የኦሮሚያው ተቃውሞ #OromoProtests በተቀሰቀሰ ማግስት ኢትዮጵያ የበይነመረብ ግንኙነትን ቆለፈች

Photo published on EthioTube page titled "Pictures from Oromo Protest - Winter 2015". No attribution or further context appears on the site.

“Pictures from Oromo Protest – Winter 2015″ በሚል ርዕስ ኢትዮቲዩብ ላይ የተለጠፈ ፎቶ፤ ምንም አይነት መለያ ወይም ገለጻ በመካነ ድሩ አይገኝም፡፡

በጥቅምት 2008 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ 75 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው ትንሿ ከተማ ጊንጪ የሚኖሩ ተማሪዎች ሠላማዊ ሰልፍ አካሄዱ፡፡ መቀመጫውን በአሜሪካን ያደረገው የተቃውሞ ሚዲያ አራማጁ ጃዋር መሐመድ በየደቂቃው እየተከታተለ ከ500 ሺሕ በላይ ተከታይ ባለው በጣም ታዋቂው የፌስቡክ ገጹ ስለተቃውሞው መዘገብ ጀመረ፡፡

ተቃውሞው የተጀመረው መንግሥት አዲስ አበባን በዙሪያው ወደሚገኘው የኦሮሚያ እርሻ መሬቶች ለማስፋፋት ያሰበውን ዕቅድ በማይደግፉ አነስተኛ የተማሪዎች ተቃውሞ ነበር፡፡ የኦሮሚያ ክልል በሕገ መንግሥቱ ራሱን ችሎ እንዲተዳደር የተወሰነለት ትልቁ የኢትዮጵያ ክልል ነው፡፡ በኋላ ግን ባለፉት ዐሥር ዓመታት መንግሥት ላይ ከተደረጉ ተቃውሞዎች ትልቁ እና ተከታታይ የሆነ፣ ብዙ ደም የፈሰሰበት፣ በትንሹ 400 ሰዎች የተገደሉበት፣ በርካቶች የቆሰሉበት እና በሺ የሚቆጠሩ ዜጎች ለእስር ወደተዳረጉበት እንቅስቃሴ ተለውጧል፡፡

ጃዋር በፌስቡክ ካሰራጫቸው ስለተቃውሞው የሚገልጹ የቀጥታ ዘገባዎች ጎን ለጎን የበየነ መረብ ተጠቃሚዎች ከኢትዮጵያ የሚመጡ በርካታ ምስሎች፣ ቪዲዮዎች፣ ጦማሮች፣ ትወታዎችን በተለያዩ የማኀበራዊ ሚዲያ ምኅዳሮች አማካኝነት ተመለከቱ፡፡ ብዙዎቹ #OromoProtests  የኦሮሚያ ተቃውሞ የሚለውን መለያ ታርጋ የያዙ ነበሩ፡፡

ከዐሥርት ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ መንግሥት በኦሮሚያ ተቃውሞ የሚያሰሙ ተማሪዎችን በጭካኔ ሲደፈጥጣቸው ቢቆይም እንደ አሁኑ ግን የኢንተርኔቱን ትኩረት አልሳበም ነበር፡፡  በጣም ጥቂት የውጭ ሚድያዎች ዜና አርዕስቶችን እና የአፍቃሬ-መንግሥት ሚዲያዎች ዝምታ እና አሳሳች ዘገባን ተክቶ በይነመረብ ስለ ተቃውሞው መረጃ በማሰራጨት እንደዋና ምንጭነት አገልግሏል፡፡ የጃዋር ፌስቡክ ገጽ እና የትዊተር ቀላቢ ስለተቃውሞው መረጃ የሚሰጥ ኦፊሴል ያልሆነ ኦፊሴላዊ (ይፋዊ ያልሆነ ነገር ግን ይፋዊ ባለሥልጣን) ሆኗል፡፡ ይህም የዳያስፖራ ጸሐፊያን ጃዋርን እንደቁልፍ የኅብረሰተሰቡ አስተሳሰብ እና ክስተቶች ቅርጽ ሰጪ አርገው እንዲወስዱት አድርጓቸዋል፡

ምንም እንኳን እነዚህ የተጣመሩ የተግባቦት ቴክኖሎጂ ውጤቶች በመላው ዓለም የተለመዱ ቢሆንም የበይነመረብ ተደራሽነት ከአምስት በመቶ በታች በሚያንዣብባት ኢትዮጵያ ቅንጦት ናቸው፡፡ ይህ መረጃ ለመጨረሻ ጊዜ እ.ኤ.አ. በ2013 በተባበሩት መንግሥታቱ ዓለምዐቀፍ ቴሌኮሚኒኬሽኖች ኅብረት የተሰበሰበ ነው፡፡

የአሮሞ ተቃውሞ #OromoProtests ያልተቋረጠ ፍሰት መንግሥት የዲጂታል ፍሰቱን ለመገደብ እና ለመዝጋት በርካታ ሙከራዎችን እንዲያደርግ አስገድዶታል፡፡

በትንሹ ላለፉት ሁለት ወራት የማኀበራዊ ሚዲያን የተቃውሞውን ወሬዎች የማጉላት ድርሻ እያደገ መምጣትን ለመግታት እና የበላይነትን ለማግኘት በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኘው ብቸኛው አገልግሎት አቅራቢ ኢትዮቴሌኮም  ትዊተር፣ ፌስቡክ ሜሴንጀር እና ዋትስአፕን ጨምሮ የማኀበራዊ ሚዲያ ምኅዳሮች በኦሮሚያ እንዳይታዩ አግዷል፡፡ በተመሳሳይ ወቅት እንደቫይበር፣ ፌስቡክ ሜሴንጀር፣ ስካይፒ እና ጎግል ሀንጋውት የመሳሰሉ ታዋቂ በኢንተርኔት የሚደረጉ የድምፅ ልውውጦችን (VoIP) ፕሮግራሞችን ማስከፈል እንደሚጀመር አሳውቆ ነበር፡፡

እንደ የአገር ውስጥ ሚዲያዎች ዘገባ ኢትዮቴሌኮም አዲስ የክፍያ መርሐ ግብር መዘርጋት ያቀደው እያንዳንዱ የኢትዮቴልኮምን ኔትዎርክ የሚጠቀም ደንበኛ በሚይዛቸው የስልክ ቀፎዎች ላይ ዳታዎችን የሚቆጣጠሩ እና ምን ምን ዓይነት አፕሊኬሽኖች ቀፎው ላይ እንደተጫኑ የሚገልጹ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም ነው፡፡ በተጨማሪም ኢትዮቴሌኮም ከኢትዮጵያ ገበያ ያልተገዙ ተንቀሳቃሽ የስልክ ቀፎዎችን እንደሚሰልል፣ እንደሚለይ እና እንደሚያግድ አስታውቋል፡፡ ይህ ሒደት አትዮቴሌኮም ምን ዓይነት ሰነድ ከየትኛው ተጠቃሚ ወደየትኛው ተጠቃሚ እንደሚላክ እና እንደሚደርስ በትክክል ማወቅ ያስችለዋል፡፡ እስካሁን ድረስ ይህ ቴክኖሎጂ በትክክል እንዴት እንደሚሠራ ግልጽ አይደለም፡፡ ነገር ግን ያለምንም ማወላወል የኢትዮቴሌኮም ፍላጎት ብቸኛ አገልግሎት ሰጪ መሆኑን ሙሉ በሙሉ ለፖለቲካ ትርፍ እየተጠቀመበት እንደሆነ ያሳያል፡፡

ምንም እንኳን አገሪቱ የበየነ መረብ ስርጭታቸው እጅግ ደካማ ከሆኑባቸው የአፍሪካ አገራት አንዷ ብትሆንም  የኦሮሚያ ተቃውሞ #OromoProtests መቀመጫቸውን አሜሪካ ባደረጉት በተለይ ኦኤምኤን እና ኢሳት የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ሳተላይት ቴሌቪዥኖች ተከታታይ እና ሙሉ ዘገባዎችን አግኘቷል፡፡ ሁለቱም ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ስለአሮሚያ ተቃውሞ #OromoProtests የሚያወሱ ወሬዎችን ከማኀበራዊ ሚዲያዎች በመውሰድ የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት መስተጓጎል ውጪ ለሚኖሩ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መልሰው አሰራጭተዋል፡፡

እነዚህን የተቃውሞ ጫፎች በስኬታማት ለመግታት  ፓርላማው ጥብቅ የኮምፒዩተር ወንጀልን የሚደንገግ፣ ከተቃውሞ ጋር የተያያዙ የመሥመር ላይ ንግግሮችን ወንጀል የሚያደርግ እና ዲጂታል የተግባቦት መሣሪያን ወደ ዜጎችን መሰለያ መሣሪያነት እንዲያገለግል የበለጠ አሟጦ ለመጠቀም የሚያስችል አዋጅ አፅድቋል፡፡

ስለአዲሱ ሕግ ኤሌክትሮኒክ ፍሮንታየር ፋውንዴሽን በሰጠው የሰላ ትችት እንዲህ ብሏል፡፡

Ethiopia's prosecutors have long demonized legitimate uses of technology, claiming in court that the use of encryption, and knowledge of privacy-protecting tools is a sign of support for terrorists….By criminalizing everyday actions it ensures that anyone who speaks online, or supports online free expression, might one day be targeted by the law…. [This regulation] will intimidate ordinary Ethiopian citizens into staying offline, and further alienate Ethiopia's technological progress from its African neighbors and the rest of the world.

የኢትዮጵያ ዐቃብያነ ሕግ ሕጋዊውን ቴክኖሎጂ መጠቀምን፣ መረጃን ሌላ ሰው እንዳያየው መቆለፍን እና የግላዊነት መጠበቂያ መሣሪዎችን የመጠቀም ዕውቀትን ሽብርተኞችን የመደገፍ ምልክት መሆኑን በፍርድ ቤት በመከራከር ማጠልሸት ከጀመሩ ቆይተዋል… የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴን ወንጀል በማድረግ ማንኛውም በበይነመረብ ላይ የተነጋገረ፣ የበይነመረብ ላይ ነጻ ሐሳብን መግለጽን የደገፈ አንድ ቀን የሕጉ ሰለባ እንደሚሆን ያረጋገጠ ነው… [ይህ አዋጅ] ተራ ኢትዮጵያውያን ዜጎች በይነመረብ እንዳይጠቀሙ በማስፈራራት የኢትዮጵያን የቴክኖሎጂ ዕድገት ከጎረቤቶቿ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ብሎም ከቀሪው የዓለም ክፍል የበለጠ በመነጠል ወደኋላ የሚያስቀር ነው፡፡

እንደዘገባዎች አዲሱ አዋጅ የተጣበበው የነበረውን እንደ ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ያሉ ዲጂታል መብቶች የበለጠ የሚያጠብ፣ ወንጀለኛ የሚያደርግ እና ከሥም ማጥፋት ጋር ለተያያዙ የበይነመረብ ላይ ንግግሮች ከባድ ቅጣቶችን የሚጥል ነው፡፡ አዋጁ በተጨማሪ አገልግሎት ሰጪዎች በእነርሱ በኩል የሚያልፍውን ጠቅላላ የመረጃ ልውውጥ ሰንደው በትንሹ ለአንድ ዓመት እንዲያስቀምጡ የሚያስገደድ ነው፡፡

 የግልባል ቮይስን የኢትዮጵያን ኦሮሚያ ተቃውሞ #OromoProtests ያንብቡ

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.