- Global Voices በአማርኛ - https://am.globalvoices.org -

ሳኡዲአረቢያን መሰናበቻው ቀነ ገደብ ሲቃረብ፣ ኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች አጣብቂኝ ውስጥ ገብተዋል

Categories: ከሰሃራ በታች, ሳውዲአረቢያ, ኢትዮጵያ, ሰብዓዊ መብቶች, ሴቶችና ስርዓተ ጾታ, ስደተኞች, ስደት እና ስደተኞች, የሰብአውያውያን ምላሽ, የዜጎች መገናኛ ብዙሐን, ጉልበት

ሳኡዲ ያሉ ኢትዮጵያውያን በኤምባሲያቸው ውስጥ ያለው ቀርፋፋ አሠራር ላይ ያላቸውን ቅሬታ ከሚያሳይ የኢትዮትዩብ ቪዲዮ ሪፖርት [1] ላይ የተወሰደ ምስል።

በሳኡዲአረቢያ ተሰደው የሚሠሩ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የገልፏ አገር ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያንን አሽጋ ከመመለሷ በፊት መውጫ ቪዛቸውን ለማግኘት እንዲችሉ የሚያስችላቸውን ሰነድ በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲያዘጋጅላቸው መንግሥትን እየለመኑ ነው።

ሳኡዲ አረቢያ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኛ ሠራተኞች አገሯን ለቀው እንዲወጡ [2] የዘጠና ቀን የእፎይታ ግዜ ከሰጠች 3 ወር ሊሞላት ነው።

ሳኡዲአረቢያ እና ጎረቤቷ ኳታር ከአገራቸው የሚወጡ ስደተኛ ሠራተኞች የመውጫ ቪዛ እንዲይዙ ከሚያስገድዱ ጥቂት የዓለማችን አገራት ውስጥ ናቸው። ቪዛውን ለማግኘት ደግሞ መሟላት ያለባቸው ሰነዶች አሉ።

ዳያስፖራ ተቀማጩ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) የሚከተለውን ተናግሯል:

የሳኡዲ ባለሥልጣናት ሕጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ሠራኞች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ከተናገሩ ጀምሮ፣ ሳኡዲአረቢያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኢምባሲ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ እርዳታ እንዳላደረገላቸው በመናገር ስደተኞቹ ጠንካራ ወቀሳ እያቀረቡ ነው።

የ90 ቀኑ የእፎይታ ግዜ ከማለቁ ሳምንት በፊት እና ወራት ከፈጀ ቢሮክራሲያዊ መዘግየት [3] በኋላ፣ ኤምባሲው 80 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ብቻ በሕጋዊ መንገድ የመውጫ ቪዛ የሚያስገኝላቸውን ሰነድ መስጠት ችሏል።

400 ሺሕ ከሚገመቱ በሳኡዲአረቢያ ያልተመዘገቡ የኢትዮጵያ ስደተኞች መካከል፣ 80 ሺሕ ጥቂት የበለጡት ብቻ “የመውጫ ቪዛ አግኝተዋል”፤ የእፎይታ ግዜው በ11 ቀናት ውስጥ ያልቃል።

- አዲስ ስታንዳርድ

750 ሺሕ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች  በሳኡዲአረቢያ እንደሚኖሩ  [8]ይገመታል። ከነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ የሥራ ፈቃድ የላቸውም።

ኢትዮጵያውያን ወደ ሳኡዲአረቢያ በተለያዩ መንገዶች ይገባሉ [9]። ጥቂቶች ፈቃድ አግኝተው በፕሌን ወደአገሪቷ ሲገቡ፣ ብዙዎቹ ግን በአስኮብላዮች ታግዘው በመሬት ወደአገሪቷ ይዘልቃሉ። ሙስሊሞች ወደመካ የሚያደርጉትን ሒጅራ አስታከው በመሔድ በዚያው የሚቀሩም አሉ።

እስካሁን 30 ሺሕ ስደተኞች ወደ ኢትዮጵያ ተጓጉዘዋል። ነገር ግን የአሁኑ ወደ አገር ቤት የመመለስ ዘመቻ ፍጥነት ሲታይ የእፎይታ ግዜው ካለቀ በኋላም ቢሆን ብዙዎቹ ስደተኞች ሳኡዲአረቢያ ይቆያሉ። የሳኡዲ ባለሥልጣናት ሐምሌ 3 ጀምረው ሐሰሳ በማድረግ ስደተኞቹን ወደ አገር ቤት አስገድደው ይመልሷቸዋል።

በ2006 የሳኡዲ ባለሥልጣናት ተመሳሳይ እርምጃ ሲወስዱ፣ ኢትዮጵያውያን እስከሞት የሚዘልቅ አካላዊ ጥቃት [10] ከደረሰባቸው ውስጥ ነበሩ። ወደ ኢትዮጵያ ሊመለሱ ማቆያ እስር ቤት የታሸጉት ስደተኞች ጥሩ መጠለያና ምግብ አልቀረበላቸውም ነበር።

በ2006ቱ አስገድዶ የመመለስ ዘመቻ ግዜ፣ ኢትዮጵያውያን ማኅበራዊ ሚድያን በመጠቀም ሳኡዲአረቢያ ላይ ያላቸውን ተቃውሞ [11] አስተባብረው ነበር።

ከዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ በተቃራኒ እና የኢትዮጵያ መንግሥት በፍጥነት ተመላሾችን ለማደላደል ከሚሰጠው ቃል በተቃራኒ አገሪቱ ውስጥ ባለው ውሱን የኢኮኖሚ ዕድል ሳቢያ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ የማይፈልጉ ስደተኞችም አሉ።

ሳኡዲአረቢያ የሚኖር ነብዩ ሲራክ የተባለ የማኅበራዊ ሚድያ ላይ ጸሐፊ እንዳሰፈረው [12]:

ጥቃት ሊደርስባቸው እንደሚችል እያወቁ ብዙ ኢትዮጵያውያን ወደ አገር ቤት ለመመለስ ፍላጎት አለማሳየታቸው ያስደነግጣል።

ሠራተኞቹ ስለ ወደፊቱ ሕይወታቸው ሲጨነቁ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሚመለሱ ስደተኞች የመሳፈሪያ ዋጋውን በግማሽ [13] ለመቀነስ እና ከተመለሱ በኋላ ወዲያው በሥራ ለማደላደል ቃል እየገባ ነው። ነገር ግን ቃል ለብዙዎች ይህ የውሸት ቃል ኪዳን ነው።