- Global Voices በአማርኛ - https://am.globalvoices.org -

ኢትዮጵያዊው ተቃዋሚ በፌስቡክ ጽሑፎቹ ሳቢያ ስድስት ዓመት እስር ተፈረደበት

Categories: ከሰሃራ በታች, ኢትዮጵያ, ሰብዓዊ መብቶች, አመጽ, የንግግር ነፃነት, የዜጎች መገናኛ ብዙሐን, ዲጂታል አራማጅነት, 'የዓለም ድምጾች' አድቮኬሲ
[1]

ዮናታን ተስፋዬ። ፎቶ በኢያስፔድ ተስፋዬ (@eyasped) ትዊተር ላይ የተለጠፈ

ይሄ ሳምንት በኢትዮጵያ፣ ሁለት ታዋቂ የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች ገዢውን መንግሥት በመተቸታቸው በፌስቡክ “የማነሳሳት” ክስ ረዘም ያለ የእስር ቅጣት የተጣለባቸው ሳምንት ነው።

ግንቦት 17፣ ዮናታን ተስፋዬ በዘጠኝ የፌስቡክ ጽሑፎቹ መንግሥትን የሚቃወሙ አመፆችን “አነሳስተሃል” በሚል የስድስት ዓመት ከስድስት ወር እስር ቅጣት ብይን ተላልፎበታል።

ሰበር ዜና: የኢትዮጵያ ፌዴራል ፍርድ ቤት የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ዮናታን ተስፋዬ ላይ በሽብር የ6 ዓመት ከ3 ወር የእስር ቅጣት አስተላለፈበት።

ከ2008 ጀምሮ የኢትዮጵያን ገዢ ፓርቲ ያስጨነቀውን ተቃውሞ ተከትሎ፣ የ30 ዓመቱ ይህ የመብቶች አራማጅ ተቃውሞውን በይፋ ሲገልጽ ነበር። ዮናታን በ2008 በገዛ ፈቃዱ ከመሰናበቱ በፊት ለታዋቂው ተቃዋሚ፣ የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ በመሆን አገልግሏል።

ዮናታን የተከሰሰባቸው  ዘጠኝ የፌስቡክ ጽሑፎቹ [6] ለተቃዋሚዎቹ አጋርነትን ከማሳየታቸውም ባሻገር፣ ለግልጽ ውይይት የሚጋብዙ እና ደም አፋሳሽ አመፅ እንዲቆም ጥሪ የሚያደርጉ ነበሩ።

ዮናታን ላይ የቅጣት ብይን ከመተላለፉ አንድ ቀን አስቀድሞ፣ የቀድሞ ባልደረባው ጌታቸው ሽፈራው ላይ በፌስቡክ የውስጥ መስመር በተለዋወጠው መልዕክት ሳቢያ አመፅ ለማነሳሳት በመሞከር የጥፋተኛነት ፍርድ ተላልፏል። የተቃዋሚው ጋዜጣ ነገረ ኢትዮጵያ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጌታቸው የአንድ ዓመት ከስድስት ወር የእስር ቅጣት ተላልፎበታል፦

ሰበር ዜና – የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ላይ እስካሁን የታሰረውን ያህል፣ የ1 ዓመት ከ6 ወር የእስር ቅጣት ብይን አስተላለፈ።

የፌስቡክ መልዕክት ልውውጡ በ2004 የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ሲምፖዚየም ላይ ንግግር ሲያደርጉ የተከሰተባቸውን የማደናቀፍ ገጠመኝ የሚገልጽ ነበር። ጌታቸው በጻፈው መልዕክት ውስጥ “በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳሩ ስለጠበበ፣ ባለሥልጣናቱን በትላልቅ መድረኮች ማደናቀፍ መደበኛ ስልት መሆን አለበት” ብሏል።

እነዚህ እምብዛም ከማይታወቁ ነገር ግን የመሬት መብት ጥበቃ እና ሌሎችም መሠረታዊ መብቶችን ጥየቃ የሚደረጉ ተቃውሞዎችን በአገዛዙ በኃይል የማስቆም ዘመቻ ተጠቂ ከሆኑ ዜጎች ጥቂቶቹ ናቸው። እንደ ሰብኣዊ መብቶች ታዛቢ፣ 800 የፖለቲካ ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ ፖሊስ እጅ ሲገደሉ [10] ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ታስረው፣ የማሰቃየት ተግባር ተፈፅሞባቸዋል።

ፌስቡክ ለመብት አራማጆች – እና ለሕግ ማስከበር – ቁልፍ መሣሪያ ነው

ፌስቡክ እና ሌሎች የማኅበራዊ ሚድያ መድረኮች በኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ተቃዋሚዎች መካከል የመገናኛነት ማዕከላዊ ሚና እየተጫወቱ ነው። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በሚያዝያ 2006 ጀምሮ እስካሁን ለዘለቀው የተቃውሞ ማዕበል ማኅበራዊ ሚዲያን ይወቅሳሉ። በጥቅምት ወር 2009 የታወጀውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ተከትሎ፣ ፌስቡክ በኢትዮጵያ እንዳይታይ ታግዷል። ሆኖም፣ የመብት አራማጆች – እና የሕግ የበላይነት ተቆርቋሪዎች – አቋራጭ መንገዶችን በመጠቀም ፌስቡክ መጠቀማቸውን ቀጥለዋል።

ምንም እንኳ ትክክለኛ ቁጥራቸውን ማወቅ ባይቻልም፣ ብዙ ደርዘን እስረኞች የፌስቡክ ጽሑፍ በመውደዳቸው፣ በመጻፋቸው ወይም በማጋራታቸው ብቻ ለፍርድ እየቀረቡ ነው። ሌሎች ደግሞ ከዳያስፖራ ተቃዋሚዎች ጋር በግል መልዕክት በመለዋወጣቸው ነው የታሰሩት።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እስረኞቹን የፌስቡክ የይለፍ ቃሎቻቸውን በመቀበል የሚመሠርቷቸው ክሶች እየተለመዱ መጥተዋል። አንዳንዴ፣ ዜጎች ምንም ክስ ሳይመሠረትባቸው ይታሰሩና የፌስቡክ የይለፍ ቃላቸውን እንዲሰጡ ተገደው፣ ባለሥልጣናቱ ከብርበራው በሚያገኙት ክስ ይመሠረትባቸዋል።

ፖሊስ የመብት አራማጆችን ካሰረ በኋላ የፌስቡክ የይለፍ ቃላቸውን በመቀበል በሚያደርገው ብርበራ፣ የግል የመልዕክት ልውውጦቻቸውን ጠቅሶ ክስ ይመሠርትባቸዋል።

ጌታቸው “አመፅ የማነሳሳት” ክስ የተመሠረተበት ከታሰረ በኋላ የፌስቡክ የተጠቃሚ ሥሙን እና የይለፍ ቃሉን እንዲሰጥ ከተገደደ በኋላ ነው። የግል የመልዕክት ልውውጡ የክስ ማስረጃ ተደርገው ፍርድ ቤት ቀርበውበታል።

ፍርድ ቤቱ ምንም ወሰነ ምን፣ የዮናታን እና ጌታቸው ወዳጅ ዘመዶች ቁርጣቸውን አውቀው ለቀጣዩ ትግል ለመዘጋጀት ሒደቱ ቶሎ እንዲጠናቀቅ ፈልገዋል። ነገር ግን የፍርድ ሒደቱ፣ እንደሌሎች ብዙ የፍርድ ቤት ሒደቶች ሁሉ ዘግይቷል።

በኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪዎችን የሚያካትቱ የፍርድ ሒደቶች ከሌሎች ጉዳዮች የባሰ ረዥም ጊዜ መውሰዳቸው ያልተለመደ ነገር አይደለም። ይህ፣ ለተከላካዮቹ መሰላቸትን እና ለወዳጆቻቸው መንገላታት መንስዔ ነው።

ዮናታን እና ጌታቸው ፍርዱን ከመቀበላቸው በፊት ሁለቱም በወኅኒ 18 ወራት አሳልፈዋል። ቢያንስ ደርዘን ለሚያህል ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርበዋል። የፌስቡክ ገጾቻቸው በባለሥልጣናት እጅ ወድቀዋል። አንዳንዴ ዳኞቹ ሳይቀርቡ ይቀራሉ፣ አንዳንዴ ደግሞ ፖሊስ እስረኞቹን ሳያቀርብ በመቅረት ጉዳዩ ለ18 ወራት ተንጓትቷል።

ፌስቡክ ለኢትዮጵያ የመብት አራማጆች የሰብኣዊ መብቶች ጥሰትን ለማጋለጥ እና ለመመዝገብ ወሳኝ መድረክ ሆኖላቸዋል። ይህም፣ የዮናታን እና ጌታቸውን ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን አጥንት ድረስ ዘልቆ የሚሰማ እንዲሆን ያደርገዋል።