በትልቁ የኢትዮጵያ ሐይቅ ላይ አደጋ ይዞ የመጣው አረም

የአባይ ወንዝ መውጫ፣ ፎቶ ሪቻርድ ሞርቴል (ፎቶ Flickr. CC BY 2.0)

ከ2004 ጀምሮ እንቦጭ የተባለ ተስፋፊ አረም በብዙ ሺ ሔክታር የሚቆጠር የጣናን ውኃማ አካል፣ በዙሪያው ያለውን ረግረጋማ ስፍራ፣  እንዲሁም የከብቶች ማሰማሪያ አካባቢ ወርሮታል።

በአካባቢው የተፈጥሮ ጥበቃ እና እንክብካቤ ላይ የሚሠራው የጀርመን መንግሥታዊ ያልሆነ የተፈጥሮ እና ባዮዳይቨርስቲ ጠባቂው ኅብረት (ናቡ) ጣና ሐይቅ፣ በውኃው፣ በዙሪያው ባለው የከብቶች ማሰማሪያ እና ሌሎችም ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ 2 ሚሊዮን የሚገመቱ ሰዎች ጥገኛ እንደሆኑ ተናግሯል። እንቦጭ የተባለው አረም በተለይ የተስፋፋው፣ በሐይቁ ምዕራባዊው ክፍል ሲሆን ይህ አካባቢ ብዙ የአሳ አጥማጆች፣ ገበሬዎች እና ከብቶቻቸውን የሚያሰማሩ ሰዎች ይሰማሩበታል።

832 ስኵዌር ማይል የሚሰፋው ጣና ሐይቅ የኢኮሎጂ፣ ባሕላዊ፣ እና ታሪካዊ ሀብት የታቀፈ ሐይቅ ነው። ጣና በትልቅነቱ ሁለተኛ የሆነው የኢትዮጵያ ክልል – አማራ ክልላዊ አስተዳደር – ውስጥ ይገኛል።

የጣና ሐይቅ ዝርያቸው ሊጠፋ የተቃረቡት ባለ ጥቁር ኮከን መንቁራም ወፎችን እና ሌሎችም ተሰዳጅ አእዋፋትን አቅፎ ይዟል።

ጣና ሐይቅ፣ የሱዳን ዋና ከተማ፣ ካርቱም ላይ ከነጭ አባይ ጋር ለመቀላቀል ወደምዕራብ የሚፈሰው የጥቁር አባይ ምንጭም መሆኑም ይታወቃል።

የዓለማችን ትልቁ ወንዝ ናይል ሁለት ታላላቅ መጋቢዎች ጥቁር አባይ እና ነጭ አባይ ናቸው። የናይል ወንዝ ወደ ሰሜናዊዋ ግብጽ ሲጓዝ በመንገዱ ላይ ብዙ ትናንሽ ወንዞች ይመግቡታል። ነገር ግን 80% የሚሆነውን ድርሻ የሚይዘው ጥቁር አባይ ነው። የጣና ሐይቅን ጠቃሚነት ሲገልጽ ታዋቂው ተጓዥ እና ጂኦፊዚስት ፓስኳል ስካቱሮ “የግብጽ ሀብት ከጣና ሐይቅ በስጦታ የተገኘ ነው” ብሏል

የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍጥነት በማደጉ በዚያው ልክ ፍላጎቱ እየጨመረ በመጣበት በዚህ ወቅት፣ ሐይቁ ላይ ያጠላበት አደጋ የተፈጥሮ ሀብቶች ላይ ያንዣበበው ችግር ልዩ ትዕምርት ሆኗል።

በ2004 ለመጀመሪያ ግዜ ሲታይ፣ እንቦጭ የተባለው አረም፣ 77 ስኵዌር ማይል ያክል የውኃውን ብዙም ጥልቅ ያልሆነ ምዕራባዊ ክፍል እና ጥግ ጥጉን ነበር ያዳረሰው። ከዚያ ወዲህ፣ ተንሳፋፊው አረም በጣም ብዙ የሐይቁን አካል አዳርሷል። በውጤቱም፣ የአካባቢው ነዋሪዎች ለመንግሥት ብዙኃን መገናኛ  እንደተናገሩት በምዕራባዊው አውራጃ ደንቢያ አካባቢ ያለው የሐይቁ ውኃ መጠን በገፍ ቀንሷል።

ለመንግሥት ብዙኃን መገናኛ የተናገሩት ባለሙያዎች እንዳብራሩት ከሆነ፣ 155 ስኵዌር ማይል የሸፈነው እንቦጭ ሙሉ ለሙሉ የተስፋፋው ከ2004 ወዲህ ነው። ነገር ግን ባለፈው ዓመት የታየው ድርቅ መስፋፋቱን ትንሽ አዘግይቶታል።

የዚህ ተስፋፊ እንግዳ አረም መንስዔ ሰዎች በሐይቁ ዙሪያ የሚሠሩት ሥራ ነው። አንድ በሁለት ምሁራን የተዘጋጀ የጥናት ወረቀት እንደሚያስረዳው የዚህ አደገኛ አረም መስፋፋት መንስዔ በዙሪያው ካሉ የከተማ እና የግብርና ተረፈ ምርቶች ወደሐይቁ የሚገባው ምግብ አዘል ፈሳሽ ውኃ እና እንደ ሐዋሳ ሐይቅ እና ዝዋይ ሐይቅ ያሉትን ሌሎች የኢትዮጵያ ሐይቆችን ጭምር አደጋ ላይ የጣለው የኢንዱስትሪ ተረፈ ምርት ነው።

ከ2007 ጀምሮ፣ ዩኔስኮ ጣና ሐይቅ ለያዘው ልዩ የኢኮሎጂ እና ባዮስፌር ሀብት፣ ናቡ የተባለው ድርጅት በውስጡ ያሉትን ሀብቶች ለመጠበቅ እንዲያስችለው ባደረገው  ጥረት፣ የዓለም ቅርስነት ዕውቅና ሰጥቶታል። ዩኔስኮ የሐይቁ ደሴቶች ላይ ለሚገኙት ታሪካዊ፣ ባሕላዊ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስትያን ትልቅ ዋጋ የሚሰጣቸው ሀይማኖታዊ ቅርሶችም ዕውቅና ሰጥቷል።

ሐይቁ የታሪካዊ ገዳማት እና ቤተ ክርስቲያኖች መገኛ ነው። ለነዚህ ቅርሶች መጠበቅ የደሴቶቹ ከነዋሪዎች የተነጠለ መሆን አስተዋፅዖ አድርጓል። ነገር ግን አስደንጋጩ የእምቦጭ ወረራ ሐይቁ ላይ ያሉትን እና የገቢ ምንጫቸው ሐይቁ ላይ የተመረኮዘውን ሰዎች እንዲሁም የጣና ሀይቅ የተፈጥሮ ሀብቶች ሁሉ አደጋ ላይ ናቸው።

1 አስተያየት

  • አለም

    እንዳልክ፣ ትልቅ ሥራ እየሠራህ ነውና በርታ። ዛሬ ይህን የአማርኛ ገጽ ሳይ እጅግ ደስ አለኝ። እንግዲህ ጥሩ ጥሩ ጸሐፊዎችን አሰባስብ። ህዝቡን ማስተማር እንጂ ውሸት መዝራት ውጤቱ ጉዳት ብቻ ነው። ህዝቡን ነጻ የሚያወጣ እውነቱንና ታሪኩን ማወቁ ነው።

ንግግሩን ይቀላቀሉ

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.