ታንዛኒያዊው ፌስቡክ ላይ ፕሬዜዳንቱን ‘በመሳደቡ’ የሦስት ዓመታት እስር ይጠብቀዋል፡፡

ምስል:- የታንዛንያ ፓርላማ አባል የሆኑት ዚቶ ካበዌ ሩያዋ በትዊተር ያጋሩት (@zittokabwe)

ምስል:- የታንዛንያ ፓርላማ አባል የሆኑት ዚቶ ካበዌ ሩያዋ በትዊተር ያጋሩት (@zittokabwe)

 

የታንዛኒያ ዜጋ የሆነው ይስሃቅ ሐባኩክ ኤሚሊ በፌስቡክ ገጹ የታንዛኒያው ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊን በመሳደብ በአሩሻ ወረዳ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ ተብሏል፡፡

ኤሜሊ ሦስት ዓመታት በእስራት ማሳለፍ ወይም በቅጣት የተጣለበትን አምስት ሚሊዮን የታንዛኒያ ሺሊንግ (2300 የአሜሪካን ዶላር) መክፈል ይጠበቅበታል፡፡ የታንዛንያ አመታዊ የነፍስ ወከፍ ጊቢ ከ1000 የአሜሪካን ዶላር በታች መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህንን የገንዘብ መጠን ክፈል የተባለው የአከባቢው ዜናዎች ምንጭ የሆነው ዘ ሲቲዚን እንደዘገበው የጠበቃው ይግባኝ ተቀባይነት በማግኘቱ ከሰባት ሚሊዮን ሺሊንግ ተቀንሶለት ነው፡፡ ቅጣቱን እስከ ነሐሴ ሁለት መክፈል አሊያም የተወሰነበት እስራት ለመፈጸም ወህኒ መወረዱ ነው፡

በሚያዝያ ሰባት፣ 2008 ዓ.ም. ለመጀመሪያ ጊዜ ፍርድ ቤት የቀረበው ኤሚሊ የሀገሪቱን ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊን ‘በመሳደብ’ በሚል ክስ  የታንዛኒያ የኮምፒዩተር ወንጀልን ለመደንገግ የወጣ አዋጅ  ቁጥር 14፣ 2015 16ኛውን ክፍል በመተላለፍ ተጠርጥሮ ነበር፡፡ አዋጁ እንዲህ ይላል

Any person who publishes information, data or facts presented in a picture, text, symbol or any other form in a computer system where such information, data or fact is false, deceptive, misleading or inaccurate commits an offence, and shall on conviction be liable to a fine not less than three million shillings or to imprisonment for a term not less than six months or to both.

ማንኛውም ሰው መረጃ፣ አሃዝ ወይም እውነታን የሚገልጽ ስእል፣ ጽሁፍ፣ ወይም በማንኛውም መልክ የኮምፒዩተር ሥርዓትን በመጠቀም ካሰራጨ ይህ መረጃ፣ አሃዝ ወይም እውነታን የሚገልጽ ስእል፣ ጽሁፍ ሐሰት፣ የሚያታልል፣ የሚያሳስት ወይም ትክክል ያልሆነ እንደሆነ  ከሦስት ሚሊዮን ሺሊንግ ያላነሰ ገንዘብ ወይም ከስድስት ወራት በማያንስ እስራት ወይንም በሁሉቱም ይቀጣል፡፡

የተከሰሰው ስለ ሀገሪቱ ፕሬዘዳንት የሐሰት ወይም አሳሳች ጽሑፍ መለጠፍ በሕግ የተከለከለ መሆኑን እያወቅክ በመጋቢት አምስት፣ 2007 ዓ.ም. በኪስዋሒሊ ቋንቋ የተጻፈ አነጋጋሪ የፌስቡክ መልዕክት ለጥፈሃል በሚል ነበር፡፡ የእርሱ መልዕክት ያተኮረው በክላውድስ ቲቪ ላይ ወቅታዊ ጉዳዮችን በሚዳስሰው 360 መርሐ ግብር ላይ የፕሬዚዳንት ማጉፉሊን ያልተጠበቀ የስልክ ጥሪ ማድረግ እና በቀጥታ ስርጭት የመርሐ ግብሩን አቅራቢዎች አመስግነው ለመርሐ ግብሩ ያላቸውን አድናቆት መግለጻቸውን መሠረት ያደረገ ነው፡፡

ነገር ግን በፍለጋ የሚገኙት የኤሚሊ የግል የፌስቡክ ገጽም ሆነ መልዕክቱን ለጥፎበታል ተብሎ የተገለጸው የውይይት ገጽ የፌስቡክ አስተያየት እንዲህ ይነበባል፡፡

Hizi siasa za maigizo, halafu mnamfananisha huyu bwege and Nyerere wapi buana.

የፖለቲካ ትያትር [የቀጥታ ስርጭት የስልክ ጥሪውን ለማመልከት]፣ ይህንን ቂል ሰውዬ[ማጉፉሊ] እንዴት ከኒሬሬ [ዋሊሙ ኒሬሬ የታንዛኒያ ተወዳጁ እና የመጀመሪያው ፕሬዚዳንት] ጋር ታወዳድራላችኹ?

የእርሱ ጥፋተኛነት ብይን በታንዛኒያ በአንጻራዊነት አዲስ ሊባል በሚችለው ፓርላማው ከህጻናት ጋር ወሲባዊ ድርጊት በግልጽ ሲፈጽም የሚያሳዩ ውጤቶችን፣ ከኮምፒዩተር መሣሪያና ዳታ አጠቃቀም ጋር የተያያዙ ወንጀሎችን፣ የኤሌክትሮኒክ ማንነት ስርቆትን፣ የስፓም መልእክቶችን፣ ዘረኝነትን  እና በሌላ ሀገር ሰዎች ላይ ጥላቻን የሚሰብኩ የኮምፒዩተር ውጤቶችን፣ ህገወጥ የኮምፒዩተር ዳታ ወይም ኔትዎርክ ደራሽነትን  እና የሐሰት መረጃዎች ህትመትን ለመቆጣጠር በማሰብ  በመጋቢት 23፣ 2007 ዓ.ም. ካጸደቀው  የሳይበር ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ውጤት ነው፡

ምንም እንኳን አዋጁ ከፖለቲከኞች፣ ከማኀበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች እና ከሰብዓዊ መብት አራማጆች ሰፊ ተቃውሞ ቢገጥመውም በአንጻራዊነት ትንሽ ሊባል በሚችል ውይይት እና ክርክር በፓርላማው ጸድቋል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃካያ ኪዌቴም በሰኔ 2007 ዓ.ም. ፈርመው ህግ አድርገውታል፡፡

የሳይበር ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ተቃዋሚዎች ‘ህጉ ያለ በቂ ትርጉም ለፖሊስ፤ህጉን ጥሰዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ቤት እንዲበረብር፣ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችን በቁጥጥር ስር እንዲያውል፣ ከበየነ መረብ አገልግሎት ሰጭዎች ዳታዎቻቸውን እንዲጠይቅ ከልክ ያለፈ ስልጣን ይሰጣል’ ብለው ይከራከራሉ፡፡ በተጨማሪም ፖሊስ ወይም መንግስት ስልጣኑን የመስመር ላይ አራማጆችን ወይንም የማኀበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎችን  ለማጥቃት ሊጠቀምበት ይችላል ብለው አስጠንቅቀው ነበር፡፡

በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. ሁለት ታንዛኒያውያን የአዲሱ ህግ የመጀመሪያ ሰለባዎች ሁነዋል፡፡ የ24 አመቱ የዳሬሰላም ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተማሪ የሆነው ቤኔዲክት አንጄሎ ጎናያኒ  ‘የሐሰት ወይም በተገቢው አካል ያልረተረጋገጡ’ ውጤቶችን በማሰራጨት ተከሶ ነበር፡፡የተጠረጠረው ‘የታንዛኒያ የመከላከያ ኃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ዳቪስ ዋሙያንጌ የተበከለ ምግብ በልተው ሆስፒታል መግባታቸውን’ የሚገልጽ ጽሑፍ ፌስቡክ ላይ በመለጠፍ ነው፡፡

በዚያው ወር ሌላው የበየነመረብ ተጠቃሚ ዜጋ ሶስፒተር ጆናስ የታንዛኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሚዜንጎ  ፒነዳ “መሆን የሚችሉት የወንጌል ሰባኪ ብቻ ነው” የሚል የፌስቡክ መልዕክት ከለጠፈ በኋላ  “በየነመረብን አለአግባብ በመጠቀም”  በሚል ክስ በዶዶማ ክልል በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቧል፡፡

በጥቅምት 2008 ዓ.ም. ለይላ ሲናሬ፣ ጎድፍሬይ ሶካ፣ ዴዎ ሶካ እና ሞኒካ ጋስፓርይ ሶካ  የተባሉ አራት ታንዛኒያውያን ከምርጫ ጋር የተያያዘ የሐሰት መረጃ ዋትስአፕ በተሰኘው ማኀበራዊ የመልዕክት መለዋወጫ ምህዳር አሰራጭተዋል በሚል  የሳይበር ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ 16ኛውን ክፍል በመተላለፍ ተከሰው ነበር፡፡አራቱም በጥቅምት 26፣2008 ዓ.ም. ዳሬ ሰላም በሚገኘው ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡ ዓቃቤ ህግ ተጠርጣሪዎቹ “ሶካ ቡድን” በተባለ የዋትስአፕ ስብስብ በድምጽ መጭበርበር ውንጀላዎች በታወከው  በ2015 ኦክቶበር የታንዛኒያውያን ጠቅላላ ምርጫ ህብረተሰቡን ለማሳሳት በማቀድ የድምጽ መረጃ አሰራጭተዋል በሚል ክሱን አቅርቧል፡፡

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.