በሁለቱ የኢትዮጵያ ክልሎች፣ ኦሮምያ እና ሶማሊ መካከል የነበረው የዘውግ ቡድኖች ውጥረት ወደ አመፃዊ ግጭት በማደጉ ቢያንስ ደርዘን ያህሎችን ለሞት፣ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናትን ደግሞ ለስደት ዳርጓል።
የሟቾች ቁጥርን በተመለከተ በማኅበራዊ ሚድያዎች የሚወጡት ቁጥሮች እንደ ሪፖርት አድራጊዎቹ ማንነት የተለያየ ነው። ለመንግሥት የሚወግኑ ጋዜጠኞች የሟቾቹን ቁጥር ደርዘን አካባቢ ሲወስኑት፣ ዳያስፖራ ተቀማጭ ሚድያ ግን በጣም ብዙ ያደርገዋል። ሁለቱም ግን የተናፈቀሉት ሰዎች በሺሕዎች የሚቆጠሩ እንደሆኑ ተናግረዋል።
ከሪፈረንደሙ ከ14 ዓመታት በኋላ ግጨቱ አገርሽቷል
በኢትዮጵያ ክልሎች ትልቁን ድንበር የሚጋሩት ኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች ናቸው። ሁለቱም ክልሎች በኢትዮጵያ፣ በቅደም ተከተል፣ 1ኛ እና 2ኛ ጂኦግራፊያዊ ስፋት አላቸው።
በዚህ ክልላዊ ድንበር አካባቢ ለረዥም ግዜ የቆየ ውጥረት በተለይ በኦሮሞዎች እና በሶማሌዎች መካከል ነበር።
በ1987 የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የሶማሊ ክልል የደቡብ ምሥራቅ የኦሮሚያ ክልልን ጥሶ እየገባ ነው በማለት ወቀሳ አቅርቦ ነበር። ኦነግ ከዚያ በኋላ በአገዛዙ አሸባሪ ተብሎ ተፈርጇል። በሰኔ 1992፣ ኦነግ በኦሮሞዎች እና ሶማሊዎች መካከል በተደረገ የትጥቅ ግጭት 70 ሰዎች መገደላቸውን ሪፖርት አድርጎ ነበር።
በታኅሣሥ 1996 በውኃ እና ደረቅ መሬት ሀብት ሳቢያ በተቀሰቀሰ አመፅ የቀላቀለበት ግጭት ደግሞ ከክልሎቹ ድንበር አካባቢ 19ሺሕ ያህል ሰዎች ተፈናቅለዋል።
በ1996 የኢትዮጵያ መንግሥት ሪፈረንደም አዘጋጅቶ ግጭቶቹን ለመፍታት ሞክሯል። በውጤቱም 80 በመቶ የሚሆኑት አጨቃጫቂ ወረዳዎች በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሥር እንዲካለሉ ተወስኗል።
ታኅሣሥ 1998፣ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔውን ተግባራዊ ሊያደርግ ሲሞክር አመፁ ተባብሶ አገረሸ። ሪሊፍ ዌብ የተባለ ዓለማቀፍ ድርጅት እንዳወጠው መረጃ ከሆነ፣ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በወቅቱ ከአካባቢው ተፈናቅለዋል። በዚህ ሳቢያ የኢትዮጵያ መንግሥት በሕዝበ ውሳኔው ወደ ኦሮሚያ እንዲካለሉ የተወሰኑትን አካባቢዎች የማካለሉን ሥራ ለሌላ ግዜ ለማስተላለፍ ተገዷል። ከዚያ በኋላ ነገሮች በአንፃራዊ ሁኔታ ተቀዛቅዘው ነበር።
የአሁኑ ግጭት እንዴት ተቀሰቀሰ?
በሚያዝያ ወር 1999፣ በደቡባዊ የሞያሌ ከተማ ድንበር አካባቢ በተቀሰቀሰ ግጭት ከኦሮሞዎቹም፣ ከሶማሌዎችም ሰዎች መገደላቸው ሪፖርት ተደርጓል። በዚህ ወቅትም የግጭቱ መንስዔ የውኃ እና የደረቅ መሬት ሀብት እጥረት ነው።
መንግሥት በዚያው ወር፣ በ1996ቱ ሕዝበ ውሳኔ በተስማሙበት መሠረት ድንበሮቹን አሠምራለሁ ብሎ አሳወቀ።
ይህም ለመጨረሻ ግዜ በ1996 የታየውን ግጭት እንደገና ቀስቅሶት ከፍ ያለ ደረጃ አደረሰው። የኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልል ባለሥልጣናት እንዲሁም አራማጆችም የታጣቂ ኃይሎች ሲቪሎች ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውን ወንጅለዋል።
ምንም እንኳን ብዙ የኦሮሞ ማኅበራዊ ሚድያ አራማጆች የአሁኑን ግጭት በዘውግ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማመን ባይፈልጉም፣ ግጭት ውስጥ የገቡት ዜጎች ግን በዘውግ በጣም ተከፋፍለዋል።
ባለፈው ሳምንት፣ ቢያንስ 32 በኦሮሚያ እና ሶማሊ ክልሎች ሲገደሉ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኦሮሞዎች ደግሞ ከሶማሊያ ክልል ጥቃት ፍራቻ እየሸሹ ነው።
የፌዴራል መንግሥቱ ስለዚህ ምን አደረገ?
የመንግሥት ሚድያ እንደገለጸው፣ የፌዴራል መንግሥቱ የዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ ጣልቃ ገብቷል። ነገር ግን ብዙዎች የመንግሥትን ሚና በጥርጣሬ ነው የተመለከቱት። እንዲያውም አንዳንዶች፣ መንግሥት የዘውግ ቡድኖችን በማጋጨት በአገሪቱ እያደገ የመጣውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የደገሰው ውጥረት ነው እስከማለት ደርሰዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን በተለይም በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የበለጠ ፖለቲካዊ መብቶችን እና ማኅበራዊ ፍትሕ ለመጠየቅ እንዲሁም የመሬት መቀራመትም ለማስቆም አምፀዋል። የመንግሥት ምላሽ ደግሞ ፈጣንና ክፉ ነበር፣ በዚህም ብዙዎች ታስረዋል፣ ተገድለውማል።
ኢትዮጵያ፣ ብቸኛው ኢሕአዴግ ሥልጣኑን የተቆጣጠረባት አሀዳዊ የፖለቲካ ፓርቲ አገረ መንግሥት ሆናለች።
ምንም እንኳን ኢሕአዴግ የአራት የዘውግ ቡድኖች – ማለትም ብአዴን፣ ኦሕዴድ፣ ደኢሕዴን እና ሕወሓት ጥምረት ቢሆንም ሕወሓት የስለላ፣ ፖሊስ እና መከላከያ መዋቅሮችን ላለፉት ሩብ ምዕተ ዓመታት በመቆጣጠር ፍፁማዊ ሥልጣን ጨብጧል።
የኢሕአዴግ አባል ፓርቲዎች ከዘጠኙ የፌዴሬሽኑ ክልሎች አራቱን ይገዛሉ። ቀሪዎቹ አምስቱ የኢሕአዴግ አባል ባይሆኑም የኢሕአዴግ አጋር በሆኑ የየክልሉ የዘውግ ፓርቲዎች ይመራሉ።
ብዙ ተቺዎች የሕወሓት አባላት በመከላከያ ውስጥ ትልቅ ሥልጣን ስላላቸው የእነዚህ አምስት ክልሎች የእጅ አዙር መሪ ሕወሓት ነው ይላሉ።
ብዙ ኦሮሞዎች ሕወሓት ይህንን የኦሮሞ እና ሶማሊ ክልል ግጭት ፈብርኮታል እያሉ በስሜት ይወቅሳሉ። የዚህ ግጭት መንስዔ በሶማሊ ክልል የሰፈረው የመከላከያ ሠራዊት ነው ብለው ያምናሉ።
ሌሎች ኢትዮጵያውያን ደግሞ ማኅበረሰቦችን በዘውግ ማንነታቸው በመበየን የከፋፈላቸው በማለት የዘውግ ፌዴራሊዝሙን ወቅሰዋል።
በግጭቱ ማዕከል ያሉትን ወገኖች ተዋወቋቸው
የዘንድሮው ግጭት ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ረገድ በኦሮሞና ሶማሊ ፖለቲከኞች መካከል አለመግባባት ፈጥሯል።
ብዙ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና አራማጆች አመፁን ‘ልዩ ፖሊስ’ ከሚባለው ወታደራዊው ሚሊሽያ ጋር አያይዘውታል። ‘ልዩ ፖሊስ’ አሁን በተቋቋመለት ከሶማሊ ክልሉ ታጣቂዎችን የማስወገድ ኃላፊነት አልፏል ብለው ያምናሉ።
የኦሮሞ ተቃዋሚ አራማጆች ነገሩን ለጥጠውት፣ ‘ልዩ ፖሊስ’ የትግራይ ሠራዊት ድጋፍ ያለው ወራሪ አድርገውታል። በነሐሴ 2009 በተደረገው አድማ ወቅት ከተነሱ ጥያቄዎች አንዱ ‘ልዩ ፖሊስ’ መስማማት ካልተደረሰባቸው የኦሮሚያ ወረዳዎች ይውጣ የሚል ነበር።
በርግጥ፣ ‘ልዩ ፖሊስ’ በነውጠኝነት ሲወነጀል ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ቀደም ሲል የወጣ የሰብኣዊ መብቶች ታዛቢው ድርጅት ሪፖርቶች በተደጋጋሚ ‘ልዩ ፖሊስ’ ሶማሊ ክልል ውስጥ የፈፀማቸውን ጅምላ ግድያ፣ የቡድን አስገድዶ መድፈር፣ እና የማዋከብ ወንጀሎችን ጠቅሷል።
‘ልዩ ፖሊስ’ የተመሠረተው አንዳንድ የሶማሌ ክልል ተወላጅ ኦጋዴን ጎሳ ሰዎች መሣሪያ ታጥቀው በመንግሥት ላይ ባመፁበት ወቅት፣ በ2000 ነበር። የኦጋዴን ጎሳ በሶማሌ ክልል ረዥም ግዜ የቆየ ምሬት በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ቋጥሯል። ብዛታቸውም ከኢትዮጵያውያን ሶማሌዎች ከ80 እስከ 90 በመቶ ይሆናሉ።
ምንም እንኳ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ባላቸው ግጭት ምክንያት ቢሸፈንም፣ በሶማሊዎች መካከልም ጠንካራ ውስጣዊ ግጭት አለ። አክራሪ እና አማካይ መንገድ የሚመርጡ የኦጋዴን ጎሳ አባላት አሉ። አንዳንዶች ሰፋ ያለ ራስን የማስተዳደር ነጻነት ሲጠይቁ፣ ሌሎች መገንጠልን ይመርጣሉ። እንዲያም ሆኖ፣ ራሳቸውን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ያስተሳሰሩ አሉ። ከነዚህ ውስጥ ነው ታጣቂ የኦጋዴን ጎሳ አባላትን ለመደምሰስ የኢትዮጵያ መንግሥት የክልሉን ‘ልዩ ፖሊስ’ን የመሠረተው።
አብዲ ኢሌ በመባል በተለይ የሚታወቁት አብዲ ሞሐመድ ኡመር የተባሉት የሶማሊ ክልል ፕሬዚደንት ከመሆናቸው በፊት የ‘ልዩ ፖሊስ’ የመጀመሪያ መሪ ነበሩ። ፕሬዚደንት አብዲ የኢትዮጵያ መንግሥት ታጣቂዎቹን ለመደምሰስ ባደረገው ጥረት ላይ አግዘውታል።
ግጭቱ እንዳዲስ ካገረሸ ወዲህ፣ የአብዲ የሕዝብ ግንኙነት ሠራተኞች የገዢው ፓርቲ የኦሮሞ ባለሥልጣናት ላይ የወቀሳ ናዳ እያወረዱባቸው ነበር። በፌስቡክ ገጻቸው የአብዲ ኢሌ የሕዝብ ግንኙነት ወኪሎች የኦሕዴድ ባለሥልጣናትን ውጭ ተቀማጭ ከሆኑ የኦሮሞ አራማጆች ጋር ግንኙነት አላቸው በማለት ከሰዋቸዋል።
የኦሕዴድ ባለሥልጣናትም በበኩላቸው፣ ወቀሳውን አጣጥለው በወንጀለኞቹ ላይ የፌዴራል መንግሥቱ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል።
ግጭቱ በቅርብ ግዜ ይቆማል?
ሳምንታት ከዘለቀ መወነጃጀል በኋላ የኦሮሚያ ፕሬዚደንት ለማ መገርሳ እና የሶማሊ ፕሬዚደንት አብዲ ኢሌ መስከረም 7፣ 2010 በዋና ከተማይቱ አዲስ አበባ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር። ሁለቱም ስለግጭቱ በጥቅሉ ነበር የተናገሩት።
ሁለቱም በአካባቢው መረጋጋት ያስፈልጋል ቢሉም በግጭቱ መንስዔ የተስማሙ አይመስልም። ለምሳሌ፣ አቶ ለማ ሥማቸውን ያልጠቀሷቸውን አካላት ሲወቅሱ፣ አቶ አብዲ ግን የኦሕዴድ ባለሥልጣናትን ለግጭቱ መባባስ ወቅሰዋል።
ችግሩ፣ ብዙ ኢትዮጵያውያን፣ በተለይም ደግሞ ኦሮሞ አራማጆች በትግራይ ልኂቃን የሚመራው አገዛዝ በግጭቱ በንቃት ተሳትፏል ብለው ያምናሉ። ለዚህ እንደማስረጃ የሚጠቅሱት፣ ከሶማሊ ፕሬዚደንት ጋር ቅርብ ቁርኝት ያላቸውንና በሶማሊ ክልል ልዩ ፍላጎት ያላቸውን የፀጥታ ኃይሎች ነው።
ይሁን እንጂ ሁለቱም ፕሬዚደንቶች የተፈናቀሉትን ዜጎች ወደነበሩበት በአስቸኳይ በመመለሱ ጉዳይ ላይ የተስማሙ ይመስላል።
ነገር ግን ግጭቱ በመሬት ላይም ይሁን ግራ መጋባት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ የሚከሰቱ አመፆች ምንጭ ላይ የታቀደ ማደናገር በተሠራበት ማኅበራዊ ሚድያ ላይ ይቀጥላል።