ይህ ልጥፍ ከWorld Policy Journal ጦማር ጋር በመተባበር የታተመ ነው።
የአለምአቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ስርዓት የተሰናከለ ነው – እንዲያውም መጀመሪያውኑ ሰርቶ ላያውቅ ይችላል።
በብዙ ጉዳዮች ላይ እንደታየው ከሆነ የዜጎች ሰብዓዊ መብቶች በየአገራቸው ብሔራዊ ህጎች ይጣሳሉ፣ ምንም እንኳ በተባበሩት መንግስታት ሁለገብ አዋጅ (United Nations’ Universal Declaration)፣ እና በአውሮፓ የደህንነት እና የትብብር ድርጅት፣ በየአሜሪካ አገራት ድርጅት፣ በአፍሪካ ኮሚሽን እና በሌሎች ውስጥ ያሉ ቃል የተገባባቸው የአለምአቀፍ ሰብዓዊ መብቶች ቢያካትቱም። የአለምአቀፍ ወንጀል ፍርድ ቤቱ አይን ካወጡት በስተቀር ማንኛውም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ ማድረግ የሚችለው ነገር የለም፣ እና አባል አገራት ፍትህ በመሠላቸው መልኩ የመስጠት ሰፊ ነጻነት አላቸው።
ሐሳብን የመግለጽ መብትን የሚጠብቁ የገዛ ህጎቻቸውን ማክበር ወይም ማስፈጸም ባልቻሉ አገሮች ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች አለምአቀፍ መርሖዎች እውነተኛ መፍትሔ ቢሰጣቸውም ከስንት አንዴ ነው። ዛሬ ዞን ፱ ተብሎ በሚታወቀው ነጻ የኢትዮጵያውያን ጦማሪያን ቡድን ላይ እየሆነ ያለውም ይኸው ነው።
ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ውስጥ የኢትዮጵያ መንግስት ስድስት የዞን ፱ አባላትን ሶስት ቅርበት ካላቸው ጋዜጠኞች ጋር በአዲስ አበባ ውስጥ አስሯል። ምንም ክስ ሳይመሰረትባቸው ለወራት የተያዙ ሲሆኑ ከሌሎች ጋር እንዳይገናኙም ተከልክለዋል። ሐምሌ ላይ ከእስር ቤት የወጣው የበፍቃዱ ኃይሉ ማስታወሻ እና እንዲሁም በፍርድ ቤት ውስጥ የተሰጡ ቃሎች በደል እና ተደጋጋሚ ድብደባዎች እንደደረሰባቸው ያስረዳሉ። እነዚህ ዘጠኝ ሰዎች «የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንደሆኑ ከሚያስመስሉ የውጪ ድርጅቶች ጋር አብሮ በመስራት…በማህበራዊ ገጾች በኩል የሕዝብ አመጽ ለማነሳሳት ገንዘብ ተቀብለዋል» በሚሉ ውንጀላዎች ተይዘዋል።
ሐምሌ ላይ የዞን ፱ እስረኞች መንግስት በይፋ አሸባሪዎች ብሎ ከሰየማቸው የፖለቲካ ተቃዋሚ ድርጅቶች ድጋፍ በመቀበል እና በአለምአቀፍ ተሟጋቾች ታክቲካል ቴክኖሎጂ ኮሌክቲቭ (Tactical Technology Collective) ከተባለው ጋዜጠኞች እና ተሟጋቾች እራሳቸውን ከዲጂታል ክትትል እንዲጠብቁ ከሚያግዛቸው ቡድን በኢሜይል ኢንክሪፕሽን እና ዳታ ሴኩሪቲ ስልጠና በመቀበል በ2001 ኢትዮጵያ ጸረ-ሽብር አዋጅ ተከስሰዋል።
የዞን ፱ ጦማሪያን በቅርብ ጊዜ በነበረው የአረብ አመጾች ላይ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰቱ በሚችሉ ተመሳሳይ አመጾች የዘገበው እስክንድር ነጋን ጨምሮ በተመሳሳይ ህጎች ከተነጣጠሩ ሌሎች የሚዲያ ድምጾች ጋር ተቀላቅለዋል። በቁጥጥር ስር ውሎ በ«ሽብርን በማቀድ፣ ዝግጅት በማድረግ፣ በማሴር፣ በማሳመጽ እና ሙከራ በማድረግ» ተከስሶ የ18 ዓመት እስር ተፈርዶበታል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያደረጓቸው አለምአቀፍ ስሞታዎች በጉዳዩ ላይ ተጽዕኖ አልነበረውም። ግንቦት ላይ የተባበሩት መንግስታት ከፍተኛ ኮሚሽነር ናቪ ፒሌይ እንዲህ ብላ የሚያብራራ ቃል ሰጥታለች፣
በሽብርተኝነት ላይ የሚደረገው ዘመቻ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንን፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አባላትን ለማስፈራራት እና ድምጽ ለማጥፋት እንደ ሰበብ ሆኖ ሊቀርብ አይችልም። እና ደግሞ ከውጪ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ጋር አብሮ መስራት እንደ ወንጀል ተደርጎ ሊቆጠር አይገባም።
በተጨማሪም፣ ሰባት የአለምአቀፍ ሰብዓዊ መብቶች እና የፕሬስ ነጻነት ድርጅቶች በላኩት አስቸኳይ ጥያቄ የአፍሪካ ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግስታት በዞን ፱ ላይ በተከፈተባቸው ጉዳይ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ ጠይቀዋል። ጥያቄው ጉድለት ባለው የክሶቹ ግልጽነት እና ተከሳሾቹ በቂ የህግ ምክር የማግኘት መብት ላይ ያተኮረ ነው።
የሚዲያ ህግ መከላከያ ተነሳሽነት (Media Legal Defence Initiative) ጠበቃ እና የጥያቄው መሪ ፈራሚ የሆነችው ናኒ ጃንሰን በኢሜይል ውስጥ ሁለቱም የአፍሪካ ኮሚሽን እና ተመድ «በእነዚህ ጉዳዮች ቀዳሚ ደረጃዎች ላይ በሚስጥራዊነት ስም ነው የሚሰሩት» ብላ ጽፋለች። እንዲህ ብላ ትቀጥላለች፦
ከአንድ መንግስት ጋር አንድ ጉዳይ ሲከታተሉ የውጪውን ዓለም ሳያሳውቁ ነው። ብዙ ወራት (አብዛኛው ጊዜ ከዓመት በላይ) ካለፉ በኋላ ብቻ ነው ከአንድ መንግስት ጋር የተደረጉት እነዚህ ልውውጦች ለበላይ አካሉ በሚደረገው የእንቅስቃሴ ስልት ሪፖርት ላይ የሚታተመው።
ስለዚህም፣ ማንኛውም ጣልቃ መግባት ዞን ፱ በሚወክለው የድምጽ ማፈኛ ስርዓት ውስጥ ይገባል—ከሕዝባዊ እይታ ወይም ተሳትፎ ተደብቆ።
እነዚያ አካላት ጉዳዩን ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር ቢከታተሉትም እንኳ ያላቸው አማራጭ የተገደበ ነው። በአስቸኳይ ጥያቄው ላይ በጻፈችው ጽሑፍ ጃንሰን የአፍሪካ ኮሚሽን እስራቶቹን በአቋም ማውገዝ እንደሚችሉ፣ የሁለቱም ድርጅቶች ሪፖርት ጸሐፊዎች ምርመራ ለማካሄድ ወደ ኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ጉብኝቶችን እንዲያደርጉ መጠየቅ እንደሚችሉ፣ እና ኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል እንደመሆኗ መጠን እንደዚህ ያለ ጥያቄ የማክበር ግዴታ እንዳለባት አውስታለች። ነገር ግን እንደዚህ ያሉ ጥያቄዎች ቢቀርቡ እና መርመራዎች ቢካሄዱም እንኳ ሊገኙ ይችላሉ ተብሎ የሚገመቱት ውጤቶች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የማስፈጸም ዕድሉ በጣም አነስተኛ ነው።
ጥያቄው ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት በተከሳሾቹ ላይ በክሱ እንደቀጠለበት ነው። በችሎቱ ላይ ያሉ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች ለተከሳሾቹ ቅርብ በሆኑ ወዳጆች በሚሄድ የችሎት መከታተያ ጦማር (Trial Tracker Blog) ላይ ማግኘት ይቻላል።
እንደ የ#Freezone9bloggers የማህበራዊ ሚዲያ ዘመቻ ያሉ የኢትዮጵያ መንግስት በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚፈጽማቸው ጥሰቶችን ይፋ ለማውጣት የሚደረጉ ይፋዊ ጥረቶች ቀጥተኛ ያልሆነ ውጤት ነው ያላቸው። ለእስረኛዎቹ የተሻለ አያያዝ እንዲኖር ለማረጋገጥ የኢትዮጵያ መንግስትን ለማሳፈር ያለሙ ናቸው። እንዲሁም በአለምአቀፍ ድርጅቶች እና እንደ ለኢትዮጵያ መንግስት ወሳኝ የጦር እና የደህንነት አጋር በሆነችው አሜሪካ ያሉ ተባባሪዎች ላይ ጫና ለማሳረፍም ያለሙ ናቸው። ተስፋ የሚደረገው እነዚያ ድርጅቶች በተራቸው ኢትዮጵያ የዞን ፱ ተከሳሾችን ነጻ እንድታወጣ የፖለቲካ ጫና እንዲያሳርፉ ነው።
እንግዲህ በአለምአቀፍ ደረጃ ቃል የተገባባቸውን ነገሮች መተግበር የሚወሰነው እየሰራ እና ተፈጻሚነት ባለው የህግ ስርዓት ሳይሆን በዋነኝነት በድርድር የሚካሄድ የፖለቲካ ሂደት ነው የሚመስለው። ኢትዮጵያ ውስጥ ለፖለቲካዊ ዓላማ ሲባል ህጉ ምን ያህል በቀላሉ ስራ ላይ እንደሚውል ወይም ችላ እንደሚባል ሲታይ ጉዳዩ ለእነሱ እንዲፈታላቸው ያለው ተስፋ ፖለቲካዊ ጫና ብቻ መሆኑ ሲታይ ነገርየው ከባድ ምጸት ነው።