እና ረዥም ምላሳቸው ነው!››

 

ፀዲ ለማ የተባለች ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ በሰጠችው አስተያየት ደግሞ በግለሰቦች ጉዳይ ላይ የምሁራዊ ውይይት ብስለት እንደሚያንሰን ጠቁማለች፡-

‹‹የቤቲ ስብራት (The Betty fiasco): አሁንም የግለሰቦች ግላዊ ምርጫ ብሔራዊ ውክልና ይኑረው አይኑረው በሚለው ጉዳይ ላይ ምሁራዊ ሥነ-ምግባራችን ጎዶሎነቱ ነው የታየው፡፡  ቤቲ፣ ራሷን ነው የሆነችው፤ በዚያ ላይ ቤቲ ማለት የራሳቸውን ምርጫ በየዕለቱ ሰከንዶች የሚፈቅዱ ሌሎች ሚሊዮንን ሴቶች ማለት ነች፡፡ ጥያቄው ‹ለምን ቤቲ የወል እሴቶቻችንን እንድትበይንልን ፈለግን?› የሚለው ነው፡፡ ለምንስ ድርጊቷን (እኔም ራሴን በማልበይንበት፣ ነገር ግን የግሏ ነው ብዬ የምተወውን ድርጊቷን) እንደ አንዲት ወጣት፣ በትዕይንቱ ላይ ለመሳተፍ እንደፈቀደች አፍላ ሴት – ሰው የመሆንን ድንበር እስከ የመጨረሻው የምንዱባን ጥግ ድረስ ለመግፋት እንደሞከረች ሴት ለምን አንወስዳትም?››

መማር ዘላለም በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ ስም የሚታወቅ ሰው ግን ቤቲ ኢትዮጵያን አልወከለችም በሚለው አይስማማም፡፡ ነገር ግን ተመልሳ ወደአገር ቤት ስትመጣ ሊደርስባት ስለሚችለው መገለል ከወዲሁ መስጋቱን ገልጧል፡፡ እስካሁን እየተሰነዘረባት ያለው ትችትም ተገቢ እንዳልሆነ ተከራክሯል፡-

‹‹…ቤቲ የፈጸመችው ድርጊት ምቾት አልሰጠኝም፣ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ወክላ ሄደችም/አልሄደችም፤ ማንኛውም ሰው በየሄደበት ሀገር በተዘዋዋሪም ቢሆን የሀገሩ አምባሳደር ነው ብየ ስለማምን፡፡ ከዚህም ባሻገር በትልቅ የቲቪ ሚዲያ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሳ ኢንተርቪው ስታደርግ ነበር፣ ጋዜጠኞችም፣ ተመልካቾቹም ሲጠሯት ‹Betty from Ethiopia› እያሉ መሆኑም ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ የምር ለመናገር ተሸማቅቂያለሁ፤ እንዲያውም አሁን እማ ብታዩኝ ተሸማቅቄ… ተሸማቅቄ አውራ ጣት አክያለሁ… አብዛኛው ሰውም እንደኔ ደብሮታል፤ አዎ ቤቲ ይህን ማድረግ አልነበረባትም፡፡ ይህን ነገር የማድረግ መብቷን ግን ፈፅሞ ልጋፋት አልችልም፤ መብቷን አከብራለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይቺ ልጅ በጣም አሳዘነችኝ ክፉኛ በሐበሻ አፍ ውስጥ ገብታለች፤ ወደሀገሯ በተመለሰች ጊዜ የሚገጥማት ወሬና ግልምጫ ሳስበው የእውነት አዘንኩላት፤ በወሬ አመድ ማድረግ የሚችል ጀግና ሕዝብ እኮ ነው ያለኝ፡፡ እኔ ግን ይቺ ልጅ ከዚህ ቀደም ጓደኛዬ፣ አብሮ አደጌ፣ የሥራ ባለደረባዬ ሁና ቢሆን ኖሮ ከዚህ ቀደም እሰጣት ከነበረው ፍቅር ቅንጣት ታክል አልቀንስባትም፡፡ አሁንም ቢሆን መንገድ ላይ ድንገት ባገኛት ዘወር ብዬ ላላያት ቃል እገባለሁ… ባአካባቢዬም አየሃት ቤቲን? ያቸውልህ እያት… የሚለኝ ሰው ካለም ጆሮውን እቆነጥጠዋለሁ፡፡ ሰዎች፣ እኛ እሷን እንዲህ የመተቸት መብት እንዳለን ሁሉ እሷም እንዲህ የማድረግ መብት እንዳላት አትዘንጉ፣ … ሁሉም ሙጫ ሙጫ አምባገንን ነው እኮ በየቤቱ፤ በስመ ወግ ባሕላችን ተነካብን ብለን የማንንም መብት መጋፋት አንችልም፡፡ እናንተ እንዲህ ከሆናችሁ ከጋሽ መንግሥቴ በምን ትሻላችሁ? መንግሥቴ እኮ በምንም በምንም ሰበብ ነው መብቴን እየተጋፋው ያለው፡፡››

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማጣቀስ ቤቲ ላይ እየደረሰባት ያለው ውግዘት ከተመሳሳይ ድርጊት ነጻ በሆኑ ሰዎች እንዳልሆነ የተከራከረችው ደግሞ ሕይወት ወንድማገኝ የተባለች ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነች፡-

‹‹በጣም ከምወዳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ በዝሙት ምክንያት በድንጋይ እንድትወገር የተፈረደባትን ሴት ኢየሱስ ‹‹ከናንተ ኃጢያት የሌለበት እሱ የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውርባት›› ብሎ አድኗታል፡፡ እውነትም፣ ማንም እጁን አላነሳባትም፡፡

እኔ ሌሎቻችንም ይህንን ሐሳብ በሌሎች ላይ ከመፍረዳችን በፊት እንድናስብበት እመኛለሁ፡፡››

 

ሌሎች ደግሞ ችግሩ ያለው ከቤቲም ከተቺዎችም ሳይሆን ከስርዓቶች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የፀረ-ሉል ሴራ የተሰኘ ጦማር የ‹ወንድም ጋሼ አፍሪካ› ፕሮግራም ራሱ ሰብኣዊነትን ለማጥፋት የተዘጋጀ ነው ሲል፤ ሲስ ሒው የተባለ ሰው ደግሞ በአገር ውስት ባሕላዊ እሴቶቻችንን የሚያበረታታ ነገር እንደሌለ የታዘበውን አስፍሯል፡-

‹‹…ትርኢቱ እጅግ ጋጠወጥ ሲሆን በተለያየ ዘመን ባቀረባቸው ትርኢቶች የተለያዩ ለፕሮግራሙ በከፍተኛ ወጪ ማስተዋወቅያ እንደሚነገርለት ሳይሆን ክብረ ነክ የሆኑ ድርጊቶች፣ እራቁት መታየት፣ ስካር፣ ወንዶችና ሴቶች እራቁታቸውን ፍል ውሃ ውስጥ ተዘፍዝፎ መታየትና አብሮ መታጠብ ወዘተ. የተለመዱት ናቸው፡፡ ይህ እንዲሁ ሁኖ የአገራችን ኤፍ ኤም ሬድዮ ፕሮግራሞች በሚከፈላቸው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ስለ ፕሮግራሙ ጥሩ ማውራት እንጀራቸው ነው፡፡ አክብረን አንብበን ወዳጆቻችንም እንዲያነቡ የምንመክራቸው የህትመት ውጤቶችም ስለዚህ ክብረ ቢስ ፕሮግራም በተከበረው ወረቀቶቻቸው ላይ ውደሳ ያጎርፉለታል፡፡ ከዚህ በፊት ባለማወቅ ከሆነ እንዲህ የተደረገው ለቀጣይ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ደረጃ እንዲታገድ አበርትተው እንዲታገሉ እንጠይቃለን፣ እንዲህ ካልሆነ ግን በአንባቢው ዘንድ ክብርን እንዳይጠብቁ እንንገራቸው፡፡ ክብረ ቢስ ድርጊቶች በሚከበሩ ሚድያዎች መገኘት የለባቸውምና፡፡ ሁሉም የየራሱ ቦታ አለው፡፡ የዚህ ትርኢት አደጋም አለክብሩና አለቦታው መቀመጥ መቻሉ ነው፡፡

እንዲህ የመሰሉ የእውነተኛ ክስተቶች ትርኢት ወይም ሪያሊቲ ሾው ግማሽ  ክ/ዘመን በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ሲሆን ከሁሉ አነጋጋሪው ይህ ዓለም አቀፋዊው ወንድም ጋሼ  የተሰኘው ሪያሊቲ ሾው ነው፡፡ ሪያሊቲ ሾው ለፕሮፖጋንዳ የተመቸ ነው፣ ማሸነፍ ከፈለጉ የትርኢቱ መሪ ፍልስፍናዎችን ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋልና ተወዳዳሪዎቹ ለዚህ ሲሉ የማይሆኑት ነገር የለም፡፡…››

 

‹‹…ሚዲያዎቻችንን፣ ዩንቨርስቲዎቻችንን፣ ትምህርት ቤቶቻችንን፣ የትምህርት ሥርዓታችንን፣ እና የትምህርት መሣሪያዎቻችንን ተመልከቱ፤ የትኞቹ ናቸው ባሕላዊ እሴቶቻችንን እና ቅርሶቻችንን እንድናከብር የሚያስተምሩን? ወጣቱ ትውልድ ቤቲ እና ሃኒ የሚያደርጉትን ነገር ያደንቃል፡፡ ፖለቲከኞቻችን ሳይቀሩ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን እና የሆሊዉድ ፊልምን እየተከታተሉ ስለ ማኅበራዊ እሴቶች እና መብቶች ከማይጠይቁዋቸውጋ ነው የሚወግኑት፡፡…››

ሌሎች ደግሞ ቤቲ ወደቀጣዩ ዙር እንዳታልፍ ካሁኑ የፌስቡክ ገጽ ከፍተው ቅስቀሳውን ጀምረዋል፡፡

2 አስተያየቶች

 • amsalu gebrekidan argaw

  ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

  Big Brother Africa Reality Show እና ቤተልሔም አበራ
  ትናንት ቅዳሜ 2-10-2005 ዓ.ም ፌስ ቡክ ላይ ተጥጄ በነበርኩበት ሰዓት አንዱ ጓደኛዬ አንድ ከቪዲዮ (ከትዕይንተ ኩነት) የተወሰደ ፎቶ (ምስለ ኩነት) ለጥፎ እዚያው ላይም አስተያየቱን ጽፎ ሌሎቹም ይጽፉ ዘንድ ጋበዘ፡፡ ነገር ግን ይህ ጓደኛዬ ስለጉዳዩ ትክክለኛ መረጃ አልነበረውም ነበርና በአስተያዬቱ ላይ ለሕዝብ በቀጥታ በሚታይ መድረክ ላይ ከወገብ በታች እርቃን መታየት ከኢትዮጵያዊ ጨዋነት የወጣና መወገዝ እንዳለበት በ3 መስመር ጽፎ ነበር፡፡ እኔም ፎቶውን(ምስለ ኩነቱን) ዓይቼ በነገሩ ተደናግጬና ግራ ተጋብቼ ከስር (is she a healthy woman? I am sure she is a escapee from the Amanuel mental institution) ጤነኛ ነች ግን? እርግጠኛ ነኝ ከአማኑኤል የእዕምሮ ሕሙማን የሕክምና ማዕከል ያመለጠች ነች ብዬ ጻፍኩ፡፡ ለካ ነገሩ እንዲህ ቀላል አልነበረም ኖሯል ማታ ላይ በአንዱ የF.M ሬዲዮ (ነጋሪተ ወግ) የመዝናኛ ፕሮግራም(ምስናድ) ሳዳምጥ የተፈጸመው ጉዳይ ከዚህ የከፋ የሰማውን ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሁሉ ሁለት ጆሮዎቹን ጭው የሚያደርግ የልጅቱን ቤተሰቦችና ዘመዶች በድቅድቅ ጨለማ እንደሚሄድ ሰው የጉምብስ የሚያስኬድ ያየንበትንና የሰማንበትን ዓይንና ጆሮ ለማመን የሚያዳግት ጉድ መፈጸሙን ተረዳሁ፡፡ወይ ወደላይ ብሎኝ አላረፍኩት የማቅለሽለሽ ስሜት ለሰዓታት ተናነቀኝ ከተኛሁ በኋላም እንደ መጥፎ ቅዥት ደጋግሞ ያባትተኝ ነበር፡፡ የማውቃቸው ሴቶች ሁሉ እሷን መስለው ታዩኝ፡፡ እኔን ይሄን ያህል የጎዳኝ ቤተሰቦቿን በተለይም ወላጆቿንማ እንዴት ያደርጋቸው ይሆን ብዬ ለእነሱ በጣም አዘንኩ፡፡
  ነገሩ እንዲህ ነው በDSTV. የሚታይ 8ኛ ዙር Big Brother Africa የሚባል reality show (የእውነት ትዕይንት) የመዝናኛ ፕሮግራም (ምስናድ) ላይ ኢትዮጵያን ወክለው ከሄዱት ሁለት ወንድና ሴት ኢትዮጵያዊን ቤተልሔም አበራ በመባል የምትጠራዋ ዜጋ ያልተጠበቀ አይደለም ጨርሶ ያልታሰበ በባለፈው የውድድር ጊዜ ተሳትፋ የነበረችውን ኢትዮጵያዊት ምክርና ማስጠንቀቂያ ወደ ጎን በመተውና ይሄንንም በማድረጓ ከኢትዮጵያዊያን ለደርስባት የሚችለውን መገለልና ጫና በመናቅና ከምንም ባለመቁጠር በብዙኃን መገናኛ ለሕዝብ በቀጥታ በሚተላለፉ በእንደዚህ ዓይነት ዝግጅቶች ላይ ተደርጎ የማይታወቅ እጅግ አስደንጋጭ ነውረኛና ጸያፍ ድርጊት (ወሲብ) ከሴራሌዮናዊ ወንድ ጋር ፈጽማ ስለነበርና ይሄንንም መላው ዓለም እየተቀባበለ ጠላት እንደተለመደው ሲደሰትና ኢትዮጵያዊያንንም ለማሸማቀቅ ለማዋረድ ለማሳፈር የሀገራችንን ገጽታ ለማጉደፍ ሲጠቀምበት ወዳጅ ደግሞ አንገቱን ሲደፋበት እና ይህ ጸያፍና ነውረኛ ድርጊት በፍጹም ጨዋና ቁጥብ ባሕል ያለውን፣ ሃይማኖተኛ የሆነውን የኢትዮጵያን ሕዝብ አይወክልም በማለት ሲከራከሩበት ዐቢይ የብዙኃን መገናኛ ርእስ ሆነ፡፡
  እኔ በግሌ ከልጅቱ ተግባር ባልተናነሰ ያበገነኝና ያቆሰለኝ ማታ ሳደምጠው የነበረው የመዝናኛ ምስናድ አዘጋጆች ጉዳዩን ሚዛናዊ ያደረጉ መስሏቸው ይናገሩት የነበረው ነገር ነበር፡፡ ነገር ግን እንኳንና ልጅቱ የፈጸመችው ድርጊት በቀጥታ ሊተላለፍ እንደሚችል አስቀድማ እያወቀች፣ ተገዳ ወይም ተደፍራ ሳይሆን ወዳና ፈቅዳ እንዳደረገችው ታውቆና ይህን በማድረጓ በሀገርና በሕዝብ ላይ ያደረሰችውን ሀፍረት ውርደት መሸማቀቅና ሥብራት ያህል ሚዛን የሚያነሣ ምክንያት ይኖራት ይመስል ስልክ እየደወሉ ይሄንን ድርጊቷን በጥብቅ ያወግዙ ለነበሩ አድማጮች እንዲህ ከማለታችን በፊት የእሷንም ቃል ማድመጥ ይኖርብናል የምትለው ነገር ይኖራታል ብለን እንጠብቃለን መቼም ያለምንም ምክንያት ይሄንን ነገር ታደርጋለች ብለን አናስብም ወዘተ ማለታቸውና ሕዝብ በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰማውን ስሜት ሲገልጹ የምስናዱ አዘጋጆች ከሆኑት አንዱ ድርጊቱን ያወገዙ የተቃወሙትንና መብቷ ነው ያሉትን ሰዎች የነሲብ ግምት ሲገልጽ እኩል በእኩል እንደሆነ አድርጎ ሲያወራ ሌላኛው አብሮት ያለው ደግሞ ድርጊቱን ያወገዙት እንደሚበዙ ይናገራል፡፡ እኔ ግን እርግጠኛ ነኝ እነኝህ አዘጋጆች ለሚዛናዊነት ባላቸው የተሳሳተ መረዳት ነገሩን ሚዛናዊ ያደረጉ መስሏቸው እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በዚህ አስከፊና ጸያፍ ጉዳይ ላይ የሕዝብ ስሜት እኩል በእኩል ይሆናል ብሎ መገመት የማይታሰብ ነው፡፡ የተባለው እርግጥ ሆኖ እኩል በእኩል ሆኖ ከተገኘ ግን ለዚህ ላለንበት የሞራል (የቅስም) ሥብራትና ልሽቀት የሥነምግባር ውድቀት “ሞተን ተቀብረናል በድናችን ነው የሚንቀሳቀሰው” የሚለው ቃል ራሱ የሚገልጸው አይመስለኝም ነገር ግን ይህ ይለመሆኑን በቀላል ትዝብት መረዳትና መገመት እንደሚቻለው የላይኛው አባባል ሐሰት እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በዙሪያችን ያሉ ሰዎችን ለክብሩና ለነውር ግድ የለሽ የሆነውንና የማይገደውን ፀረ ግብረገብ የሆነውን ካልሆነው ጋር ብናነፃጽር የምናገኘው ውጤት እውነታውን ያስረዳናል፡፡ በመሆኑም ይሄንን ስሕተት በተደጋጋሚ ሲፈጽሙት አስተውላለሁና ሊገምቱት ከሚችሉት በላይ ሕዝቡን ተስፋ የመቁረጥና በቀላሉ እጅ የመስጠት ችግር ውስጥ እንዲገባ የማድረግ አሉታዊ ውጤት አለውና እጅግ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ አይበለውና እኩል በእኩል ደረጃ የሚገለጽበት ደረጃ ወይም ዘመን የምንደርስ ከሆነም እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ሊስተናገዱ የሚገባቸው አሁን በቀረበበት ሁኔታ ሳይሆን ዳታው (ቁጥሩ) እንዲህ በእንዲህ መሆኑ የቱን ያህል አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆናችንንና ልንሠራበት እንደሚገባ በሚያስገነዝብ በሚቀሰቅስ መልኩ እንጂ ጭራሽ በሚያደፋፍርና በሚያሳስት መልኩ መሆን አይኖርበትም፡፡ ይህንን ስል አፋቸውን ሞልተው መብቷ ነው የሚሉ ሰዎች ጨርሶ አይኖሩም እያልኩ እንዳልሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ የመብት ምንነትን የማያውቁ ግለሰቦችና እነሱም በተመሳሳይ ቦታና ጊዜ ቢሆኑ ይህች ልጅ ያደረገችውን ከዚያም የከፋ ድርጊት የማድረግ ፍላጎትና አቋም ያላቸው የወደቀ ሰብእና የሞራል(የቅስም) ስብራት፣ የሥነ ምግባርና የግብረገብ ብልሽት ያለባቸው ግለሰቦች ይሄንን ሊያደርጉ እንደሚችሉ የሚጠራጠር ይኖራል ብዬ አልገምትም፡፡
  ሲጀመር አንድ ግለሰብ ሁሉንም ነገር የማድረግ መብትና ነፃነት ፈጽሞ የለውም፡፡ ደናቁርትና ማሰብ የተሳናቸው ግለሰቦች ሁሉ መብቴ ነው፣ መብቷ ነው፣ መብታቸው ነው ለማለት የትም መቸም ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ እንኳን አያደርጉም፡፡ አንድ ግለሰብ ያሰበውን ነገር የማድረግ መብትና ነፃነት የሚኖረው ያ ሊያደርገው ያሰበው ነገር የሰው ልጆችና ማኅበራዊ ፍጥረቶች እንደመሆናችን የጋራ ጥቅማችንን የማይጎዳ የማይፃረር የማይቃረን እስከሆነ ጊዜ ብቻና ብቻ ነው የየትኛውም የሕግ መጽሐፍና የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎች ከዚህ ጽንሰ ሐሳብ የወጣ አይደለም፡፡ ይህች ልጅ እንኳንና በተለቀቁት ማስታወቂያዎች ሀገርን ወክላ እንደተሳተፈች ተገልጾ ቀርቶ ባይገለጽም እንኳን እኛ ኢትዮጵያዊያን (ሐበሾች) እንደ ሕዝብና እንደ ሀገር የጋራ ጥቅሞች አሉን፡፡ ከእነሱም ውስጥ ሀገር፣ ባሕል፣ ሃይማኖት፣ ክብር፣ ማንነት፣ ታሪክ፣ ቅርስ፣ ወዘተ. እያልን ልንዘረዝራቸው እንችላለን፡፡ የምንሠራው ሥራ እነኝህን ነገሮች የሚጎዳ የሚጻረር ከሆነ ያንን ነገር ማድረግ መብታችን ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡ ከዚህ የአስተሳሰብ ሚዛን ወይም ደረጃ ወጥተን ማሰብና መተግበር ከሞከርን ከሰውነት ደረጃ ወርደን ወደ እንስሳነት ከእንስሳነትም ከብዙዎቹ በወረደ በዘቀጠ ባነሰ የአስተሳሰብ ደረጃ ላይ እንዳለን ማወቅ መረዳት ይኖርብናል፡፡
  እዚህ ላይ ተያይዞ የሚጠቀስ ነገር አለ ‹‹ምን ነው? እሷ በግልጽ ስላደረገችው ነው እንዴ? ሁሉም ተደብቆ የሚፈጽመው ተግባር አይደለም እንዴ?›› የሚባል፡፡ የተደበቀውማ ተደብቋል የሚያውቀው የለም ይሄኔ እኮ ስንት የምናከብራቸው የምንኮራባቸው የምናደንቃቸው ሰዎቻችን ከዚህ በከፋ ነውር ላይ ውለው ይሆናል፡፡ነገር ግን ያደረጉት ተደብቀው በመሆኑ ሀፍረቱና ውርደቱ ከእነሱ አልፎ እንደ ሀገር ለኢትዮጵያ እንደ ሕዝብ ለሐበሻ አልሆነብንም፡፡ በድብቅ የምናደርገው አይደለም እንዴ! ተብሎ በግልጽ እናድርገው ማለት ይሄ ከበድ ያለ የአዕምሮ ጤና መቃወስ ችግር ነው፡፡ ሰው ደካማ ፍጡር እንደመሆኑና ጥንካሬውም አንዱ ከሌላው የማይመጣጠን እንደመሆኑ ከስሕተት(ከኃጢአት) የጸዳ ሊሆን አይችልም፡፡ስሕተት የምንለው ነገር በራሱ ክብደትና ቅለቱ የሚለያይ ቢሆንም፡፡
  እናም ድክመት ከሰው ልጅ የማይጠፋ መሆኑ ቢታወቅም ለጋራ ሰላም፣ ለጥምረታችን ደኅንነት፣ ለማኅበራዊነታችን ጤንነት ሲባል እስከዛሬ ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ የምግባር ድክመትና ብልሹነት(አመል) ያለብን ሰዎች መታረም ካልቻልን ነውራችንን በስውር በድብቅ ብናደርገው ኃላፊነት ከመወጣት ጋር የሚነጻጸር ተግባር እንደፈጸምን ይቆጠራል ጓዳ የማይችለው ጉድ የለምና፡፡ ከዚህ ወተን ካሰብንና ከሠራን ግን እንደ ጤነኛ ሰው በጤነኛ ዓይን መታየትና መስተናገድ አይኖርብንም፡፡
  Big brother Africa reality show ተወዳዳሪዎቹ እንዲያደርጉት ከሚፈልገውና ከሚያደርስባቸው ጫና ባጠቃላይ ከዝግጅቱ ቅርጽ አንጻር ስናይ ተወዳዳሪዎቹ ሀገርን ወክለው እንዲሳተፉ ማስታወቅና ማድረግም ሳይኖርበት ይሄንን ማድረጉ የልጅቱ የሥነ ምግባር ብልሹነት እንዳለ ሆኖ ይህ ድርጊት የኢትዮጵያዊያንን ስም ለማጥፋት ለመስበር የሕዝቡን ሞራል (ንቃተ ወኔ) ለማኮላሸት ሆን ተብሎ እንደተደረገ መገንዘብ ይቻላል፡፡
  ሲጀመር ሀገርን በግለሰብ የመወከል ተግባር እጅግ እጅግ ከባድ ነገር ነው፡፡ምክንያቱም ተወካዮቹ የሚያደርጉት እያንዳንዱ ነገር ሁሉ የሀገርንና የሕዝቧን ባሕል ማንነትና አስተሳሰብ እንደገለጸ ይቆጠራልና፡፡ እንዲያዝ የተፈለገው ግንዛቤ ይሄ ሆኖ ውክልናው ከተደረገም ተዎካዮቹ እንዲያደርጉ የሚጠበቀውና የሚበረታታው የሚያንጸውም አዎንታዊ የሆኑ ነገሮችን እንጅ ጭራሽ የማያደርጉት የማያስቡት የነበረውን ሁሉ እንዲያደርጉ መገፋፋትና ማበረታታት አይኖርባቸውም፡፡ ይህ የእውነታን ትዕይንት ቅርጽ የሚለውጥ ድርጊት ነውና፡፡ ነገር ግን የዚህ ‹‹የመዝናኛ›› ዝግጅት አዘጋጆች ይሄንን እንደሚያደርጉ ቀደም ሲል ተሳትፈው የነበሩ ተወዳዳሪዎች አረጋግጠዋል፡፡
  Reallity show (የእውነታ ትዕይንት) ተብሎ ሀገር በምግባረ ብልሹዎች እንድትወከል የማድረጉ ጽንሰ ሐሳብ በራሱ የሎጅክ (የአመክንዮ) ችግር አለበት፡፡ ምክንያቱም የሥነምግባር ብልሽት እንከን ያለባቸው ግለሰቦች ብዙውን ጨዋ የኅብረተሰብ ክፍል ሊወክሉ አይችሉምና፡፡ ይሄንን ባለመረዳት ወይም ለመረዳት ሳይፈለግ ቀርቶ ይህ ከተደረገ ግን ከጀርባው ሌላ ስውር ዓላማ እንዳለው መረዳት ይቻላል፡፡ የሆነውም ይሄው ነው በዚህች ልጅ አማካኝነት ከእንግዲህ ከማንም ቀድመን የሀገራችን ኢትዮጵያ በብዙኃን መገነናኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጸመ ርኩሰት በሚል ስሟ የውርደት መዝገብ ላይ ሠፍሯል፡፡ የሚገርመኝ ይህ የreality show (የእውነታ ትዕይንት) ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሠራ የተፈቀደለት እንደሆነ ነው የምናየው ነገር ግን ነገሩ ከዚህ የተለየ እንደማይሆን የሚጠቁም መሆኑ ነው፡፡ ይህ የሀገርንና የሕዝብን ቅስም የሠበረ የሀፍረትና የመሸማቀቅ ዱላውን በእያንዳንችን ላይ ያሳረፈ ጸያፍ ድርጊት ከተፈጸመና የወዳጅና ጠላት መሳለቂያ ከሆንን በኋላም የመንግሥት የብዙኃን መገናኛዎች አሁንም የBig Brother Africaን ማስታወቂያ እያስተላለፉ በመሆኑ፡፡ ይህ ሕዝብ ጨዋና ታጋሽ ሆኖ ነው እንጂ ይህ ድርጊት የተፈጸመው በሌሎች ሀገሮች ላይ ቢሆን ኖሮ የDSTV. በሀገሪቱ ያለውን ተወካይና የBig Brother ተወካይ መሥሪያ ቤቶች ላይ አደጋ በደረሰ ነበር፡፡
  በእርግጥ የከበረ ታሪክና ማንነት እንዳለው ከዓለማዊ እስከ መንፈሳዊ ያሉ ጥንታዊ መረጃዎች የሚያረጋግጡት እውነታ በመሆኑ የዚህች ልጅና የመሰሎቿ ድርጊት የተመሰከረለትን ሕዝብና ሀገር የሚወክል አይሆንም፡፡ የምትወክለው ራሷንና እንዳለመታደል የድንቁርናም ነገር ሆኖ ሥልጣኔና ዘመናዊነትን እጅግ በተሳሳተ መንገድ የተረዱትን ከአንድ በመቶ በታች ያሉትን “ኢትዮጵያዊያንን” ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከ90 ሚሊዮን (ከእላፋት) ሕዝብ በላይ እንዳላት ይገመታል፡፡ ከዚህ ቁጥር በጠቀስኩት የጨነገፈ አስተሳሰብ የተመረዙት 15 በመቶ ሕዝብ በሚኖርበት በከተሞች ያሉ ጥቂት ዜጎች ብቻ ናቸው፡፡ በመሆኑም ይህች ልጅና ድርጊቷ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚወክልበት ምንም ሆኔታ የለም፡፡ ይህ ሁሉ እየታወቀ ኢትዮጵያን በዚህ ርኩስ ግብር ስሟ እንዲጠራና ለመጀመሪያ ጊዜም እንደመደረጉ በውርደት መዝገብ እንዲሰፍር መደረጉ ታስቦበት ለክፋት አይደለም የሚለኝ ካለ የዋህ መሆኑን ልነግረው እወዳለሁ፡፡
  በመጨረሻ ሌሎች እኅት ወንድሞቻችን በቀጣይ ጊዜያት በተመሳሳይ መድረኮች ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይፈጽሙ ለማስገንዘቢያነት ይረዳ ዘንድ ይህች ልጅ ይህንን ድርጊት በመፈጸሟ በግል ሕይወቷ ምን ሊገጥማት ይችላል የሚለውን እንመልከትና እናብቃ፡፡ ማኅበረሰባችን እንደምናውቀው ጥብቅና ክብርን የማዕዘን ድንጋዩ ያደረገ፡፡
  ሃይማኖታዊ አሻራ የሰፈረበትና የታነጸ ባሕል ያለው ኅብረተሰብ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ይህች ልጅ ከባድ የሆነ የመገለል አደጋ ያጋጥማታል፡፡ የመገለሉ አደጋ ከእርሷም አልፎ ቤተሰቦቿ ላይም ሊደርስ ይችላል፡፡ ይህንን ጸያፍ ድርጊት የሀገርና የሕዝብ ወኪልነቷን ለገንዘብ ስትል ለሕዝብ በቀጥታ በሚታይ መድረክ ፊት አድርጋለችና እስከ ተከፈላት ጊዜ ድረስ Blue film (የወሲብ ምትርኢት) እስከ መሥራት ድረስ አላደርግም የምትለው ነገር እንደማይኖር ሊያስገምታትና የሰውነት ክብር ሊያሰጣት ይችላል፡፡ ወላጆቿንም አሳዳጊ የበደላት በማሰኘት ለዘለፋ ትዳረጋለች፡፡ ምናልባትም አንዳንዴ ያልዘሩት ይበቅላል ይባላልና ይሄኔ ወላጆቿ በመልካም ሥነ ምግባር ለማሳደግ የደከሙ ሆነው ይሆናል፡፡ነገር ግን እንዲህ የነበሩ ቢሆኑም እንኳ ያለ ሥራቸው ለዘለፋ ዳረገቻቸው ማለት ነው ፡፡
  ልጅቱ መምህርት እንደሆነች ይነገራል፡፡ የሚገርመውም ይሄው ነው መማር ሥነምግባርንም ለማነጽ ይጠቅማል ተብሎ ይታሰባልና አሁን አሁን በየዩኒቨርስቲው የምናየው ነገር ይሄንን አባባል የሚሽር እየሆነ የመጣ ቢሆንምና ይህች እኅታችንንም መማሯ አርቃ ለማሰብና ለማገናዘብ የጠቀማት ባይሆንም፡፡ እናም የገለጸችውና ያሳየችው የሥነምግባር ግድፈትና ብልሽት ለተማሪዎች አርአያ ሊያደርጋት ስለማይችል ወይም በመጥፎ አርአያነት ስለሚያስቆጥራትና ከዚህም አንፃር የምታስተምርበት ት/ቤት በእሷ ምክንያት ተማሪ ሊያሳጣው ስለሚችል እንደሚያሰናብታት ወይም የሥራ ዋስትናዋን ሊያሳጣት ይችላል፡፡
  ልጅቱ እንደተመኘችው አሸናፊ ሆና 300 ሺህ ዶላር ሽልማት ማሸነፍ ብትችል እንኳ እንዳሰበችው የአስጎብኝ ድርጅት ብትከፍት በዜጎች የሚወደድ፣ ተቀባይነት ያለው፣ እንደአስገብኝ ድርጅት ኃላፊነት የሚሸከም እንደማይሆን የመጠርጠር የመገለል በአጠቃላይ ሥራዋን ልትሠራ የምትችልበትን ከባቢ ያለማግኘት ችግር ይገጥማታል ምክንያቱም ገንዘቡ የተገኘው ክብሯን ሸጣ፣ ማንነቷን አዋርዳ፣ ሰብእናዋን አርክሳ፣ ሕዝቧን አሳፍራ፣ ቤተሰብ ዘመዶቿን አሸማቃ፣ ታሪኳን እስከወዲያኛው አጠልሽታ፣ ጤናዋን ለአደጋ ዳርጋ፣ ኅሊናዋን አቆሽሻ፣ ሃይማኖቷን አስተሃቅራ በመሆኑ፡፡ ስለሆነም ይህ ገንዘብ የተባረከ አይሆንም እንደአመጣጡ ሁሉ የጥፋት ይሆናል እንጅ፡፡ በሉ እግንዲህ ከዚህ ይሰውረን እንጂ ሌላ ምን ይባላል፡፡
  እኅቴ ቀላሉን ያድርግልሽ ለንስሐ ያብቃሽ
  በሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
  amsalugkidan@gmail.com

  • ትዙ

   በጣም በጣም አወዛጋቢ ነው ምን ማለት እንደምችል ራሱ አልገባኝም፡፡ በምንም ስሌት ብናሰላው እንኳን ከውድድሩ ጋር ሊሄድ ማይችል ሥራ እንደሠራች ነው የሚሰማኝ፡፡
   ለማንኛውም እግዚአብሔር መጽናናትን እንዲሰጣት እመኛለሁ፡፡

ንግግሩን ይቀላቀሉ

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

 • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
 • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.