ለተቃዋሚዎች፣ የዓለም ጤና ድርጅት እጩ ሊቀ መንበሩ የኢትዮጵያን ጨቋኝ መንግሥት ነው የሚወክሉት

የጤና ጥበቃ ምኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ እኤአ በ2012ቱ የለንደኑ የቤተሰብ ምጣኔ ጉባዔ ላይ ንግግር ሲያደርጉ።

አባል አገራት ከመጨረሻዎቹ እጩዎች አንዳቸውን ለመምረጥ ድምፅ ከሚሰጡበት ጥቂት ሳምንታት አስቀድመው፣ አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ተሰናባቿን የዓለም ጤና ድርጅት ጠቅላይ ሊቀመንበር ማርጋሬት ቻን ፉንግ ፉ-ቹን ለመተካት የታጩት ቴድሮስ አድሃኖም ላይ የመረረ ዘመቻ እያደረጉ ነው።

የቀድሞው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ እና የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ቴድሮስ፣ ከፓካስታናዊዋ ሳንያ ኒሽታር እና እንግሊዛዊው ዴቪድ ናባሮ ጋር ለጠቅላይ ሊቀመንበርነቱ  ባለፈው ጥር ወር ከብዙ ተፎካካሪዎች መካከል ተሳክቶላቸው የወጡ ሦስት ዕጩዎች አንዱ ናቸው።

ጠቀም ያለ የገንዘብ ድጋፍ የተደረገለት ቅስቀሳ እያደረጉ ያሉት ዶ/ር ቴድሮስ፣ በውድድሩ ጥሩ ዕድል ያላቸው ተደርገው ይቆጠራሉ። ቀድሞ በአፍሪካ ኅብረት ተቀባይነት ያገኘው እጩነታቸው ባለፈው ሳምንት ደግሞ የእንግሊዝ የዓለምዐቀፍ ልማት የቀድሞው ዋና ጸሐፊ አንድሩ ሚሼልን ተቀባይነት አግኝተዋል።

ነገር ግን ከገዛ  ዜጎቻቸው ቁጣን የቀላቀለ ተቃውሞ ተጋርጦባቸዋል።

በአገራቸው ጉዳይ በአገሪቱ መንግሥት እንደተገለሉ የሚሰማቸው ኢትዮጵያውያን የሕዝቡን ሳይሆን የአምባገነኖች ስብስብ የሆነውን የኢትዮጵያ አመራር ነው የሚወክሉት የሚል መከራከሪያ በማቅረብ አቶ ቴድሮስ እንዳይመረጡ በኢንተርኔት ላይ ዘመቻ ጠንካራ ዘመቻ እያካሔዱ ነው።

ከሐዘን የከበደ ስላቅ። በ#ኢትዮጵያ የሰው ዘር ላይ ለተፈፀመ ወንጀል ተጠያቂ የሆኑት ሰው ለ#ዓለም የጤና ድርጅት ጠቅላይ ሊቀ መንበርነት እየተወዳደሩ ነው። #ቴድሮስ_እንዳይመረጡ

በኢትዮጵያ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር እያሉ፣ ዶ/ር ቴድሮስ አድርሰዋቸዋል ያሏቸውን ጥፋቶች እና የገንዘብ አላግባብ አጠቃቀም የሚያሳዩ  ጥናታዊ ፊልሞችን ያዘጋጁ ከመሆኑም ባሻገር፣ እንዳይመረጡ የሚቃወሙ ሰዎችን ፊርማ የማሰባሰቢያ ገጽም ከፍተዋል።

ቴድሮስ አድሃኖም በኢትዮጵያ የተፈፀመው የዓለም ገንዘብ ድጎማ ብክነት ውስጥ ተሳትፎ አድርገዋል።  #ቴድሮስ_እንዳይመረጡ

በጉዳዩ ላይ የሚደረጉ ንግግሮችን ለማቀናጀት እንዲመቻቸው ትዊተር ላይ #NoTedros4WHO (ቴድሮስ እንዳይመረጡ) በሚል ሀሽታግ ዘመቻ አድርገዋል። ሰዎች በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ የነበረውን ድርሻ እንዲረዱ ለማድረግ፣ ዶ/ር ቴድሮስን በብቃት ማነስ፣ በውሸት መረጃ አቅራቢነት እና ስኬቱ በሐሰት የተጋነነ መሆኑን የሚያጋልጡ ዝርዝር ጥናት አጋርተዋል።

ከሁለቱ ተፎካካሪዎች ጋር የዶ/ር ቴድሮስ ምስል ኤክስ ተደርጎበት በኢንተርኔት ሲዘዋወር የነበረ ምስል። ከትዊተር ላይ የተገኘ። @DahlaKib

ምንም እንኳን የተቃውሞ ዘመቻዎቹ የማሸነፍ ዕድላቸውን ይቀንሰዋል ተብሎ ቢሰጋም፣ የመንግሥት ሰዎች እጩነታቸውን በመደገፍ ዘመቻ እያካሔዱ ነው። ዶ/ር ቴድሮስ የገጠማቸውን ተቃውሞ ከአገራዊ ስሜት ማጣት፣ ክፋት እና ምቀኝነት ጋር በማመሳሰል ለማንኳሰስ ሞክረዋል።

እኤአ ከሚያዝያ 2014 ጀምሮ በኢትዮጵያ የተካሔደው ሕዝባዊ ተቃውሞ የኃይል ምላሽ የሰጠውን መንግሥት ፈትኖታል። የሰብኣዊ መብቶች ታዛቢ ቢያንስ 800 ሰዎች መሞታቸው እና ብዙ ሺሕ ተቃዋሚዎች እና በመቶዎች የሚቆጠሩ እምቢተኞች መታሰርና፣ መሰቃየታቸውን ገልጿል። እኤአ ከጥቅምት 2016 ጀምሮ በዓለም እጅግ ከባድ ከሆኑት የዕቀባ መመሪያዎች መካከል አንዱን በአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ደንግገዋል።

የዘውግ ፖለቲካ ሚና

አንዳንድ ተቺዎቻቸው የዶ/ር ቴድሮስን መታጨት የሚቃወሙት የብቃት ማነስ አለባቸው በሚል ነው። ነገር ግን አብዛኛውን የመረረ ተቃውሞ የሚመራው የዘውግ ፖለቲካ ነው።

ዶ/ር ቴድሮስ ፒኤችዲያቸውን የያዙት በማኅበረሰብ ጤና ከኖቲንግሃም ዩኒቨርስቲ ነው። የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በባዮሎጂ ከአስመራ ዩንቨርስቲ፣ ከዚያም ከለንደን ዩንቨርስቲ የማስትሬት ድግሪያቸውን በኢሚዩኖሎጂ ኦቭ ኢንፌክሺየስ ዲዚዝስ ሠርተዋል።

ምንም ያህል በትምህርት ብቁ ቢሆኑ እንኳ፣ ሰዎች የዶ/ር ቴድሮስን ሥም ሲሰሙ የሚመጣባቸው የኢትዮጵያ መንግሥት የገደላቸውን ሰዎች፣ የታሰሩ በሺሕ የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች እና የተሰቃዩ እምቢ ባዮች ምስል ጋር ተያይዞ ነው።

ረዥም የሥልጣን ጉዟቸው የጀመረው እኤአ በ1991 ፒኤችዲአቸውን እንደያዙ የትግራይ ጤና ቢሮ መሪ ተደርገው ሲሾሙ ነው። በሁለት ዓመት ውስጥ፣ ራሳቸውም የትግራይ ተወላጅ የሆኑት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር አድርገው ዶ/ር ቴድሮስን ሾሟቸው። እኤአ በ2012 አቶ መለስ ሲሞቱ ዶ/ር ቴድሮስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ተደርገው ተሾሙ።

ትግራይ በብሔር ከተከፋፈሉት ዘጠኝ የፌዴራሉ ክልሎች አንዷ ነች።

ባለፉት 26 ዓመታት፣ የትግራይ ልኂቃን ወታደራዊ፣ የስለላ እና የኢኮኖሚ ጉዳዮችን በበላይነት መቆጣጠር በመቻላቸው የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ማዕከላዊ ስፍራ ወስደዋል። ምንም እንኳ የሕዝብ ብዛታቸው ከ6% ባይበልጥም፣ የትግራይ ልኂቃን ሁሉንም የመከላከያ፣ ስለላ እና ሌሎች ጠቃሚ ተቋማት የኃላፊነት ቦታዎች ተቆጣጥረዋል። ይህ ተደምረው የኢትዮጵያን ሕዝብ 65% በሚሸፍኑት የኦሮሞ እና የአማራ ልኂቃን ዘንድ የሁልጊዜ የቅሬታ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። የኢትዮጵያ መንግሥት አምባገነናዊ ዘዴዎችን የሚጠቀም ሲሆን፣ የፖለቲካ ምኅዳሩም ዝግ ነው፤ ነገር ግን እንደ አሜሪካ እና እንግሊዝ ያሉ ትላልቅ አገራትን ድጋፍ ይቀበላል።

በዓለምዐቀፍ መድረክ የአገርውስጥ አለመግባባት

የዶ/ር ቴድሮስ እጩነት የገጠመው ጠንካራ ተቃውሞ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በዓለምዐቀፍ አደባባይ መንፀባረቅ መጀመሩን ይጠቁማል። ይህ በአንድ በኩል፣ የዓለምዐቀፉ መድረክ በአገር ውስጥ የተነፈገው የፖለቲካ ምኅዳር ምትክ መሆኑንም ያሳያል።

የኢትዮጵያ መንግሥት የአገር ውስጥ ተቋማትን እና የግንኙነት መሠረተ ልማቶችን በመቆጣጠሩ ምክንያት፣ ምንም እንኳን ጥረቶቻቸው ወጥ እና የተቀናበሩ ባይሆንም፣ ዳያስፖራዎች ይህንን አጋጣሚ አገር ውስጥ የሚፈፀሙ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች በትዊተር ዘመቻ ለማጋለጥ ተጠቅመውበታል።

ዛሬ አፕሪል 28፣ በአውሮፓ ሰዐት 18:00 እና በዋሽንግተን ዲሲ 12:00 ከሰዐት በኋላ እንዲሁም በእንግሊዝ ሰዐት  17:00 ሰዐት ላይ የትዊተር ዘመቻ ይኖራል። እነዚህን ሀሽታጎች ተጠቀሙ #ቴድሮስ_እንዳይመረጥ እና

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.