- Global Voices በአማርኛ - https://am.globalvoices.org -

ማንነትን መነሻ ያደረጉ ግጭቶች የኢትዮጵያን የማህበራዊ ሚዲያ የሐሳብ ልዉዉጥ እንዴት ሊያጋግሉ እንደሚችል

Categories: ከሰሃራ በታች, ኢትዮጵያ, መገናኛ ብዙሐን እና ጋዜጠኝነት, ብሔር እና ዘር, ቴክኖሎጂ, የዜጎች መገናኛ ብዙሐን, ዲጂታል አራማጅነት, ጦርነት እና ግጭት, ፖለቲካ, 'የዓለም ድምጾች' አድቮኬሲ

በአዲስ አበባ የሚገኝ አንድነት ፓርክ፤ ኢትዮጵያ፣ሕዳር 2012 ዓ.ም ፎቶ፡ በራስ አዲሱ ’Flickr CC BY-SA 2.0 [1]’ በኩል

ከተለያዩ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት የተወጣጡ መሪዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ቤተ-መንግስት ውስጥ የተሰራውን የአንድነት ፓርክ ምረቃ ስነ-ስርዓት [2] ለማክበር በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም የሀገሪቷ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ ተገኝተው ነበር።

ይህ ፓርክ የለውጡ መሪ በሆኑት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይ አሕመድ የግል ተነሳሽነት [3] የተገነባ ሲሆን የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ብሔር ብሔረሰብ እና ባህልን የሚያሳዩ ማዕከለ-ስዕላትን(galleries) አካቶ ይዟል [4]። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ቀደምት ነገሥታት ከሆኑት፣ በድምሩ ለ70 ዓመታት በንግስና የቆዩትን የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ እና አፄ ኃይለስላሴን  ባለቀለም የሰም ሀውልት ይዟል።

ይህ ፓርክ የሁሉም [5] ኢትዮጵያኖችን ታሪክ [6] ለማንፀባረቅ እንዲሁም የሀገሪቱን የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች፣ሀይማኖቶች፣ባህሎች፣ታሪካዊ ቅርሶች እና ብርቅዬ እፅዋትና እንስሳትን ለማክበርና ለመዘከር ታልሞ የተዘጋጀ ነው።

ነገር ግን በማህበራዊ ሚዲያ የቀረቡ ዘገባዎች [7] ምልከታ እንደሚያሳየው የፓርኩን መመረቅ ተከትሎ ፖለቲካና ዘር ተኮር የሆኑ አፀፋዎች፣ በተለይም በሁለቱ ታላላቅ የአማራና ኦሮሞ ብሔሮች መካከል በጎሳ መስመሮች ላይ ያረፉ እርስ በእርስ የሚደረጉ ትርክቶች [8] ተስተናግደው ነበር።

በዚህ ክፍፍል በዋነኝነት ሁለቱ ቀደምት መሪዎች በነገስታት አልባሳት አጌጠውና በዙፋናቸው ተቀምጠው የሚያሳዩትን ሀውልቶች አስመልክቶ ሁለት ፅንፍ የያዙ ግብረ-መልሶች ይገኛሉ ። እነዚህም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ሥር የሰደዱ የስህተት መስመሮችን የሚወክሉ ናቸው፡፡

[9]

የአፄ ኃይለ ስላሴ የሰም ሀውልት
 ፎቶ፡ በኤዶም ካሳዬ

አብዛኛው የአማራ ብሔርተኞች በፕሮጀክቱ ደስተኞች ቢሆኑም ጥቂቶች ግን አብይ ራሱን እንደ ኦሮሞ ስለሚለይ ‘የአብይ ከንቱ ፕሮጀክት [10]’ ሲሉ አጣጥለውታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በርካታ የኦሮሞ ፖለቲከኞች እና ተሟጋቾች ቁጣቸውን አሰምተው የነበረ ሲሆን በተለይም በሁኔታው ተበሳጭቶ [11] የነበረው ታዋቂው ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ጃዋር መሐመድ ተጠቃሽ ነው። አቶ ጃዋር ለዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ እና አፄ ኃይለስላሴ ሀውልት ማሰራት ማለት በአፄዎቹ ስርዓት ስር ለተጨቆኑ ኦሮሞዎችና ሌሎች ብሔሮች ስደብ ነው ሲል ተናግሯል [11]

ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ሀገሪቷን በለውጥ ጎዳና [12] ያስኬዱ የመጀመሪያው ዘመናዊ የኢትዮጵያ ንጉስ ተደርገው በሰፊው ይወሰዳሉ። እሳቸውም የነፃነት እና የይቅርታ ምልክት ተደርገውም ክብር የሚሰጣቸው [13] ቢሆንም በሌላ በኩል የደቡብ ክልል ነዋሪዎችን ከመሬታቸው በማፈናቀል አማርኛ ቋንቋና ክርስትናን የታደለ ልዩ መብት ሰጥተዋል ተብለውም ይወቀሳሉ [14]

በቀጣዩ ቀን አቶ ጃዋር የፖለቲካ አርበኛና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) መስራች አባል ከሆኑት ከአቶ ሌንጮ ለታ ጋር በመሆን የአኖሌ የሰማዕታትን የመታሰቢያ ሀውልት ለመጎብኘት ስፋት ባላት ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ወደምትገኘው ማዕከላዊ ምስራቅ ሄጦሣ አውራጃ ተጉዘው [15] ነበር። ይህ ስፍራ በ19ኛው ክ/ዘመን መገባደጃ የኦሮሞ ህዝብ በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ የደረሰባቸውን ለብዙ ጊዜ የቆየ [16] የጭካኔ ግድያዎች፣ የባህል መገለል፣ የአባቶቻቸውን መሬት ማጣትና በደል የሚያመለክት ታሪካዊ ቦታ ነው።

ከሳምንታት በኋላ ጃዋር በቴሌቪዥን በሰጠው ቃለ መጠይቅ እንዲህ ሲል ተናግሮ [17] ነበር።

 As long as they elevate Menelik, we will dig out his crimes and make generations know about his crimes, as long as they elevate Haile Selassie. … we are going to do that.

እነሱ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክን እስካሞገሱ ድረስ እኛ ደግሞ የሱን ወንጀል ፈልፍለን ትውልድ እንዲያውቀው እናረጋለን። ሀይለስላሴን እስካሞገሱ ድረስ….ያንኑ እናደርጋለን።

ይህ የአንድ ጊዜ ጉዳይ አልነበረም።

ዶ/ር አብይ በመጋቢት ወር 2010 ዓ.ም ወደስልጣን መጥተው የ27 ዓመታትን የጭቆና ቀንበር ካስወገዱ [18] በኋላ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ግጭት በለበሱ ቋንቋዎች ስለተለያዩ ጉዳዮች ማለትም ታሪካዊ ክስተቶችን፣ ባንዲራን [19]ፖለቲካዊ ተቃውሞን [20]ታሪካዊ ሀውልቶችን [21] እና ስለ ቀደምት መሪዎች [22] የተነሱት አርዕስቶች ሰፊውን ቦታ መያዝ ጀምረው ነበር።

ይህም ተደጋጋሚ ሂደት ነው።

በአጭሩ የሚሆነው አንዲህ ነው፤ አንድ የመንግስት ባለስልጣን፣ የተቃዋሚ መሪ፣ ጋዜጠኛ ወይም ዝነኛ ግለሰብ አንድን በታሪክ ታዋቂ የሆነን ሰው አስመልክቶ አስተያየት ይሰጣል። ለምሳሌ በአንድ ታዋቂ የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ ላይ ስለ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ቢጻፍ በደቂቃዎች ውስጥ ማህበራዊ ሚዲያው በመቶዎች በሚቆጠሩ የድጋፍና የተቃውሞ ምላሾች ይሞላል።

የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ የሰም ሀውልት ፎቶ- በኤዶም ካሳዬ

እነዚህ ባህልን መሰረት ያደረጉ እሰጥ-አገባዎች በማህበራዊ ሚዲያ በተለያዩ ብሔሮች በተለይም በምሁሮቻቸው መካከል ቂም [23] የተሞላ ድባብ እንዲጠነክር ያደርጋሉ። እነዚህ ጥቃቶች አንዱ የብሔር ቡድን በሌላው ፀብ ምክንያት ለመጥፋት አደጋ ተጋልጧል የሚል ስሜት ስር አንዲሰድ ይዳርጋሉ።

ከመጋቢት 2010 ዓ.ም በኋላ በሀገሪቱ በፍጥነት እየተለወጠ የመጣው የሚዲያ ስነ-ምህዳር ውጤት አንድ አካል የሆኑትና በስፋት ወደ ህዝብ የመጡት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች [24] ይህንን ክፍፍል ሲያስተጋቡና ሲያጋግሉ፣ ክፉ መዘዞችንም አስከትለዋል።

ለምሳሌ አቶ ጃዋር ጥቅምት 2012 ዓ.ም ላይ የመንግስት ሀላፊዎች የግድያ ሙከራ ሊያደርጉበት እንዳሴሩ [25] በፌስቡክ ገፁ [25] ላይ መግለፁን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የጋራ ጥቃት [26] ተቀስቅሶ ነበር። በሰኔ 2012 ዓ.ም በአማራ ክልል የተደረገው የመፈንቅለ-መንግስት ሴራ [27] ከፅንፈኞች የማህበራዊ ሚዲያ ትርክት ጋር በመደበኛነት የተገናኘ ሊሆን ይችላል።

የፌስቡክ እና ዩቲውብ ተጠቃሚ ግለሰቦች [28]የመንግስት ደጋፊዎች [29]፣ ተቃዋሚዎች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የዲያስፖራ ጋዜጠኞች በብዙ ጉዳዮች ላይ ከጅማሬውም በተወሳሰበው፣ ግራ በሚያጋባው እና በተጋጋለው የማህበራዊ ሚዲያ ድባብ ላይ ፀብ አቀጣጣይ መረጃዎችን በመዝራት በተደጋጋሚ ይሳተፋሉ። ይህንንም በአብዛኛው ለራሳቸው ዓላማ ድጋፍ የማግኛ መንገድ አድርገው ይጠቀሙበታል።

ሁለት የተቃዋሚ መሪዎች ድጋፍን እንዴት ሊቆሰቁሱ እንደሚችሉ

ሁለቱ የተቃዋሚ መሪዎች ማለትም የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ(ኦፌኮ) አባል የሆነው አቶ ጃዋር መሐመድ እና የቀድሞ የፖለቲካ እስረኛ እና በቅርብ የተቋቋመው የባልደራስ ለእውነተኛ ዲሞክራሲ ፖለቲካ ፓርቲ ሊቀ-መንበር የሆነው አቶ እስክንድር ነጋ የበለጠ ድጋፍን ለማግኘት ማህበራዊ ሚዲያን የሚጠቀሙበት መንገድ ጎልተው እንዲወጡ ያደርጋቸዋል።

አቶ ጃዋር ወደ 1.9 ሚሊዮን የሚጠጉ የፌስቡክ ተከታዮች ያሉት ሲሆን አብዛኛዎቹም ጉጉ ወይም ቀናተኛ ደጋፊዎች ናቸው።  እሱም ራሱን የኦሮሞ ጥቅም ተሟጋች [30] አድርጎ ያስቀምጣል። ብዙ ተከታዮቹ የሆኑት ቄሮ የተሰኙት የኦሮሞ ወጣቶች እንቅስቃሴ  ከፍተኛ አስፈላጊነት እንዳላቸው በጥብቅ ይናገራል ። በአጠቃላይም እንደ መሪያቸው ይገለፃል [31]

ይህ በስፋት በማህበራዊ ሚዲያ የተዘዋወረው ሚም (meme) በጥቅምት 2012 ዓ.ም በዋና ከተማዋ ሊካሄድ ታስቦ በእስክንድር ነጋ የተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ የከተማዋን ነዋሪዎች ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥቅም ላይ የዋለ ነው። በምስሉ ላይ እንደሚታየው እስክንድር ነጋ አንድ የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን(ኦነግ) ባንዲራ ከለበሰ አስፈሪ ፊት ካለው ሰው የከተማዋን ነዋሪዎች የሚከላከል ደፋር ተሟጋች አድርገው አስቀምጠውታል።

በሌላ በኩል እስክንድር ትዊተርን በይበልጥ ድጋፉን የማሳደጊያ መንገድ አድርጎ ይጠቀምበታል። ምንም እንኳን ትዊተርን ዘግይቶ ቢቀላቀልም ብዙ ተከታዮችን በሚገባ ማፍራት ችሏል። የሚሰጣቸው (ላልቶ ይነበብ) አስተያየቶችም ብዙ ጊዜ ከተቃዋሚዎች ቁጣና ንዴት ያዘሉ አፀፋዎችን ሲያስከትሉ ይስተዋላል። የተንቀሳቃሽ ስልኮችና የተንቀሳቃሽ ስልክ ትስስር እየጨመረ በመጣበት በዚህ ጊዜ ይህንን መድረክ መቀበሉ ፖለቲካዊ አንድምታ እንዳለው ተደርጎ ይወሰዳል።

የትዊተር ገፁን [32] በመደበኛነት የቄሮ አባላት በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኙ አናሳ የሀይማኖት እና የብሔር ቡድኖች ላይ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈፅመዋል በማለት ለመወንጀል ይጠቀምበታል። ይህ ለቄሮ ያለው ምልከታ በሺዎች በሚቆጠሩ የአማራ ብሄርተኞች አና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ በሆኑ ግለሰቦች የትዊተር አካውንት መልሶ ይስተጋባል።

ምንም እንኳን ጃዋር እና እስክንድር ሁለት የተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ መድረኮች (platforms) ማለትም ፌስቡክና ትዊተርን ቢቆጣጠሩም አሉታዊ የሆነ ‘ኬሚስትሪያቸው’ ግን እኩል ግልጽ ሆኖ የሚያይ ነው።

ሁለቱም በከፍተኛ ሁኔታ የሚቃረኑ ዕይታዎችን ያንፀባርቃሉ። ለምሳሌ፤ የኢትዮጵያ ፌደራላዊ መዋቅርን፣ የኢትዮጵያ ዋና ከተማና የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ እንዲሁም በኦሮሚያ ድንበር ውስጥ የምትገኘው የአዲስ አበባ ከተማን ህጋዊ ሁኔታ፣ የዳግማዊ አፄ ሚኒሊክን ታሪክ እና የኢትዮጵያ ህገ-መንግስትን አስመልክቶ ያሉ ጉዳዮች ላይ የሚቃረኑ አቋሞችን ይገልፃሉ።

ይህ በማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ተዘዋውሮ የነበረ ሚም (meme) ሲሆን፤ እስክንድር ነጋን ሰላም ፈላጊ ግለሰብ፣ ጃዋር መሐመድን ደግሞ ጸብና ግጭት ቀስቃሽ አድርጎ ይስለዋል።

እነዚህ ግለሰቦች ከደጋፊዎቻቸው ጋር ያላቸውን የቀደመ ጠንካራ ግንኙነት በማህበራዊ ሚዲያው በኩል ይበልጡን ማጠንከር ይፈልጋሉ። በፌስቡክና ትዊተር የሚያገኙት ምላሾች ፣ አስተያየቶች እና ማጋራቶች(retweets and shares) ከሌሎች ተቃዋሚዎች በእጅጉ የሚልቅ ነው።

እናም በመካከላቸው ላሉት ልዩነቶች ሁሉ አሳሳች መረጃዎችን በሀገሪቱ የመረጃ ስነ-ምህዳር ውስጥ በማሰራጨት የየራሳቸው ድርሻ ይጫወታሉ።

አቶ እሰክንድር ብዙ ጊዜ ስለ ኢትዮጵያ ልዩነቶች፣ የታሪካዊ ስፈራዎችን ውድመት እና በተለይም በኦሮሚያ ክልል ስለተፈፀሙ የጥፋት ጉዳዮችን በማጋነን ሌላ መልክ በመስጠት አዙሮ ያስቀምጣል።

ለምሳሌ ከዚህ በታች በሚታየው ትዊት፣ እስክንድር አማርኛ ቋንቋ ከአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ መካከል አንዱ ሆኖ መመረጡን ቢያሰፍርም አማርኛ ቋንቋ ግን የስራ ቋንቋ ሆኖ በጭራሽ ተመርጦ አያውቅም [33]

አዎ ለአማርኛ፣ ለ 700 ዓመታት ያክል ብሔራዊ የኢትዮጵያ ቋንቋ የሆነው አማርኛ የአፍሪካ ህብረት አንዱ የስራ ቋንቋ ለሆነው……አማርኛ የመላ አፍሪካን የረዥም ዓመት የሀገር ግንባታ ታሪክ የያዘ ነው። ይህ ጉዳይ የአንድ ቋንቋ ብቻ አይደለም ይህ በአለም ታሪክ የአፍሪካን ቦታ የሚያሳይ ነው።

ከመስከረም 2010 ዓ.ም ጀምሮ ሁለቱም ተቃዋሚዎች በረዥም የትግል ጎዞ ውስጥ የቆዩ ሲሆን በተለይም በቅርቡ በሕዳር 2012 ዓ.ም ሁለቱም በኢትዮጵያ ላሏቸው የፖለቲካ ፕሮጀክቶች ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ አባላት ገንዘብ ለማሰባሰብ ወደ አሜሪካ ጉዞ ማድረጋቸው [36] ያላቸውን ፉክክር አሳይቷል።

ቄሮ ባይታገል ኖሮ ከወያኔ አገዛዝ መቼም አትወጡም ነበር! ምስጋና ቢሶች!

‘ትናንት ትዊት እንዳደረኩት ፣ ባዶ ማስፈራሪያዎች…. ያለምክንያት የሚደረጉ ተቃውሞዎች ወደ የትም አይሄዱም…ይህ በአስከፊ ሁኔታ በንፁሀን ደም የሚፃፍ የፌዝ ድራማ ነው.. ማን ነው ተጠያቂ?’

በአሜሪካ በነበራቸው ጉዞ ወቅት በደጋፊዎቻቸው መካከል የነበረው የአይጥና ድመት ጨዋታ በሁለቱ ተቃራኒ ወገኖች መካከል ያለውን ውጥረት በሚገባ ያሳየ አጋጣሚ ነው።

የአቶ ጃዋር ጉብኝት በርካታ የሁከት ቀናቶች [39] የተስተናገዱበት ነበር። በፌስቡክ ገፁ ላይ ያቀረበው ውንጀላ [25] በደጋፊዎቹ ዘንድ የጫረው [40] በርካታ ስሜቶች [41] በአዲስ አበባ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ በር ላይ እንዲሰበሰቡ በማድረግ የጀመረ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል የጋራ አመፅ በመስፋፋቱ ምክንያት የ86 [42] ሰዎች ህይወት እንዲያልፍም ምክንያት ሆኖ ነበር።

ተቃዋሚዎቹ ለ86 ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የእርሱ የፌስቡክ ልጥፍ(post) ነው ይላሉ [39]። አቶ እስክንድርም በተለየ ሁኔታ ሀላፊነቱን ወደ አቶ ጃዋር ጠቁሟል [43]

ይሁን እንጂ አቶ ጃዋር የእሱ ፌስቡክ ልጥፍ(post) ከተነሳው ግጭት ጋር የሚያገናኘው ነገር እንደሌለ አስተባብሎ [44] ይልቁንም የሱ ተግባር የከፋ ግጭት እንዳይፈጠር [44] እንዳደረገ ይናገራል።

በመላው አሜሪካ ጉዞ ባደረገበት ወቅት ደጋፊዎቹ [45] የኦሮሞ ህዝቦች በብዛት በሚኖሩባቸው የተለያዩ ከተማዎች ውስጥ የአዳራሽ ስብሰባዎችን በማስተባበርና ገንዘብ በማሰባሰብ አንድነታቸውን አሳይተዋል።

በአብዛኛው የአቶ እስክንድር ደጋፊ የሆኑ የአቶ ጃዋር ተቃዋሚዎች [46] በአሜሪካ የተደረገውን የከተማ አዳራሽ ስብሰባዎችን በመቃወም ተከታታይ ተቋውሞችን [47] አካሂደው ነበር።

ልክ እንደ አቶ እስክንድር ሁሉ አቶ ጃዋርም አጠያያቂ የማሳመን ዘዴዎችን የመጠቀም ልማድ አለው። ብዙ ጊዜም የአማራ ባለስልጣናትን የአፄዎችን ዘመን አፍቃሪ ናቸው፤ አንዲሁም በአማራ ክልል በአናሳ ብሔሮች ላይ የሚያነጣጥር ጥቃትንም ይፈፅማሉ በማለት ይወቅሳቸዋል።

የአሜሪካ ጉዞውን አጠናቆ ከተመለሰ በኋላ የአማራ ክልላዊ መንግስት ባለስልጣናትን በጥላቻ የተሞላ፣ አሳፋሪ የሁከት ዘመቻን አደራጅተዋል፤ እንዲሁም የገንዘብ ድጋፍ አድርገዋል የሚል ወቀሳ [48] አቅርቦ ነበር።

ለወቀሳው ማስረጃ ይሆነውም ዘንድ የአማራ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት አቶ ዮሐንስ ቧያሌው [49] እና ዲያስፖራ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆነው፣ ስድብ [50] እና ፀብ ቃስቃሽ ሀሳቦች [51] በማንሳት ከሚታወቀው ዮኒ ማኛ [52] ጋር የተነሱትን ፎቶ ከፅሁፉ ጋር አያይዞ አቅርቦ ነበር።

 

ይህ ሙከራ የአማራ ክልል ሀላፊዎች ከተቃውሞዎቹ በአንዱ ላይ ታይቶ [53] ከነበረው ከዮኒ ማኛ ጋር አብረው ሰርተዋል የሚል ስሜት ለመፍጠር ነበር።

አንዳንድ ተቃዋሚ ሰልፈኞች የኦሮሞ ተወላጆችን በግልፅ በፀያፍ ቃላት [54] ሲጠሯቸው የነበረ ቢሆንም እነዚህ ተቃውሞዎች በትክክልም በኢትዮጵያ ባለስልጣናት መዘጋጀታቸውን እና በገንዘብ መደገፋቸውን የሚያሳይ ማስረጃ የለም።

ከሕዳር 15 ቀን 2012 ዓ.ም የጃዋር የፌስቡክ ገፅ ልጥፍ(post) ላይ የተወሰደ ቅጽበታዊ-ገጽ እይታ(Screenshot)። የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣን ዮሐንስ ቧያለው (በቀኝ) ዮኒ ማኛ(በግራ) የተነሱት ፎቶ።

የፅንፈኝነት ስሜት ሙዚቃዎች ውስጥ

እስካሁን ድረስ ፀብ ቀስቃሽ መልዕክቶች ሲሰራጩባቸው የነበሩ መንገዶች ፅሁፎች፣ ሚሞች(memes)፣ አጫጭር ክሊፖች፣ ግራፊክስና ስዕሎች ነበሩ። አሁን ግን ማህበራዊ ሚዲያ በስፋት ካደገ በኋላ የብሔር ሽኩቻ ውጥረት ወደ ዩቲውብ ቪዲዎች ተስፋፍቷል።

በጥላቻ ንግግርና ሐሰተኛ መረጃ ላይ የወጣ አዲስ ህግ

በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ “ማህበራዊ መግባባት” እና “ብሔራዊ አንድነት” ለማሳደግ አስተዋፅዎ የሚያደርገውን አዲሱን የጥላቻ ንግግር እና የሐሰተኛ መረጃ ስርጭት ተከላካይ እና ተቆጣጣሪ አዋጅ [55] ህግ አውጪዎች አፅድቀውታል። ነገር ግን ህጉ ሰፋ ያሉ እና ግልጽ ያልሆኑ ትርጉሞችን መያዙ ሀሳብን በነፃነት የመግለፅ መብትን አደጋ ላይ ሊጥል እንደሚችል በተጨማሪም አንዳንድ ድንጋጌዎች  ከአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች ጋር የማይጣጣሙ መሆናቸው ችግር ሊያስከትል እንደሚችሉ የመብት ቡድኖች ይናገራሉ [56]

ብዛት ባላቸው የኦሮምኛና የአማርኛ መዚቃ ቪዲዮች ላይ ዘፋኞች የብሔር ትርክትን የሚያንፀባርቁ፣ የራሳቸውን ወገን የበላይ አድርገው የሚስሉና አንዳንዴም ከሌላው ወገን ጋር ፀብን የሚቀሰቅሱ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ ይደመጣሉ።

ከብዙዎቹ ዘፈኖች መካከል አንዳንዶቹ የሀገር መሬት፣ባንዲራ እና የድሮ ታሪኮች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ። ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክን እንደ ነፃ አውጪ ወይንም እንደ ጭራቅ ማውገዝ ለረጅም ጊዜ ሲደጋገም የቆየ ገጽታ ነው።

በእርግጥ በዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ወታደሮች የተፈፀሙትን ጭፈጨፋዎች ለማሳየት በ2005 ዓ.ም የተከፈተ የፌስቡክ ገፅ [57] ይገኛል።

ነገር ግን የአንድነት ፓርክ መከፈት የመንግስት ሀላፊዎችን የዘር ምንጭ አስመልክቶ ብዙ የኦሮምኛ የሙዚቃ ቪዲዮዎች እንዲሰሩ አነሳስቶ ነበር።

አንድነት ፓርክ የአብይ ፕሮጀክት ስለሆነም አንዳንዶቹ ዘፈኖች ዶ/ር አብይ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክን በማክበር ብሔሩን የካደ እንደሆነ አድርገው ይገልፁታል።አንዱ ዘፈን ብሔሩን አሳልፎ የሰጠ ከሃዲ [58] አድርጎ ሲገልፀው፣ ሌላው ደግሞ ከነጭራሹም ኦሮሞ መሆኑን ጥያቄ ውስጥ ይከታል [59]

የአፋን ኦሮሞ ዘፋኝ የሆነው ጫላ ደገፋ ዶ/ር አብይ ያለፉ ነገስታትን በማወደሱ ምክንያት ብሔሩን የካደ ነው ብሎ ይወቅሰዋል። እንደ ጭራቅ ለሚገልፃቸው ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ ተብሎ የተሰራውን ሀውልትም ይቃወማል።

በተመሳሳይ ቪዲዮ ኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) ‘የኦሮሞ ህዝብ ነጻነት ትግልን በፅናት ያስቀጠሉ ጀግኖች’ በማለት ያለውን አክብሮት ይገልጻል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአማርኛ ቋንቋ ዘፋኞች ደግሞ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክን የአንድነት እና የነፃነት ተምሳሌት አድርገው ይገልጿቸዋል።

ታዋቂነትን እያተረፈ የመጣው የአማርኛ ሙዚቀኛ ዳኜ ዋሌ በአንድ ሙዚቃ ቪዲዮው ላይ ጠመንጃውን ይዞ በካሜራው ፊት በማወዛወዝ ጀግንነቱን የወረሰው አባት ብሎ ከሚገልፃቸው ዳግማዊ አፄ ሚኒልክ እንደሆነ ይናገራል።

‘ወይ ፍንክች’ በተሰኘ የሙዚቃ ቪዲዮ ባህላዊ አልባሳት የለበሱና ጠመንጃ የታጠቁ ብዙ ሰዎች የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለቡ መሬቱን በእልህ ሲረግጡት ይታያል። የሚያጋሳ አንበሳም የቪዲዮው ማጀቢያ ሆኖ ቀርቧል።

እነዚህ የሙዚቃ ቪዲዮዎች በዩቲውብ ላይ ብዛት ያላቸው ተመልካቾችን ያፈሩ ሲሆን የዘር ግጭትን እያቀጣጠሉ በዛውም ከዩቲውብ የሚገኝ ዶላርን ያጭዳሉ።

ይህ  ፅሁፍ ‘’የማንነት መሰረት፡ በአፍሪካ የመናገር ነጻነትን የሚጎዱ ጉዳዮችን በበየነ መረብ አውታሮች መቆጣጠር‘’ ከተሰኘው ተከታታይ ክፍል ውሰጥ አንዱ ነው። እነዚህ ልጥፎች ማንነትን መሰረት ያደረጉ የማህበራዊ ሚዲያ የጥላቻ ንግግሮች ወይም ቋንቋን ወይም ጂዮግራፊን መሰረት ያደረጉ አድልዎች፣ የተዛቡ መረጃዎች እና ትንኮሳዎች (በተለይም ሴት አክቲቪስትና ጋዜጠኞች ላይ) በሰባት የአፍሪካ ሀገራት የዲጂታል ምህዳር (digital spaces) ተስፋፍተው ይገኛሉ እነዚህም፡- አልጄሪያ፣ ካሜሩን፣ ኢትዮጵያ፣ ናይጄሪያ፣ ሱዳን፣ ቱኒዚያ እና ኡጋንዳ ናቸው። ይህ ፕሮጀክት በአፍሪካ ዲጂታል መብቶች ፈንድ ለምስራቅና ደቡብ አፍሪካ አለምአቀፍ የአይሲቲ ፖሊሲ ትብብር (Africa Digital Rights Fund [60] of The Collaboration on International ICT Policy for East and Southern Africa (CIPESA [60]) የተደገፈ ነው።