ተማሪዎች የዋና ከተማዋን የመስፋፋት ዕቅድ ለምን ይቃወማሉ?

የሀረማያ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ሐዘናቸውን እየገለጹ፡፡ ፎቶው ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጨ ነው፡፡

ባለፉት ሁለት ሳምንታት፣ በኢትዮጵያ ትልቁ የሆነው ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ያሉ ተማሪዎች መንግሥት ዋና ከተማዋ አዲስ አበባን ወደ ኦሮሚያ አካባቢዎች ለማስፋፋት ያወጣውን ዕቅድ እየተቃወሙ ነው፡፡ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት የፀጥታ አባላት የጥይት ተኩስ ሳይቀር ባካተተ ኃይል የተቀላቀለበት መንገድ በሠላማዊ ሁኔታ ተቃውሟቸውን ሲገልጹ የነበሩትን የኦሮሚያ ዩንቨርስቲዎች ተማሪ ሠልፈኞችን በትነዋል፡፡

እንደ ሰብኣዊ መብቶች ታዛቢ ፖሊስ ተቃዋሚዎቹን ለመበተን በወሰደው ያልተመጣጠነ ኃይል ምክንያት፣ በክልሉ ቢያንስ ሦስት ተማሪዎች ሲገደሉ፣ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ተጎድተዋል፡፡ ሌሎች ሪፖርቶች ደግሞ የተገደሉትን ተማሪዎች ቁጥር ዐሥር ያደርሱታል፡፡ ምንም እንኳን ዋነኞቹ ተቃዋሚዎች የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ቢሆኑም፣ የአንደኛ ደረጃ እና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችም ከመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ጋር ውጥረት የተሞላ ፍጥጫ ውስጥ እንደገቡ ተዘግቧል፡፡

በግንቦት 2006 ተነስቶ በነበረው የተመሳሳይ ጉዳይ ተቃውሞ ቢያንስ ዘጠኝ ተማሪዎች በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ተገድለዋል፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰት

ተማሪዎቹ የሚሟገቱት፣ “ማስተር ፕላን” በመባል የሚታወቀው እና አዲስ አበባን ወደኦሮሚያ ክልል ለመለጠጥ የወጣው ዕቅድ ውጤቱ የኦሮሞ ብሔር አባላት የሆኑ ገበሬዎችን በገፍ መፈናቀል ያስከትላል በሚል ነው፡፡

የአንድ ብሔር አባላትን መንግሥት ሲያፈናቅል ይህ የመጀመሪያው አይሆንም፡፡ ተቺዎች “የዘውግ ማጥራት” እያሉ በጠሩት ክስተት በሺሕዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ በ2005 እንዲፈናቀሉ ተገድደው ነበር፡፡

ተማሪዎቹ ኦሮምኛን የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ የማስደረግ ሌላም ፍላጎት አላቸው፡፡ ኦሮምኛ፣ በተናጋሪዎች ብዛት በኢትዮጵያ ወደር የሌለው እና በአፍሪካም አራተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ የኦሮሞ ሕዝብ ቋንቋ ነው፡፡ ነገር ግን የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አልሆነም፡፡

እንደኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት፣ ኦሮሚያበዘውግ ላይ ከተመሠረቱት ዘጠኝ የፖለቲካ ነጻነት ያላቸው የክልል መንግሥታት አንዱ ነው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ በሕዝብ ብዛት በኢትዮጵያ ትልቁ ብሔር ነው፡፡ ይሁን እንጂ፣ የክልሉ ሕዝብ ባለፉት 24 ዓመታት ውስጥ በተቀነባበሩ መገፋቶች እና የመብት ጥሰቶች ውስጥ አልፏል፡፡ እስከ መጋቢት 2006 ድረስ 20,000 የሚገመቱ ኦሮሞ የፖለቲካ እስረኞች በኢትዮጵያ እንደሚገኙ አንዳንድ ግምቶች ያስረዳሉ፡፡

በ2006 ኦሮሚያ ውስጥ ስላለው ጭቆና በማተት የወጣ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል አንድ ሪፖርት እንዲህ ይላል:

በ2002 እና በ2006 መካከል፣ ቢያንስ 5,000 ኦሮሞዎች በሠላማዊ የመንግሥት ተቃውሟቸው ሳቢያ ታስረዋል፡፡ ይህ እንግዲህ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሠላማዊ ሰልፈኞችን እና በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባላቶችን ይጨምራል፡፡ መንግሥት በኦሮሚያ ከፍተኛ ተቃውሞ ስለሚገጥመው የተቃውሞ ጭላንጭሎችን፣ አንዳንዶቹ መታየት ከመጀመራቸው በፊት ይጨፈልቃቸዋል፡፡ ለበርካታ ጊዜያት፣ የተጠረጠሩ ተቃዋሚዎች ክስ ሳይመሰረትባቸው ይታሰራሉ፣ ወይም በእስር ወቅት ወይም በተቃውሞ ሰልፎች ጊዜ በፀጥታ ኃይሎች ይገደላሉ፡

ኢትዮጵያን የሚመሯት ልሒቃን ምንጫቸው በኢትዮጵያ ሰሜን ከምትገኘው ትግራይ ክልል ነው፡፡

ማኅበራዊ ሚዲያ ክፍተቱን እየሞላ ነው

ሌላው ቀርቶ በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ እና የተጋረጠው የምግብ እጥረት ቀውስ በአገር ውስጥ – እና ዓለም ዐቀፍ- ዜናዎች ላይ ርዕስ የመሆናቸው ዕድል ውስን በመሆኑ፣ የተማሪዎቹ ተቃውሞም እንደዚሁ በኢትዮጵያ ሚዲያ ትኩረት አላገኘም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን፣ ከፍተኛ ቁጥጥር ካለበት እና ከመንግሥት የግንኙነት መሠረተ ልማቶች ጥብቅ ገደብ ተሻግሮም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች በተለይም ፌስቡክ ላይ ሁሉንም ነገር ከዳያስፖራ ሚዲያዎች የዜና ሽፋን በተጨማሪ ሪፖርት በማድረግ ክፍተቱን ሞልተዋል፡፡

ይህ ፎቶ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በሰፊው ተሰራጭቶ ከጃዋር መሐመድ የፌስቡክ ገጽ የተወሰደ ነው፡፡

አንድ የፌስቡክ ተጠቃሚ፣ ለምሳሌ፣ የተማሪዎቹን የተቃውሞ መንስኤ ዓለም እንዲሰማለት ተስፋውን ገልጧል:

ዝምታው የውነት ያደነቁራል፡፡ ብዙ ቁጥር ባላቸው ኦሮሞዎች እየተካሄደ ያለውን የሚያነቃቃ ተግባር ማየትና መስማት አለብን፡፡ ታሪካቸውን እንናገር፣ ዓለም በታሪካቸው እንዲጥለቀለቅ ማስቻል አለብን፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሆኖ መንግሥትን የመተቸት ወይም የተቃውሞ ታሪኮችን ሪፖርት የማድረግ ነጻነት ካለመኖሩ አንጻር በዓለም ዙሪያ ያሉ ሰዎች ሊያነቡት እና ዜናውን የቻሉትን በሙሉ በማድረግ ሊያስተጋቡት ይችላሉ፡፡

አጋ ተሾመ የተባለ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ የኦሮሞ ወጣቶች የፖለቲካ አቅምን በተመለከተ የሚከተለውን ዕይታውን አስፍሯል:

…የኦሮሞ ተቃውሞ ሁሉንም የተጨቆኑ የኢትዮጵያ ሕዝቦች በመሬት መቀራመት ላይ ተቃውሟቸውን እንዲያሰሙ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

 

….የኦሮሞ ወጣቶች ተራራ ማንቀጥቀጥ የሚችል አቅም ያላቸው የፖለቲካ አካላት ናቸው፡፡ ይህ አቅም ያለው የፖለቲካ አካል የኢሕአዴግ መንግሥት የሰብኣዊ መብትን ደረጃ እና አግላይ ሥራዎችን የማጋለጥ ሚና ይጫወታል፡፡

ደሱ ተፈራ ደግሞ ይህን ይላል:

ሚዲያዎች እነዚህ ጉዳዩን ለመቃወም በመሞከራቸው የተገደሉ ተማሪዎች የሞቱበትን ሁኔታ መርምረው እንዲያጋልጡ ጥሪ እናደርጋለን፡፡ ኦሮሚያ በዓለም ዐቀፉ ሚዲያ ለድምፅ አልባው፣ ለረዥም ጊዜ የተገደሉ፣ የተንገላቱ፣ የተዘነጉ እና የተጨቆኑ የኦሮሞ ሕዝቦች ድምፅ የሚሆን አዲስ ዓይነት ዘገባ ያስፈልጋታል፡፡ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ገበሬዎችን የሚያፈናቅል፣ ኑሯቸውን የሚያጠፋ እና ማንነታቸውን የሚያንኳስሰውን ይህንን ዕቅድ ይዞ መቀጠል በጣም የሚያሳዝን ነው የሚሆነው፡፡ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ለገበሬዎቹ ጥቅም ሲሉ ነው ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ያስቀመጡት፡፡

ምንም እንኳን ማኅበራዊ ሚዲያዎች ተቃውሞውን በመዘገብ ረገድ ማዕከላዊ ሚና ቢጫወቱም፣ ታዛቢዎች ግጭቱ በምን ምክንያት እንደተከሰተ በማብራራቱ ረገድ ትልቅ ነገር ይጎድላቸዋል፡፡ በተለይም ደግሞ፣ የተማሪዎቹ ተቃውሞ የዘውግ ፖለቲካን እና የከተማ መሬት መቀራመትንም ያዋሀደ መሆኑና የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች በአገር ውስጥ ፖለቲካ ጉዳይ መሳተፋቸው ነገሩ መብራራት እንዲያስፈልገው ያደርጋል፡፡

የኢትዮጵያ ምኅዳር ቁጥጥር የበዛበት ከመሆኑ አንጻር፣ ተማሪዎቹ እንዴት ብሶታቸውን ለመግለጽ ነገሮችን ማስተባበር ቻሉ የሚለው ያጠያይቃል፡፡ ከምኅዳሩ መጥበብ እና ከመሠረተ-ልማቱ በመንግሥት ቁጥጥር ሥር መዋል በላይ ፌስቡክ እና ትዊተር ስለ ተቃውሞው የመረጃ ምንጭ ሆነዋል፡፡

አጠራጣሪ የልማት ሥራ

ጉዳዩ በማያስደስት ሁኔታ የተለመደ ሆኗል፤ ምክንያቱም ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ተመሳሳይ ተቃውሞ ሲከሰት ይህ ሁለተኛው ነው፡፡

በሚያዝ እና ግንቦት 2006፣ ተቃውሞዎቹ የጀመሩት መንግሥት “የአዲስ አበባን የተቀናጀ ማስተር ፕላን” ሊተገብር መሆኑን ተከትሎ ነበር፡፡ አዲስ አበባ፣ በኦሮሚያ የተከበበች ከተማ እንደመሆኗ ተማሪዎቹ መንግሥትን አጎራባች ከተሞችን ከአዲስ አበባ ጋር በማቀናጀት ሥም የገበሬዎችን መሬት ለመቀማት በማሰብ ይከስሱታል፡፡ ተማሪዎቹ በተጨማሪም፣ ማስተር ፕላኑ ተግባር ላይ ከዋለ የኦሮሚያን አካባቢዎች ጠቅልሎ ለመውሰድ ያልማል በሚል መንግሥትን ይወነጅላሉ፡፡

መንግሥት ውንጀላውን የሚያጣጥለው ማስተር ፕላኑ የትራንስፖርት፣ የመዝናኛ እና መሰል የልማት መሠረት ልማቶችን ለመዘርጋት እንዲያስችል የተቀረፀ ነው በማለት ነው፡፡

ተቃውሞው ሲጀምር የተማሪዎቹ ዋነኛ ጥያቄ ማስተር ፕላኑ ሙሉ ለሙሉ ውድቅ መሆን ነበር፡፡ በግንቦት ወር 2006 መንግሥት ቢያንስ በዘጠኝ ሰዎች ሞት እና በመቶዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ ተወላጆች ከታሰሩ በኋላ ፕላኑን ለጊዜው አቋርጦታል፡፡ ነገር ግን ማስተር ፕላኑን በተግባር የማዋል ዕቅዱን መልሶ ለመቀጠል መንግሥት ባለፈው ኅዳር ወር ሲወስን ቁጣው በድጋሚ አገርሽቶ ሁለት ሳምንታት የዘለቀ የተማሪዎች ተቃውሞ በመቀስቀስ ቢያንስ ዐሥር ሰዎች ሞተው ብዙዎች ተጎድተዋል፡፡

በአወዛጋቢ ሁኔታ ከተጠናቀቀው ምርጫ 97 ወዲህ ብዙ ማፈናቀሎችና የከተማ መሬት መቀራመቶች በአዲስ አበባ ተደጋጋሚ ክስተቶች ሆነዋል፡፡ የዋና ከተማዋ ፈጣን ዕድገት የገጠሩን መሬት ለኢንዱስትሪ አገልግሎት፣ ለቤት ሥራ፣ ለመሠረተ ልማትና ሌሎችም የከተማ ፍላጎቶች የማዋሉን ዝንባሌ ጨምሮታል፡፡

ዳያስፖራ አራማጆች ተቃውሞው በአገሪቱ የተንሰራፋው ጠቅላላ ብሶት ውጤት ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት ለጥቂቶች ጥቅም ብዙኃኑን መስዋዕት እያደረገ ነው በማለት ይወነጅሉታል፡፡ ከዚያም አልፎ መንግሥት ሆነ ብሎ ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎችን በአዲስ አበባ ዳርቻዎች በማበረታታት ኋላ ላይ በአካባቢው የሪል ኢስቴት አልሚዎችን እና የጋራ መኖሪያ ቤት ገንቢዎች የሚሠማሩበትን አጋጣሚ ለመፍጠር ይሠራልም ይላሉ፡፡

ኤርሚያስ ለገሰ፣ አሁን የከዳ የመንግሥት ባለሥልጣን ነበር፣ “አዲስ አባባ፤ ባለቤት የሌላት ከተማ” ባለው መጽሐፉ ውስጥ፣ የኦሮሞ ተማሪዎች ተቃውሞን 15 ዓመት ወደኋላ ጀምሮ ያስታውሳል፡፡ በ1993 የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎችን ‹‹ሕጋዊ ዕውቅና›› ከሰጣቸው በኋላ ዕውቅና የተሰጣቸውን ሰፋሪዎች መሬት ለግል የንብረት አልሚዎች መሸጡን ኤርምያስ ጽፏል፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ ብዙዎቹ ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎች መንግሥት እስኪያስነሳቸው ድረስ የተወሰነ ጊዜ ያክል ይኖራሉ፡፡ “አንዳንድ ሕገ-ወጥ ሰፋሪዎች ቡልዶዘሮች መጥተው የቀለሷትን ጎጇቸውን አፈራርሰው ለአዲስ ኢንቨስተሮች ከመሸጣቸው በፊት ማስጠንቀቂያ የሚደርሳቸው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀድሞ ነው፡፡” ይላል ኤርምያስ ከአንድ የዳያስፖራ ሚዲያ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ፡፡

2 አስተያየቶች

  • Assefa

    በእውነት ሁሉንም ነገር አንብቤዋለሁ ፤ የተማሪዎቹም ሆን የሎላው ማህበረሰብ ጥያቄ እውነት ነው፡፡ ያው መንግስት ሆን ብሎ ያሰበው ነገር አለ ፤ ይታወቃልም፡፡ እኔ ሲኤም ሲ ሉቄ አካባቢ 600 ካሬ ሜትር ቦታ ከእነ ቤቱ በዶዘር ፈራርሶ የተቀማሁ ሰው ነኝ፡፡ ለባለ ሃብት ተብሎ ተሰጥቷል (ኔካት ኢንጅነሪንግ) ምንም አይነት ካሳ አልተከፈለንም፡፡ በባዶ ነው ያለነው፡፡ ቦታው ሲኤም ሲ አፓርትመንት ፊት ለፊት ይገኛል፡፡ ፖሊስ ጣቢያው ጀርባ ፤ አሁንም ቀሪ ነበረች ሰሞኑን እንደሚያፈርሷት ነገረውናል፡፡ ሰሚ አጣን ማን አለን፤ ፤፤፤፤
    ባለ ሃብት ከተባለ ፤ ማንኛውም ሰው ሊሰራበት የሚፈለገውን አይነት ስራ ለመስራት ዝግጁ ነኝ ፤ ነገር ግን ለራሳቸው ሰው ነው የሰጡት ፤ ብርም ጉቦ ስለቴቀበሉበት ነው፡፡ ስለዚ ማጭበርበሩ ያለ ነው፡፡ ለሁሉም ጊዜ አለው፡፡ ደግሞኝ ሰልችቶኝ ትቸዋለሁ፡፡
    ቋንቋን በተመለከተ
    ቋንቋን በተመለከተ ግን የቀረበው ነገር የሚያስኬድ አይመስለኝም ፤ ለምን ኦሮምኛ ቋንቋን የሚችለው ሰው ፤ የኦሮሚያ ክልል ተወላጅ ብቻ ይመስለኛል ፤ ሁሉንም ሊያግባባ ዬሚችለው ቋንቋ አማርኛ ይመስለኛል ፤ ደግሞም ነው (አሁን እንኳ እናንተ የፃፋችሁትና የምጽፈው ፤ አማርኛ ስለሆነ ነው) ደቡብም በለው ትግሬው አማራው በለው ጉራጌው ፤ ቤንሻንጉል በለው ጋምቤላው ሁሉም አማርኛን አቀላጥፎ ይጽፋታል ይናገራታልም፡፡ በእርግጥ አማርኛንም ኦሮምኛንም እናድርገው ከተባለ ይቻላል ፤ ደግሞም እንደሱ መሰለኝ ጥያቄያቸው፡፡ ህንድን ወይም ደቡብ አፍሪካን እንዲሁም ሌሎች አገሮችን ብንመለከት ፤ ከአንድ በላይ ብሔራዊ ቋንቋ አላቸው፡፡ ነገር ግን በእኛ አገር ሁኔታ ለጊዜው አማርኛው በቂ ነው እላለሁ፡፡ ዋናው ተናጋሪው ብቻ ሳይሆን ፤ ጻፊውና አንባቢው ምን ያህል ነው የሚለውም መታየት አለበት፡፡

  • […] የተጀመረው መንግሥት አዲስ አበባን በዙሪያው ወደሚገኘው የኦሮሚያ እርሻ መሬቶች ለማስፋፋት ያሰበውን ዕቅድ በማይደግፉ […]

ምላሹን ያጥፉ

ንግግሩን ይቀላቀሉ -> Assefa

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.