የ2013ቱን የአፍሪካ አገራት ዋንጫ ኢትዮጵያውያን በተለያየ ባንዲራ ውልብልቢት እያደመቁት ነው

በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን ከባለፈው ዓመት የ2012 የአፍሪካ አገራት ዋንጫ ሻምፒዮን ጋር በኔልስፕሩት፣ ደቡብአፍሪካ ያደረገውን ከባድ ግጥሚያ በድምቀት እያከበሩ ነው፡፡

ከኢትዮጵያውያኑ ውብ አጨዋወት እና ከረዥም ጊዜ መጥፋት በኋላ በአፍሪካ ዋንጫ ከታየው ድንቅ የተጫዋቾች ችሎታ ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከኳሱ ጎንለጎን ማዕከላዊ የውይይት አጀንዳ ለመሆን በቅቶ ነበር፡፡ በስታዲየሙ ጨዋታውን ለመመልከት የገቡት ኢትዮጵያውያን የተለያዩ ጽሑፎችን እና ባንዲራዎችን ሲያውለበልቡ ታይተዋል፡፡

Ethiopian Muslims continue protesting the Ethiopian Government while supporting Ethiopian Team in South Africa at The Cup of African Nations 2013.

የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የኢትየጵያ ቡድንን በደቡብ አፍሪካው የ2013 የአፍሪካ አገራት ዋንጫ ላይ እየደገፉ የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ያላቸውን ተቃውሞ አስደምጠዋል፡፡ ፎቶው የተገኘው ከአዎሊያ ትምህርት ቤት ደጋፊዎች የፌስቡክ ገጽ ነው፡፡

Addis Rumble የተሰኘ ድረገጽ ደግሞ በበኩሉ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የተሳተፈችባቸውን የአፍሪካ አገራት ዋንጫ ጫወታዎችን ለትዝታ ያክል ለጥፏቸዋል፡፡

‹የኢትዮጵያ መመለስ› የሚል ርዕስ በሰጡት በዚህ ጽሑፋቸው የሚከተለውን አስፍረዋል፡-

በዚህ ሳምንት፣ ኢትዮጵያ በድንገቴ ድል ጎረቤታችን ሱዳንን በደርሶ መልስ ጫወታ 5 ለ 5 በመርታት የመጨረሻውን ዙር አልፋ ለ2013 የአፍሪካ ዋንጫ ለመሳተፍ በቅታለች፡፡ ለዋንጫ ጨዋታው ማለፏ ከተረጋገጠ ወዲህ ባሉት ቀናት፣ ከጥቅምት ወር ወዲህ አዲስ አበባ የተለወጠች ከተማ መስላ ሰንብታለች፡፡ ከዚህ በፊት (ከተለመደው የእንግሊዝ ፕሪሚየርሊግ ወግ በቀር) ብዙም የደመቀ የኳስ ወሬ የማይስተዋልባት ከተማ በዚሁ ወሬ ተጠምዳ ሰንብታለች… ብዙ ጊዜ የሕዝብ አስተያየት እንደሚንፀባርቅባቸው የሚታመኑት የታክሲ ውስጥ ጽሑፎች ሳይቀሩ… ‹አዎ እንችላለን› የሚል ጽሑፍ ለጥፈው ታይተዋል፡፡

 

አጋጣሚው የተለየ የፖለቲካ ጣዕምም ተቋድሷል፡፡ ሞሐመድ አዴሞ የተሰኘ፣ ኢትዮጵያዊ የኒውዮርክ ጦማሪ በፌስቡክ ገጹ ላይ የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ከነፖለቲካ ልዩነታቸው አንድ ቡድንን ለመደገፍ የቆሙበትን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጾታል፡-

ስፖርት ሕዝቦችን አንድ ያደርጋቸዋል፡፡ የደስተኞቹ ኦሮሞዎች ስብስብ ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ያንን የሚያስመሰክር ነው፡፡ በአሜሪካ ሁለቱ ወገኖች (ኦሮሞዎች እና ሌሎቹ ኢትዮጵያውያን) አንድ ቡድን ለመደገፍ የምንገናኝበት ዕድል በጣም ጠባብ ነው፡፡ የተለያዩ የስፖርት ግጥሚያዎች እና ፌዴሬሽን ነው ያለን፡፡

ዛሬ በደቡብ አፍሪካ ላሉ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ደጋፊዎች ምርጫው በኦነግ ባንዲራ እና በአገልግሎት ላይ ባለው የኦሮሞ ባንዲራ መካከል ነበር፡፡ እናንተም ቀድማችሁ በግልጽ እንዳስመሰከራችሁት፣ ኦሮሞም ሆኑ የኦሮሞ ያልሆኑ የኢትዮጵያ ቡድን ደጋፊዎች የሚያውለወልቡት ባንዲራ ልዩነት ምንም ችግር የለውም፤ ምክንያቱም ሁሉም የሚደግፉት አንድ ቡድን ነበር፡፡

ለረዥም ጊዜ፣ የዓለም አቀፍ የስፖርት እንቅስቃሴዎች፣ አንዲት ኢትየጵያን ለዓለም ሲያስተዋውቅ ነበር፡፡ የ3000 ዓመት ታሪክ ያላት፣ የክርስትያን ደሴት፣ አንድ ባንዲራ ያላት እና አንድ አማርኛ የምትናገር ኢትዮጵያን፡፡

እውነታው ግን፣ ኢትዮጵያ የብዝኃ-ብሔሮች አገር በተለያዩ ታሪኮች እና ባሕሎች የተገነባች መሆኗ ነው፡፡ በውጤቱም፣ ብሔራዊ ስሜቶች እየጎሉ መጥተዋል፡፡ ባለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታዊ ሥርዐቶች ለምሳሌ፣ ኦሮምኛ መናገር በሕዝባዊ ስፍራዎች እና በመንግሥት ጽ/ቤቶች ውስጥ የተፈቀደ አልነበረም፡፡

በኢሕአዴግ ኢትዮጵያ፣ የቋንቋና የባሕል መብቶች – ቢያንስ በኀልዮት ደረጃ ቢከበሩም የኦነግን ባንዲራ ማውለብለብና መልበስ በሽብርተኝነት ያስቀጣል፡፡ ዛሬ ያያችሁት (ስለኦሮሞ ሕዝብ ያለውን ትርክት ለመቆጣጠር የሚፈልጉ ሰዎች ስድብ እና ዘለፋ) የመነጨው ከዚህ የሐሰት የአንድነት ቀኖና ነው፡፡  ከናንተ ጋር የምስማማው፣ ልዩነታችንን በመቀበል እና ሕዝቦች ያመኑበትን በማክበር ወደፊት መቀጠል ስንችል ነው፡፡

በተመሳሳይ መንገድ፣ የኦሮሞ አራማጆቻችን ከፖለቲካ አጀንዳ አፈንግጠው ኳሱን ብቻ ለመመልከት የፈለጉትን የኳስ አፍቃሪዎች ስሜት በብሔር ነክ ጥያቄዎች ማስጨነቃችሁን ማቆም ይኖርባችኋል፡፡

ይህም ሆኖ ሳለ፣ እንደአንድ አስተዋይ ዜጋ የሚከተሉትን ጥያቄዎች መጠየቅ ተገቢ ይሆናል፡- ማነው ኢትዮጵያዊ፣ የኢትዮጵያዊነት መለያ ምንድን ነው፣ የኢሕአዴግ ባንዴራ የኢትዮጵያዊ ብዝኃነትን ይወክላል፣ የኦነግን ባንዲራ ማውለብለብስ ገንጣይ ያሰኛል፣ ለምን ኦሮሞዎች የኦነግን ባንዲራ ይወዱታል፣ ለምን ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን ኦሮሞነታቸውን የሚወዱ ኦሮሞዎችን ማየት ያስደነግጣቸዋል… ወዘተ፡፡

Shared by Ermias M Amare on Facebook

Ermias M Amare በተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ የተለጠፈ

#TeamEthiopia እና #Eritria በሚሉ ሀሽታጎች ትዊተር ላይ ስፖርትና ፖለቲካ ላይ ያተኮሩ በርካታ ውይይቶች ተካሄደዋል፡፡ ክዌስችን ሚዲያ የተባለ ተጠቃሚ ያሰፈረውን ትዊት እንመልከት:-

የ #ዛምቢያ ደጋፊዎች አንድ ባንዲራ ብቻ ሲያውለበልቡ፣ የ#ኢትዮጵያ ደጋፊዎች ከሁለት በላይ ባንዲራዎችን አውለብልበዋል፡፡ ፖለቲካ የተቀባ ኳስ – መፍትሔ ያልተሰጣቸው ጉዳዮች ነፀብራቅ፡፡

ለዘሪሁን ደግሞ ኤርትራ እስካሁን የኢትዮጵያ አካል ብትሆን ለኤርትራውያን ጥሩ እንደነበር በዕለቱ ተካሄደ ስለተባለው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየጠቀሰ ይናገራል፡፡ ሙሉ ትዊቱ ይኸው:-

ለመገንጠል ባትፈቅዱ ኖሮ፣ ይህንን ጫወታ አብራችሁን ትደሰቱበት ነበር 🙂 #ኢትዮጵያ በዛሬው የአፍሪካ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ተደስታለች፡፡ #ኤርትራ #የኢትዮጵያቡድን

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ዋንጫ ቡድን ሲ ውስጥ ከተመደበችው ቡርኪና ፋሶ ጋር፣ ዛምቢያ ደግሞ ከናይጄሪያ ጋር ቀጣይ ጫወታ ታደርጋለች፡፡ የ2013ቱ የአፍሪካ አገራት ዋንጫ፣ የብርቱካናማ የአፍሪካ አገራት ዋንጫ በመባልም ይታወቃል፣… በአፍሪካ የእግርኳስ ኮንፌዴሬሽን የሚዘጋጅ የአፍሪካ እግርኳስ ሻምፒዮኖች መለያ ነው፡፡ ይህ 29ኛው የአገራት ዋንጫ ሲሆን ከጥር 11/2005 እስከ የካቲት 3/2005 ድረስ ይዘልቃል፡፡

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.