የህንድ የሴቶችና ሕፃናት ሕብረት ዕድገት ሚኒስቴር ያወጣው ረቂቅ አዋጅ በፓርላማው ከፀደቀ፣ ሚስቶች በቤት ውስጥ ለሚሰሩት ሥራ ባሎች ውጪ ሰርተው ከሚያገኙት ውስጥ የተወሰነ መጠን ለሚስቶቻቸው እንዲከፍሉ የሚያስገድድ ይሆናል፡፡ በሚኒስቴሩ ዕቅድ መሰረት፣ ሚስቶች በቤት ውስጥ የሚሰሩት ስራ ዋጋ የሚለካበት ሞዴል የተዘጋጀ ሲሆን፣ በዚሁ መሰረት የቤት ውስጥ ሥራ የሚሰሩትን ሰዎችና ሥራቸው ለኢኮኖሚው ያለውን ተዋፅዖ ዕውቅና መስጠት ይቻላል፡፡
ረቂቅ አዋጁ የቤት ውስጥ ሥራ ፈፃሚዎችን “የጓዳ መሐንዲሶች” በማለት ጠቅሷቸዋል፡፡ ሚንስትር ክሪሽና ቲርታህ የክፍያው መጠን ከባሎች ወርሃዊ ገቢ ላይ ከ10-20በመቶ ሊደርስ እንደሚችል፣ ነገር ግን ሚስቶች ለቤት ውስጥ ሥራ የሚከፈላቸው መጠን ተደርጎ መወሰድ የለበትም ብለዋል፤ ይልቁንም እንደማበረታቻ ወይም ተመሳሳይ ነገር መቆጠር አለበት፡፡ ሚኒስትሩ ይህንን ሴቶችን በማጠናከር ረገድ አንድ እርምጃ ወደፊት የመራመድ ያክል ይቆጥሩታል፡፡ ረቂቁ በመስመርላይም (online) ሆነ ከመስመር ውጪ ከፍተኛ ውይይትን አነሳስቷል፡፡
አንዳንዶች “በቤት ውስጥ ክፍያ የማይፈፀምበትን ሥራ መለካት በፅንሰሐሳብ ደረጃ ትክክል እንደሆነ እና መሞከሩትም ተገቢ እንደሆነ ” ተሰምቷቸዋል፤ ነገር ግን ባሎችን የተወሰነ መጠን ያለው ገንዘብ በየወሩ ለሚስቶቻቸው እንዲከፍሉ ማስገደዱ ግን የተሳሳተ አቀራረብ ነው ይላሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ በጉጉት የሚጠይቁት እያንዳንዱን የቤት ውስጥ ሥራ እንዴት ‹የዋጋ መጠን› መስጠት እና ሕጉንም እንዴት ማስፈፀም እንደሚቻል ነው – ተግባር ላይ ሲውል በርግጠኝነት ሊመጡ የሚችሉትን የተለያዩ ጥያቄዎች እያነሱ፡፡
ጥያቄዎቹ በርግጥም አሁንም ተነስተዋል፡፡ ለምሳሌ፣ ሎርድራጅ እንዲህ ይጠይቃል፡
- በባለትዳሮች መካከል የተቀጣሪና/ቀጣሪ ግንኙነት ለመመስረት እየመከራችሁ ነው?
- የሥራውን ሰዓት እና ዝርዝር የሚወስነው ማነው?
መሬት ላይ በወረደ ሪፖርት ዲ ቻይታንያ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሰዎች (ወንዶችና ሴቶች) በጋለ ሁኔታ እየተከራከሩ ያሉበትን ተጨማሪ ጥያቄዎችን ዝርዝር ያስቀምጣሉ፡፡ ለምሳሌ፡-
- በሚስቲቱ ቦታ፣ የቤት ሠራተኛዋ ሁሉንም የቤት ሥራ የመሥራት ኃላፊነት ካለባት፣ የቤት ሠራተኛይቱ እንዴት ነው የምትታየው? የቤት ሠራተኛይቱ ሚስቲቱ ማግኘት የነበረባትን ጥቅም ማግኘት የለባትም? (በዚህ ሁኔታ) ከ10 ወይም 20 በመቶ መጠን ያለውን ክፍያ ለመቀበል መብት ያለው ማነው?
- 10 ወይም 20 በመቶ የሚሆነው የባልየው ደሞዝ መጠን በሚስቲቱ ስም መቀመጥ ካለበት፣ የአስቤዛውንስ ወጪ ማን ይሸፍናል?
- ይህ ሕግ በሚስቶችና ባሎች መካከል አዲስ የገንዘብ ጦርነት አያጭርም? ልክ እንደ ወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ 498-A፣ የአስቤዛ ሕግ፣ የቤት ውስጥ ጥቃት ሕግ፣ ይሄ ሕግ በአንዳንድ ሚስቶች አላግባብ መጠቀሚያ አይሆን ይሆን?
ጦማሪዋ ሱርያ ሙራሊም ይህንን ሕግ መንግስት እንዴት እንደሚተገብረው በአግራሞት ትታዘባለች፡፡ በጦማሯም እንዲ ትላለች:
ሴቶችን ማጎልበትን እደግፋለሁ፣ የገንዘብ ነፃነት እንዲኖራቸውም ጭምር… (ነገር ግን) ፍራቻዬ፣ እነዚህ ሕግ አውጪዎች ረቂቁን እንዴት ነው የሚተገብሩት? ባልየው የገቢውን የተወሰነ ሽራፊ ለሚስቱ የሚያካፍል ከሆነ እንዴት የቤት ውስጥ ኢኮኖሚውን ሁኔታ እንደሚያሻሽለው እና ሴቷንም በገንዘብ ነፃነት እንዴት እንደሚያጠናክራት አይታየኝም፡፡ ድምር ገቢው ዞሮ ዞሮ አንድ ስለሚሆን በቤትውስጥ ኢኮኖሚው ላይ ለውጥ አይኖርም፡፡ ብዙዎቹ ኃላፊነት የሚሰማቸው ባሎች፣ የቤት ውስጥ ወጪዎችን ከሚስቶቻቸው ጋር አሁንም ቢሆን ይካፈላሉ…. ጉዳዩ የተለየ ከሆነ ደግሞ፣ ይህ ዓይነቱ መፍትሄ የባል-ሚስት የቤት ውስጥ ቀመርን አያስተካክለውም፡፡
አርቻ ጃያኩማር በአይዲቫ ላይ ሲጠይቅ፡-
ይህ ከተከበረች የቤት ሠራተኝነት ሌላ ምንም የማያደርጋት እንዴት ነው?
ሱኒታ ደግሞ በSupari.org ላይ ከረቂቁ ጋር በመስማማት”ሰበር የመንግስት ቤተሰብ ነክ እርምጃ” እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ጦማሪው ሎርደራጅ ግን በመደምደሚያው እንዲህ ይላል፡-
በሴቶች ዕድገት እና ደህንነት ጉዳይ፣ የተያያዛችሁት ነገር ቢሆን ወንዶች ላይ መዝመት ነው፡፡
የወንዶች መብት ቡድንም በዚህ ይስማማል፡፡ ቪኪ ናንጃፓ ይህን ይጠቁማል፡-
የባሎችን ገቢ ቆርጦ ለሚስቶች ለመስጠት የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ የወንዶች መብት ቡድን በከፍተኛ ሁኔታ ይቃወመዋል… ‘የቤተሰብ አድን ፋውንዴሽን’ ለሚኒስትር ክሪሽና ቲራት (የሴቶችና ሕፃናት ሕብረት ዕድገት ሚኒስቴር) ደብዳቤ ረቂቅ አዋጁ ከወዲሁ እንዲሰረዝ ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ፋውንዴሽኑ፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ፣ ከ40 በላይ የወንዶችን ድርጅቶች በመወከል፣ ረቂቁን የአንድ ወገን ሐሳብ ሲል ፈርጆታል፡፡
የተረገመው የሕንድ ወንድ (The Cursed Indian Male) የተባለው ጦማሪ ተፅዕኖውን ከወዲሁ እየቀመሱትይላል፡-
በእንደዚህ ያለ ማበረታቻ፣ በርካታ ሚስቶች በቤት ውስጥ ሥራ ፈትተው መቀመጣቸው እና ከባሎቻቸው የነፃ አሻንጉሊት መቀበላቸው የሚያስገርም ነገር አይሆንም፤ በዚህ ዓይነቱ የሕንድ የሕግ ስርዓት ቡራኬ፡፡ እናም ይሄ ሁሉ የሚደረገው ደግሞ ሴቶችን በማጎልበት ስም ነው፡፡
ቢሆንም ግን ሌሎች ስለረቂቁ አዎንታዊ ምልከታ አላቸው፡፡ ለምሳሌ፣ የሕንድ የመከራከሪያ መድረክ ላይ በተካሔደ ውይይት ዩሱፍ ተደስቶ ታይቷል፡፡ በጸሑፉ፡-
በርግጥ ይህ ዜና ለጆሮዬ ሙዚቃ ነው፡፡ የገቢ ግብርን ለመቀነስ ብዙ መንገዶችን ይሰጠኛል 🙂
ጦማሪዋ ሱራይ ሙራሊ የምትመክረው፣ ሴቷን በቤተሰብ ውስጥ ‹‹ከቀጣሪ-ተቀጣሪ›› ተዋረድ የሚያላቅቁ እና በርግጥም የሚያጠናክሩ ሌሎች የተሻሉ ተግባራዊ መፍትሄዎች እንዲቀርቡ ነው፡፡ በእርሷ ጥቆማ፡-
መንግስት ሴቶች በቤት ውስጥ የሚያበረክቱትን የኢኮኖሚ ተዋፅዖ አስልቶ ለቤት እመቤቶች/ የቤት ሠራተኞች አበል ይፍቀድላቸው፡፡ ይህ ባሎችን ለሚስቶች መጠናከር ቀጥተኛ ተጠሪ እንዲሆኑ ከማድረግ ያድናል፡፡ በኔ አስተያየት፣ ይህ ሴቷን ከጥገኝነት ማላቀቅ ብቻ ሳይሆን የቤት ውስጥ ኢኮኖሚ ሁኔታንም ከስስት ኑሮ ያላቅቀዋል፡፡ ከዚያ፣ ሁለቱም ኢኮኖሚውን የማሳደግ እና ሴቶችን የማጠናከር ሕልም ግቡን ይመታል፡፡
ኢንፎኩዊንቢ በመስማማት የምትጨምረው፡-
ሕጉን ለቤት እመቤቲቱ ‹ደሞዝ› መስጠት ከማድረግ ይልቅ ለሚስቲቱ እና ልጆቹ የሕይወት፣ ሕክምና እና ኢንቨስትመንት ኢንሹራንሶች እንዲገቡላቸው ቢደነግግ መልካም ነው፡፡
የሚኒስትሩ ዕቅድ ምን እንደሚደርስ እስከምናይ ድረስ፣ ባልየው ‹‹ለጓዳዋ መሐንዲስ›› የሚያስብላት የማበረታቻ ክፍያ ጉዳይ ላይ የሚነሳው የጦፈ ክርክር ማቆሚያ አይኖረውም፡፡