ቋንቋዎች ነጻ ናቸው? የዓለም አቀፉን የአፍመፍቻ ቋንቋ የሚመለከቱ ሐሳቦች

ዛሬ የዓለምአቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን ነው፡፡ ቀኑ በUNESCO አባል አገራት የቋንቋ እና ባሕል ልዩነቶችን እና ብዝኃቋንቋዊነትን ለማበረታታት ይከበራል፡፡ ዕለቱ በተለይም በባንግላዴሽ እ.ኤ.አ. ከ1952 ጀምሮ ‹ኤኩሼ የካቲት› በመባል የሚታወቀው የቋንቋዎች ንቅናቄ ቀንን ዕውቅና ለመስጠት ነው፡፡ ዕለቱ የካቲት 14 (ፌብሩዋሪ 21) ተደርጎ የተመረጠው በባንግላዴሽ (የዛኔዋ ምስራቅ ፓኪስታን) በዕለቱ እ.ኤ.አ. በ1952 በዳካ አመፅ ላይ ሳሉ በጥይት ለተገደሉ ‹የቋንቋ ሰማዕታት› መታሰቢ እንዲሆን በማለት ነው፡፡ ሰማዕታቱ ሰልፍ የወጡት በወቅቱ ለተመሰረተችው አዲሷ ፓኪስታን የሥራ ቋንቋ ከሆነው ኡርዱ ጎን ለጎን ብሔራዊ ቋንቋ ሆኖ የአፍ ቋንቋ መፍቻቸው እንዲመረጥ ነበር፡፡.

Shaheed Minar

ፎቶ:- ሻሒድ ሚናር ጭፍጨፋው በተፈፀመበት ቦታ ላይ የቆመ መታሰቢያ ኀውልት፡፡ ኀውልቱ የባንግላዴሽ ብሔርተኝነት ትዕምርት ነው፡፡

የአፍ መፍቻ ቋንቋ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

አፍ መፍቻ ቋንቋችን ከቋንቋም በላይ ነፍስያችን ነው፡፡ የሰው ልጅ የአዕምሮ አፎት ማለት ነው፤ የታሪክ ማኅደር፡፡ ዓለምን የፈጠርነው በቋንቋ ነው፡፡

ምሩናሊኒ የራሷን አፍ መፍቻ ቋንቋ ተሉጉ አጣቅሳ:-

“ቋንቋዎቻችን ምን ያህ ጣፋጭ እና የሚያኮሩ ናቸው! በአፍ መፍቻ ቋንቋዎቻችን መናገርስ ምን ያህል ነው የሚናፍቀን! በተለይ ትንሽ ራቅ ያልን ጊዜ፡፡”

ሪፖን ኩማር ቢሰዋስ ባንግላዴሽ ዋችዶግ ላይ እንዲህ አለ

“አፍ መፍቻ ቋንቋ የተፈጥሮ ቋንቋ ነው፤ ከተናጋሪው ጋር በጥልቅ ይዋሃዳል ምክንያቱም በአካባቢያዊ ተፈጥሯዊ ሕግጋት የሚማሩት እና የተቀረፀ የግለሰቦች ስብእና የሚገነባበት በመሆኑ ነው፡፡”

ነገር ግን ከዚያም በላይ ነው፡፡ አንድ ሰው በአገሩ አይሆኖርም፤ በቋንቋው ግን ይኖራል፡፡ አገራችን ነው፤ የአባቶቻችን መሬት – ሌላ ምንም አይደለም፡፡”ብሏል ኢ.ኤም. ሲዮራን የተሰኘ ትውልደ ሮማኒያዊ ፈረንሳዊ ፈላስፋ፡፡

ለዚያም ነው ብሔርተኝነት በዓለም ዙሪያ በቋንቋ ላይ መሠረት አድርጎ ሲቀጣጠል የምንመለከተው!

የቋንቋዎች ነጻነት በዓለም ዙሪያ:-

ብዙ ሺሕ የአካባቢ መግባቢያ ቋንቋዎች የትምህርት ስርዓት፣ ብዙኃን መገናኛ፣ ሕትመት እና በጥቅሉ ለሕዝባዊ ግልጋሎቶች የሚውሉበት መንገድ ውስጥ ባብዛኛው በአገረ-መንግሥታት ፖሊሲ ድክመት ሊካተቱ አልቻሉም፡፡ 

በአፍ መፍቻ ቋንቋችን መማር ስንችል የተሻለ ዕውቀት እንቀስማለን (የአፍ መፍቻ ቋንቋ አጣብቂኝ – የዜና ወረቀት)፡፡ ነገር ግን ይህ የብዙዎቹ አናሳ ቋንቋዎች እውነታ አይደለም፡፡ 476 ሚሊዮን የሚሆኑ ትምህርት ያልቀሰሙ ሕዝቦች አናሳ ቋንቋዎችን የሚናገሩ እና  ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው መማር የማይችሉባቸው አገራት ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡

በኢራናዊያን አገዛዝ ከደቡባዊ አዘርባጃን ቤይባክ፣ ለቮይስ ኦቭ ኔሽን ይህን ብሏል:-

የኢራን ፋርስ ባለሥልጣናት እንደ ቱርክ (የኢራን ብዙኃን)፣ አረብ፣ ባሉች፣ ተርክሜን እና ኩርድ ያሉ የሌሎች ብሔረሰቦችን ቋንቋዎች ካገዱ 80 ዓመታት አልፈዋል፡፡ በያመቱ ፌብሩዋሪ 21 በዩኔስኮ የተሰየመውን ሁሉም ብሔረሰቦች የዓለምአቀፍ አፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን ያከብራሉ፡፡ ነገር ግን እንደተለመደው፣ የኢራን ፖሊስ የተሰበሰቡትን ሰዎች ይበትንና ብዙዎችን ያስራል፡፡

ከአምናው ሲነፃፀር ሰፋ ያለ ዝግጅት የዘንድሮውን ፌብሩዋሪ 21 ለማክበር እየተደረገ እንደሆነ ከደቡባዊ አዘርባጃን የመጡ ዜናዎች ያስረዳሉ፡፡ በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ በራሪ ወረቀቶች በአዘርባጃን ዋና ዋና ከተሞች እየተሰራጩ ነው፡፡ በካፒታል ተብሪዝ ዝግጅቱ ተጠናቆ ለሰልፍ ሰዓት ተመርጧል፡፡”

የዩኔስኮው መልዕክተኛ:-

ከብዙ ዓመታት በፊት፣ በሰሜናዊ ጃፓን የሚነገር የኤኑ ቋንቋ በማዕከላዊው መንግሥት ግፊት ሊጠፋ ተቃርቦ ነበር፡፡ በ20ኛው ክፍለዘመን መገባደጃ፣ ይህ ሒደት ተቀለበሰ፡፡ ምንም እንኳን የኤኑ ቋንቋ ቀጣይነት ዋስትና ባይኖረውም መነቃቃቱ ግን የማይካድ ነው፡፡

ሲድ በጽሑፉ ፖለቲካ ላይ አነጣጥሯል፡-

“የዓለምአቀፍ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ቀን በዛምቢያ መከበር አለበት፡፡ አገሪቱ ፖለቲካዊ ውሕደት ለማምጣት እና ለማስቀጠል ብዙ ዓመት ሠርታለች፡፡ ነገር ግን ሌሎች ማኅበረሰቦች የሚማሩበት ፍጥነት ከሌሎች ስለዘገየ – ይህ ብዙ የተከፈለለት ውሕደት አገሪቷን ቤቴ በሚሉ በሌሎች ቋንቋዎ ተናጋሪዎች መስዋዕትነት ከሆነ እጅግ ያሳዝናል፡፡”

የአፍ መፍቻ ቋንቋችሁ እየጠፋ ነው?

የዓለማችን 27 በመቶ ያክል ቋንቋዎች (6000 ስድስት ሺሕ ያህል) ይጠፋሉ የሚል ስጋት አለ፡፡ አደጋ ላይ ያሉ ቋንቋዎች ፋውንዴሽን 83 በመቶ የሚሆኑት ቋንቋዎች አሀዳዊ በሆኑ አገራት ውስጥ በአሃዳዊ መንግሥታት ፖሊሲዎች ተቆልፎባቸው አደጋ ውስጥ ናቸው ብሏል፡፡

አብሂናባ ባሱጂክ ጂያን እንዲህ ብሏል፡-

“በእንግሊዝኛ ቋንቋ አፋቸውን የሚፈቱ ሰዎች በቋንቋው የበላይነት ምክንያት የአፍ መፍቻ ቋንቋን ዋጋ ይዘነጉታል፡፡ ቋንቋቸውን እንደመተማመኛ ይይዙታል፡፡ ሆኖም በየዓመቱ ብዙ ቋንቋዎች ይጠፋሉ፤ የቅርብ ጊዜው የዛሬ አንድ ወር ገደማ የመጨረሻ ተወላጅ ተናጋሪው በነበረችው ማሪ ስሚዝ ጆንስ ሞት ምክንያት የጠፋው እያክ ነው፡፡

እንደሚመስለኝ ሁላችንም የአፍ መፍቻ ቋንቋችንን ለማኖር ካልጣልን ቀስበቀስ ይጠፋሉ፡፡ ቋንቋዎች እንዳይጠፉ አንደኛው በጣም ጠቃሚ መንገድ ቋንቋዎች ከቴክኖሎጂጋ እንዲዋሃዱ ማድረግ ነው፡፡”

ቴክኖሎጂን ለአፍ መፍቻ ቋንቋ አራማጅነት፡-

የዜጎች ብዙኃን መገናኛ ቋንቋዎችን ለማሳደግ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ እንደ ቴክኖራቲ ከ100 ሚሊዮን በላይ ጦማሮች አሉ፡፡ አንድ ያለፈው ዓመት ሪፖርት እንደሚያሳየው 37 በመቶ የሚሆኑት ብሎጎች በጃፓኒኛ፣ ቀጥሎ በእንግሊዝኛ (36 በመቶ)፣ ቻይንኛ (8 በመቶ)፣ ስፓኒሽ (3 በመቶ)፣ ጣሊያንኛ (3 በመቶ)፣ ፖርቹጊዝ (2 በመቶ)፣ ፈረንሳይኛ (2 በመቶ) እና ሌሎችም ናቸው፡፡ እናም፣ ሌሎችም ቋንቋዎች ያሉ ሲሆን እነርሱም እያደጉ ይሄዳሉ፡፡

እንደ ቢሻራት ያሉ የቴክኖሎጂ የለውጥ ማማጫዎች አሉ፡፡ የአፍሪካ ቋንቋ ሶፍትዌሮችን እና የመረብ ግንኙነቶችን ለማጠናከር ይሠራሉሉ፡

ግሎባል ቮይስስ (የዓለም ድምፆች) በይነመረብ ላይ የተለያዩ ቋንቋዎችን ያበረታታል፡፡ የቋንቋ ፕሮጀክቱ ዋናውን የእንግሊዝኛ ገጽ ወደተለያዩ ቋንቋዎች የማስተርጎም ሥራ ይሠራል፡፡. አሁን ይህንን ምሳሌ ሊሆን የሚችል የበይነመረብ መገናኛ ብዙኃን መረጃን ለተለያዩ አገር ሰዎች ለማዳረስ የሚደረገውን ጥረት ሌሎችም ሊከተሉት ይችላሉ፡፡

Thumbnail: UNESCO poster

 

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.