ይህ የባቡር መሥመር የአቡነ ጴጥሮስንና የዐፄ ምኒሊክን ሐውልት እንዲነሡ ያደርጋል?

ጊዜው 1988 ዓ.ም. ነበር፤ ጣሊያን ኢትዮጵያን በትዕቢት የወረረችበት፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት የነበሩት አጼ ምኒልክ መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎናቸው አሰልፈው የጊዜውን ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የጣሊያን ጦር አድዋ ላይ ድል አደረጉ፡፡ በቀሪው የንግስና ዘመናቸው ደግሞ በዘመኑ መንፈስ የተቃኙ ብዙ ስራቸውን ሲያከናወኑ የባቡር መስመርን ጨምሮ በርካታ ስልጣኔዎች ወደሀገራችን እንዲገቡ ጥረት በማድረግ አሳልፈዋል፡፡  ለዚህ  የአድዋ ድልና ሀገሪቱ ዘመናዊ እንድትሆን ላደረጉት ጥረት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ይህ  ሐውልት በመሐል አዲስ አበባ አራዳ ጊዮርጊስ ቆመላቸው፡፡

 በቆራጥ ኢትየጵያውን ጽናት የተሸነፈው የጣሊያን ጦር ለአራት አስርት ዓመታት ራሱን ሲያደራጅ እና ሲያደባ ቆይቶ  በ1928 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ወረረ፡፡ ከመጀመሪያዎቹ ኢትዮጵያውን ጳጳሳት አንዱ የሆኑት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ እጃቸውን ተይዘው ማርሻል ግራዚያኒ ፊት ቀረቡ፡፡ “የኢጣሊያ መንግስት ገዢነትን  አሜን ብለህ ተቀበል” ተብለው ሲጠየቁ “የኢትየጵያ ህዝብ ለዚህ ጠላት እንዳይገዛ አውግዣለው፡፡ የኢትዮጵያ መሬት ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡በፈጣሪዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተወገዘች ትሁን፡፡” ብለው ተናገሩ፡፡ከዚያ በማርሻል ግራዚያኒ ትእዛዝ በስምንት ጥይት ተደብድበው ወደቁ፡፡ አለመሞታቸው ሲታወቅ ከግራዚያኒ አዛዦች አንዱ በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራሳቸውን በመምታት ገደላቸው፡፡  ይህን ለሀገር ነጻነት የከፈሉትን መስዋዕትነት ለማዘከር በግፍ ከተገደሉበት ቦታ በቅርብ ርቀት ሐውልት ተሰራላቸው፡፡

ይሁንና ከቻይናው ሪልዌይ ግሩፕ ሊሚትድ ጋር በመተባበር  የከተማ ባቡር መስመር ለመዘርጋት ያቀደው  የኢትዮጵያ መንግስት እነዚህን ሁለት ሐውልቶች ሊያፈርስ መዘጋጁቱ ብዙ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል፡፡

 ስለኢትዮጵያ ታሪክ ባሕል እምነት ፖለቲካ እና ትውፊት ምልከታውን የሚያቀርበው ዳንኤል ክብረት  መሠረታዊ ጥያቄውን በማስቀድም ትችቱን አስከተለ፡

 

ይህ የባቡር መሥመር የአቡነ ጴጥሮስንና የዐፄ ምኒሊክን ሐውልት እንዲነሡ ያደርጋል?

ለዚህ ጥያቄ ምላሹ ‹አዎን› ከሆነ ስለ ባቡሩ የሚኖረን ግምት ይለያል፡፡ ኢትዮጵያን እናሳድጋለን ስንል ያሳደጓትን እየዘነጋንና መታሰቢያቸውን እያፈረስን መሆን የለበትም፡፡ ‹በማን ላይ ቆመሽ እግዜርን ታሚያለሽ› አለ ያገሬ ሰው፡፡ የምናመጣው አዲስ ነገር ባለን ላይ የሚጨመር እንጂ ያለንን የሚያጠፋ መሆን የለበትም፡፡ መኪና ያስፈልገናል፣ ግን እግር የሚቆርጥ መሆን የለበትም፡፡ ወደድንም ጠላንም ይህች ሀገር የታሪክና የቅርስ ሀገር ናት፡፡ ይህ ታሪኳና ቅርሷ ደግሞ የህልውናዋም ምንጭና መሰንበቻም ጭምር ነው፡፡ ይህን ታሪክና ቅርስ እያጠፉና እያበላሹ የሚመጣ ለውጥ አንገት ቆርጦ ፀጉርን እንደማስተካከል ነው የሚቆጠረው፡፡ እናም የሚመለከታቸው ሁሉ ወደ ርምጃ ከመግባታቸው በፊት ሦስት ጊዜ ሊያስቡ ይገባል፡፡ መቼም የመጀመርያውን ባቡር ያስገቡትን የዐፄ ምኒሊክን ሐውልት አፍርሶ ባቡር እናስገባ ማለት የታሪክ ምጸት ነው፡፡ ለነጻነት የተሠውትን የአቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ነቅሎ በባቡር ላይ በነጻነት ለመሄድ መከጀል ግፍ መሥራት ነው የሚሆነው፡፡”

 

አብይ ተክለ ማርያም ደግሞ ይህ ወሬ ውሽት እንዲሆን ተመኝቷል፡፡

አሁን በአዲስ አበባ እየተገነባ ላለው የባቡር መስመር ዋና ቲፎዞ ነኝ፡፡ ከአራት አመት በፊት ስለእርሱ ረጅም መጣጥፍ ጽፌ ነበር፡፡ ነገር ግን እጅግ ጥልቅ የዐሳብ ድህነት ያጠቃቸው የከተማችን ንድፍ ሰሪዎች መስመሩን ለመዘርጋት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጣቸውን ታላላቅ የታሪክ ምልክቶችን የሚዘክሩ ሁለት ሐውልቶች ለማፍረስ ወይም ቦታቸውን መቀየር አለብን ብለዋል? በፌስቡክ ያነበብካቸው አሉባልታዎች ውሸት እንዲሆኑ ተስፋ አደርጋለው፡፡

 

ሙሴ ጌታቸው ቀጠለ፡፡

1.ጧት ጉዞ ላይ ሳለሁ፤ ፋና ሬዲዮ ይፈርሳሉ ተብሎ እየተወራ ያለው የአጼ ምኒልክ እና የአቡነ ጴጥሮስ ኅውልቶች የማህበራዊ ድረ-ገጾች የሚያናፍሱት ያልተጣራ አሉባልታ እንደሆነ ነገረን።

2. ፋና በተጨማሪ እንዳወራው አዲስ አበባ መንገዶች ሊያሰራ ባአቀደው መንገድ፦

1.1. የአቡነ ጴጥሮስ ኅውልት ብቻ ተነስቶ፤ መንገዱ ከተጠናቀቀ በኋላ ተመልሶ እንደሚተከል

1.2. የአጼ ምኒልክ ኅውልት ግን በምንም ምክንያት እንደማይነካ ነበር የነገረን።

3. አሁንም ኢህአዴግ/መንግስት ካለው ድብቅነት ያስተላለፈው መልዕክት በፍፁም አላምነውም። ይህም እንደ ቀድሞዎቹ ጀግኖቻችን እና አርዓያዎቻችን የመግደል አባዜ ነው።

4. የአውሮፓ የጥንት ከተሞች ላይ ያሉ ኅውልቶችም ሆኑ የቅርስ ቦታዎች በመሰረተ ግንባታ ምክንያት ሲፈርሱ ሰምቼም አይቼም አላውቅም። ከዚህ በተቃራኒ Site Adaptation በመጠቀም ከቀድሞ ጎልተው እንዲታዩ ይደረጋሉ።

5. ምናልባት ህዝቡን ለማሳመን መንግስት ይህንንም እንደሌሎቹ ልምዶች (የምርጫ የስነ-ምግባር ህግ፣…) “ከሌሎች አገሮች የቀሰምኩት ምርጥ ልምድ ነው” ማለት ነበረበት።

አንድ አድርገን የተባሉ ህቡዕ ጦማሪያን ደግሞ አስተያየታቸውም እንዲህ አስፍረዋል፡፡

 እኛ እያልን ያለነው ሀገሪቱ ላይ የሚሰሩ ፕሮጀክቶች ለምን ቅድመ ጥናት ሲካሄድ የእምነትና የሐውልት ቦታዎች ፤ የአባቶቻችን ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለኢትዮጵያ አሻራቸውን ያስቀመጡበት ቦታ ከግምት ውስጥ አይገባም ? ወይስ ከበስተጀርባ ሌላ ነገር አለ……?..

 

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት አ.ማ በመካነ ድሩ ዜናውን አስተባብሎ እርስ በርሱ የሚጣረስ ዘገባውን አስነብቧል፡፡

 ሀውልቱ  ምንም ችግር ሳይደርስ የባቡር መስመር ዝርጋታው ይከናወናል ያሉት ሃላፊው ፥ የባቡር መተላለፊያ ዋሻ ከሃውልቱ ስር ስለሚገነባ ፤ ግንባታው እስኪያልቅ ድረስ ሃውልቱ ለጥቂት ጊዜ ተነስቶ ከዋሻው መጠናቀቅ በኋላ ወደ ቦታው እነደሚመለስ ተናግረዋል።አያይዘውም ይህ የባቡር መስመር ግንባታ የዳግማዊ ሚኒሊክ ሀውልትን በምንም መልኩ እንደማይነካው የሚወራው ወሬ መሰረተ ቢስ መሆኑንም ነው ያስረዱት።”

 

መንግስት በሐውልቶች ምክንያት ከህዝቡ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲገጥመው ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከዚህ በፊት በቻይና መንግስት በተገነባው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ቅፅር ግቢ ውስጥ የአፍሪካ አባት ተብለው የሚጠሩት ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴን በመተው ለጋናዊው ክዋሜ ንክሩማህ መሰራቱ ብዙዎችን እንዳስከፋ የሚታወስ ነው፡፡

2 አስተያየቶች

 • የሰልፍ ሃገሯ ወዴት ነው?

   ቢፒአር ሆይ ወዴት አለህ?
   ዘመናዊ ‘ሬሽን’ /ክፍፍል ተጀመረ እንዴ?
  ከሥራ ወጥቼ በሃይገር ባስ ወደቤት እየተመለስኩ ነው፡፡ ከጎኔ የተቀመጠው ወጣትና ሹፌሩ ወሬ አሙቀዋል፡፡ እኔ የጆሮዬን ቀልብ ወደነሱ ጣል እያደረኩ በዓይኔ ቀልብ ከባቢዬን እየዳሰስኩ እጓዛለሁ፡፡
  “ወይ ጉድ ደ’ሞ ምን ተፈጠረ?” ወጣቱ ይጠይቃል
  “ጋዝ ሊገዙ ነዋ!” ሹፌሩ ይመልሳል፡፡
  አይናቸውን ተከትዬ አማተርሁ፡፡ የነዳጅ ማደያው በሰዎች ሰልፍ ተሞልቷል፡፡
  “በቃ ያለሰልፍ የሚሆን የለም?”
  “ምን ታደርገዋለህ!”
  ግን ቆይ ምንም ማድረግ አንችልም እንዴ? በቃ ለሁሉ ነገር ካልተሰለፍን የንግድም ሆነ የኑሮ ሕይወት አይተነፍስም ማለት ነው?
  ትዝ ይለኛል የሞባይል ሲም ለማውጣት የተሰለፍኩት ሰልፍ ርዝመትና የወሰደብኝ ጊዜ-ሊያውም በመከራ የተገኘ ሰልፍ ነበር፡፡ ተሰልፎ ውሎ ነገ ኑ ወይም የለም አልቋል ከመባል የተሻለ ነበር ምክንያቱም የሰልፍ ተራ ደርሶኝ ገዥቼ ነበርና፡፡ ሲም ያወጣሁበት ያ የዑራኤል ቴሌ መንደር በቅርብ ጊዜ ሌላ ረዥም ሰልፍ አይቼበት ተገርሜ ነበር፡፡ ለካ ሰልፉ ወደ ውጭ ሃገር ለመሄድ የሚሰናዱ ሰዎች ሰልፍ ነበር፡፡ ከኃይሌ ዓለም ህንጻ በላይ የጀመረ ርዝመቱ ተጠማዞ ፍትህ ሚኒስቴር ደርሶ ነበር፡፡ ያው አካባቢ ዛሬ ሃይገሩ በካሳንቺስ አዙሮ/አቋርጦ አመጣን እንጂ ከመኪና ሰልፍ የማይጸዳ መንገድ ነው፡፡ የዑራኤል ትራፊክ ፖሊስ (መቼም መብራቱ ለመውለቅ የተተከለ ነው) ያቆመው መኪና ሰልፍ ባምቢስን ያልፋል፡፡ የባንቢሱ በተራው እስጢፋኖስ ላለመድረስ ይንፏቀቃል፡፡
  “ምን ሰዉ’ኮ ጠፋ የተባለ ጊዜ ነው ሊገዛ የሚሻማው”
  “ምን በሄድክበት ሁሉ ሰልፍ ነው፡፡ አንዲት ወረቀት ለማግኘት ስንት ባዝነህ ነው የምታገኘው”
  “እሱስ ልክ ነህ” ሹፌሩ የገጠመው ነገር ያለ ይመስል ፈጥኖ ተስማማ፡፡ እውነትም ያጋጠመው ነገር ነበር፡፡ የአንድ ትራፊክ ክስ/ቅጣት/ና ለመክፈል የደረሰበትን እንግልት እያወጋው ነበር፡፡
  በእርግጥ በሰልፍ የተወለደ (የመውለጃ ተራ በመጠበቅ ቦታ አጥቶም ሊሆን ይችላል)፣ በሰልፍ ያደገ፣ በሰልፍ የተማረና በሰልፍ ያወቀ ህዝብ ‘ሰልፍ’ ለሁሉ ነገሩ መገለጫ ባይሆን ነው የሚገርመው፡፡
  ባ’ንድ ወቅት ጨው ተወደደ ተብሎ በየሱቁ የነበረ ሩጫና ትግያ ሳስታውስ ብዙ ሕይወታችን ስክነትና እርጋታ ያልተሞላ ነገን በመጠራጠርና ተስፋን በመታረዝ የተሞላ ይመስለኛል፡፡ እስኪ ይለፍ እስኪ ይቆይ ወይም እስኪ ይረጋጋ የሚል ጠባይ አልሰራብንም፡፡ ሩጫችን ‘ነገ ሁሉ ይዘጋል፡ ነገ ሁሉ ያልቃል፡ ነገ ሁሉ ይራቆታል..’ ወዘተ የተባለ ዓይነት ነው የሚመስለው፡፡ እርግጥ የምንሰማቸውን ሁሉ በጥርጣሬና በዚህ መንፈስ ለውጠን የምንሰማቸው ይመስለኛል፡፡ ልክ ነገ ነዳጅ ይጨምራል ከተባለ የመጓጓዣ አገልግሎቱ ይዛነፋል፡፡ ዛሬ በሞላት ነዳጅ ነገ ታሪፍ/ተመን/ ጨምሮ ለመጫን ሌላው ደግሞ ከዋጋ ጭማሪ ቀድሞ ለመሙላት በየማደያው ይሰለፋል፡፡ ነዳጅ ማደያዎች ደግሞ ነገ አትርፎ ለመሸጥ ይቆጥባሉ ወይም ያሳልቃሉ፡፡
  በዚህ ሁሉ ውስጥ የሚታየኝ ነገር ቢኖር ኑሮአችን በሰከነና በተረጋጋ ሃገር ምጣኔ ሃብት/ኢኮኖሚ/ ውስጥ አለመሆኑን ነው፡፡ በተገኘው ጭላንጭል ማትረፍና መዝረፍ ወይም ማጋበስና መሰብሰብ፡፡ ቅንጣት የምጣኔ ሀብት ልውጥ ኑሮአችንን ያናጋል፡፡ ስለዚህም እንሰጋለን፡፡ ነገ የባሰ እንዲመጣ እንጅ የተሻለ እንዲኖር አይታየንም፡፡ እድሜና ልምድ ያስተማረንም ይሄንኑ ነውና፡፡
  ስንዴ ጠፋ፣ ስኳር ጠፋ፣ ዘይት ጠፋ… ስንሰማቸው የሚያሸብሩ ዜናዎች ናቸው ለነጋዴውም ሆነ ለሸማቹ፡፡ ሸማቹም እንዲህ ያስባል “ይህ የምጥ ጣር ምልክት ነው፡፡ በጊዜ አልሞላ ያለ ጎተራዬን ሳይራቆት ላከማችበት” ይላል፡፡ ስለዚህ ፍጆታዎቹ አሉ የተባሉበት ቦታዎች ሁሉ አሳዶ በመሄድ ይሸምታል፡፡ ሁሉም ወዳለበት ስለሚጓዝ ከአንድ ይሰባሰቡና ረድፍ ይሰራሉ-ተርታ ሊይዙ፡፡ ነጋዴውም እንዲህ ይላል “ይቺ የትርፍ ማዋቀሪያ ምልክት ናት፡፡ በጊዜ ሌሎች ሳይቀድሙኝ ሰብስቤ ላከማች…ነገ መጨመሩ አይቀርምና አትረፌ እሸጠዋለሁ” ይላል፡፡ ስለዚህ እርሱም ሊገዛ ይሰማራል፡፡ የሚገርመው ሸማች መሳይ ነጋዴ እንደመኖሩ ነጋዴ የመሰለ ሸማች መኖሩ ነው፡፡ ሸማች መሽሎ ነጋዴ ይሸምታል-ሊሸጥ፡፡ ሸማች የነበረውም ሰብስቦ ከቤቱ ጎተራ ይልቅ ለነጋዴ ይሸጣል-ይነግዳል፡፡
  እነዚህ የንግድ ሥርዓት ክፍለ አካላት ቢሆኑም’ኳ እንደ አንድ ጤነኛ የንግድ ሥርዓት የሚታይ አይደለም፡፡ የንግድ ሥርዓቱ ጤነኛ አለመሆን በንግድ ሥርዓቱ ተሳተፊ የሆኑት ህዝቦች ጤንነት አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡ የህዝቦቹን ጤንነት ከተጠራጠርን በእርግጥም ሃገሪቷ ታማለች፡፡ ስለዚህ ህመምተኛ ሃገር ውስጥ ስላለን መድኃኒታችንን በሰልፍ ውስጥ እንፈልጋለን፡፡ ቀድመን ለማግኘትና ቀድመን ለመግዛት፡፡ ከዚህ በላይ መግዛት አልችልም ጭማሬው በዛ ብሎ ከመጮኽ ይልቅ አብዝቶ መግዛት የህመማችን ምልክት ይመስለኛል፡፡ በየቤት ቁጥሩ በተከፈቱ ካፌዎች ውስጥ ማነው ተጠቃሚው? በውድ እቃዎችን የሚሸምተው ማነው ያጠራቀመው ወይስ የተጠራቀመበት (ማጣቱ)?

  ሌላው ሃገር የዳቦ ዋጋ ጨመረ ሲባል …..ኡኡኡ…..
  የነዳጅ ድጎማ ቀረ …..ኡኡኡ…..
  የምግብ ዋጋ ናረ …..ኡኡኡ….. ይላሉ ኡኡታቸውን በቁጣ እንደኛው በሰልፍ ይገልጻሉ፡፡ ያድማሉ፡፡ ይታደማሉ፡፡ ታዲያ ካልጮኸ ማን ይሰማዋል፡፡ ጮኾም’ኳ እንደሱ ካልቀመሱት በቀር የጩኸቱን ዋጋ አይረዱለትም፡፡ የመሪዎችና የሰሚዎች ጩኸት ሌላ ጆሮአቸው የደለበው በሌላ ነውና..
  እውነት ነው ኑሮ በጣሙን ተወዶብናል በኪነጥበቡ እንጂ መኖር ካ’ቆምን ቆይተናል፡፡ ግን ደፍረን በቃን ካላንነው በቀር ይባሱን በቁማችን እንቀበራለን፡፡ የሚመሩን መፍትሄ ካላበጁልንና ረፍት ካልሰጡን ኑሮና ሕይወታችንን በስጋትና በጥርጣሬ ከሞሉት መመራታችን ጥቅሙ ዜጋ መሆናችን ፋይዳው ምንድነው? መጮኽ በቃኝ ማለት ያስፈልጋል፡፡ የተወደደውን ዳቦ ገዝቶ ከመብላት ይልቅ በቃን መብላት አልቻልኩም ብሎ መጮኽ ያስፈልጋል፡፡ እነሱ አይሰሙም የዳቦ ዋጋ ምን ማለት እንደሆነ አያውቁትምና፡፡ ምግብ ለመኖር መሠረታዊ ፍላጎት መሆኑን ለመረዳት አይሹም፡፡ የሥልጣናቸውን እድሜ ለማራዘሚያ መድኃኒትነት ይጠቀሙበታል እንጂ፡፡
  መሰለፍን ለባለሥልጣኖቻችን የኃያልነታቸውና የኃይላቸው መገለጫ አድርገው ይገልጹታል፡፡ ተራ በመጠበቅ ተሰልፈን ሁኑ የተባልነውን ሁነን የእነርሱን ድራጎት እንድናገኝ ይፈልጋሉ፡፡ ቢፒአር በየመስሪያቤቱ ከሰለጠነ ከብዙ ዓመታት በኃላም አሁንም አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ሰልፍና መንከራተቱ አይቀንስም፡፡ ታች ያለው ባለሥልጣን መሐል ካለው ጋር አይግባባም፤ የመሐሉ ከላዩ ጋር አይቀናጅም ለምን ቢባል አገልግሎቱን ስለመስጠቱ ሳይሆን አለቃውን ስለማስደሰቱና የ’ሱን ትዕዛዝ ስለመፈጸሙ ይጨነቃል፡፡ ትዕዛዝና አሰራር ቀጥና ከላይ ትወርዳለች ለሌሎቹም ዶግማና ጸሎታቸው ትሆናቸዋለች፡፡ ተገልጋዩም እንግልትና ሰልፍ መፍትሄ ከሰጠኝ ብሎ ይቀላቀላል፡፡ ይህን የተለመደ ተግባር ትተን በቅርቡ የመጣው 40/60 የቤት እቅድ ጥሩ ማሳያችን ነው፡፡ የበላይ ባለሥልጣናት በዚህ ቀን ይጀመራል ይሄና ይሄ ያስፈልገዋል አሉ፡፡ ተጻፈም (ምሳሌ፡ ከቀበሌ ቤት አለመኖሩን ማስረጃ..) ነዋሪውም በየቀበሌው ሥራውን አሳታጉሎ ተሰለፈ፡፡ ቀበሌዎች ግን ስለጉዳዩ አያውቁም፡፡ ለተሰለፈው ህዝብ የሰልፍ ቦኖ (ኒብራ) እየሰጡ ሲበትኑና ሲያሰልፉ ዋሉ፡፡ ላልተወሰነ ጊዜ ተሸጋገረ እስኪባል ድረስ፡፡
  መጀመሪያ ላይ ያነሳሁላችሁ የሞባይል ሲም ሰልፍ የሚያሳየው የአገልግሎት አቅራቢው ለነዋሪው የነበረው ዝቅተኛ ግምትና አገልግሎቱን ያለሰልፍና ያለ እንግልት እንዳይሰጡ የዳረጋቸው መሆኑን ነው፡፡ ሌሎቹም አገልግሎቶች ግልጽነትና የአንድ ፈጻሚ አካል እጥረት ለሰልፍና ለእንግልት ይዳርጋሉ፡፡ አሁን አሁን ሳስበው የሚያስፈልጉንን የዜግነት አገልግሎቶች በሙሉ እንደ ሬሽን በእደላ ተሰልፈን ካልሰጡን በቀር ያገለገሉ አይመስላቸውም መሰል፡፡
  እንደ ጉምሩክ የመሰሉ መስሪያ ቤቶችን ያየ ደግሞ የነዋሪውን ችግር መረዳት ይቻለዋል፡፡ ነጋዴው ሂሳቡንም ሆነ ቫት ለማሳወቅ የወሩ መጨረሻ ትዝ የሚለው ይመስለኛል (ሆነ ብሎ ቸል/ይደርሳል በማለት ሳይሆን አይቀርም) የጉምሩክን ግቢ በሰልፍ ይወሩታል፡፡ መስሪያ ቤቱም አገልግሎት ለመስጠት ትንፋሹ እስኪሰልል ይታትራል፡፡ ሲያሰልፉ ሲበትኑ ቁጥር ሲያድሉ ሲቀይሩ፡፡
  የሰልፍ ሃገር ሰልፈኞች መሆናችን እርግጥ ነው፡፡ ከሰልፍ ለመገላገል የቀረበ እድል ያለን አይመስለኝምና ሰልፋችንን ሰልፍን ለማስቀረት’ኳ ብንምጠቀምበት አይሻልም ትላላችሁ?! “አንሰለፍም!” ብለን ብንሰለፍ! ወይም ከማጉረምረም ለመጮኽ ብንሰለፍ!! ቸር ይግጠመን

  ጥቅምት ፳፻፭ ዓ.ም
  አዲስ አበባ

 • […] abelpoly · 译者 leaf · 阅读原文 am · 则留言 (0) 分享: HEMiDEMi · MyShare · Shouker […]

ንግግሩን ይቀላቀሉ

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

 • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
 • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.