- Global Voices በአማርኛ - https://am.globalvoices.org -

የ‘ወንድም ጋሼ’ አፍሪካዋ ቤቲ ላይ የባሕል እሴት ጥያቄ ተቀሰቀሰባት

Categories: ሴራ ሊዮን, ኢትዮጵያ, ሐሳቦች, ሴቶችና ስርዓተ ጾታ, ታዳጊዎች, የንግግር ነፃነት, ጥበብ እና ባሕል, ፌዝ

የ‘ወንድም ጋሼ’ አፍሪካ (Big Brother Africa) [1]  የተሰኘው የእውነተኛ የኤቴሌቪዥን ትዕይንት የዘንድሮው (እ.ኤ.አ. 2013) ኢትዮጵያዊት ተሳታፊዋ መምህርት ቤቲ (Betty) [2] ከሴራሊዮናዊው ተሳታፊ ቦልት (Bolt) [3] ጋር ወሲብ ፈፅማለች የሚለው ዜና [4] ከወጣ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በሁለት ወገን የጦፈ የባሕል እና የሞራል ጥያቄዎችን በማንሳት እየተሟጎቱ ነው፡፡

ዮሐንስ ሞላ [5] የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ቤቲ አደረገች የተባለው ነገር ፍፁም ከኢትዮጵያዊ የማይጠበቅ ነውር እንደሆነ ለመግለጽ [6] ሞክሯል፡-

‹‹… በመደበኛውና ልማዳዊው አካሄድ ሰውዬው/ሴትዮዋ ላይ፥ ልብ ፈቅዶ፥… ተጣጥቦና ተጣጥኖ፣ ቤት ተገብቶ… ከቤትም መኝታ ቤት ተገብቶ…ከመኝታ ቤትም ደበቅ የሚለውና፥ ግድግዳው ላይ ሽንቁር የሌለው (ቢቻል ከጎረቤት ጋር በቀጥታ የማይዋሰነው) ተመርጦ… ከዚያም በኋላ መብራት ተጠፍቶ…. በጨለማ የሚፈፀም ነው። በዚያም ጨለማውን ሁሉ ፈልቅቆ ገላልጦ፣ ያስረሳልና በነፃነትና በፍፁም መፈቃቀድ ሲፈፀም፥ ‘ወሲብ ብርሃን’ ነው እንላለን። ብርሃንነቱም ከእርካታና ከወንድና ሴት አካላዊ ስምረት ባሻገር የመንፈስ ቅርርብንና ዝምድናን ይፈጥራል። ወዳጆቹ ከተዘጋጁና ለፍሬ ካለው ደግሞ ራሳቸውን ይተኩበታል።

…በእኔ መረዳት ወሲብና ሴሰኝነት በጣም ይለያያሉ። ጤናማ ወሲብ ውስጥ ሴሰኝነት የለም፤ ሴሰኝነት ውስጥ ግን ወሲብ አለ። ወሲብ ማንነትንም ሆነ ማህበረሰብን በማይረብሽ፣ ጤናማና ተፈጥሮአዊ በሆነ መልኩ የሚፈፀምና፣ በውጤቱም ከቅፅበታዊ የስሜት እርካታ ባለፈ የሰው ልጅን የመሰለ ክቡር ኗሪ የሚተካበት የተዋበ መንገድ ነው። ሰው የሚፈበረክበት፣ ሰው የሚሰራበት፣ አብራክ የሚከፈልበት፣ ራስ የሚተካበት… አስደናቂ መንገድ ስለሆነ እንዲሁ የግብር ይውጣ አይደረግም። እንደዚያ ሲደረግ መሴሰን ይባላል። […]

ለእኔ ቤቲ ምጣድ እንደጣደች ሴት ነበረች። ለያውም ለአገር ስም የሚጠበቅ እንጀራ በዓለም ፊት እንድታበስል የተወከለችና እያንዳንዷ እንቅስቃሴዋ ሁሉ በinfrarad ካሜራ እየተቀረፀ፣ “ኢትዮጵያ” የሚል ስም እየተለጠፈበት የሚገመገም። ግን አልገባትም። ወይም አልቻለችበትም። ወይም ጀብድ መስሏታል። እኔን ግን አሸማቀቀችኝ።…››

 

ጁኒየር ዲ [7] የተባለ ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ ደግሞ ከዮሐንስ ሞላ ተቃራኒ የሆነ ሐሳብ አንፀባርቋል [7]፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ኢትዮጵያ የጨዋዎቹም የመረኖቹም አገር ነች፡፡

ቤቲ (ምንጭ:- ቢግ ብራዘር አፍሪካ ድረገጽ)

ቤቲ (ምንጭ:- ቢግ ብራዘር አፍሪካ ድረገጽ)

‹‹…በቢግ ብራዘር አምፕሊፋይድ 2013 ላይ የተሳተፈችው ቤቲ ወሲብ ፈፀመች ተብሎ ወግ አጥባቂዎች ዋይ ዋይ እያሉ ነው:: ለማስታወስ ያህል [ኢትዮጵያ]

* ወግ አጥባቂ ሃይማኖተኞች እንዲሁም መንፈሳውያን ያሉባት ሃገር ብቻ ሳይሆን እነቺቺንያ እና መስቀል ፍላወር ሰፊውን ሕዝብ በወሲብ ንግድ የሚያገለግሉ ጉብሎች ያሉባት ሃገር ናት፣

* ቆሎ እየቆረጠሙ የሚጸልዩ የዋልድባ መነኮሳት ብቻ ሳይሆኑ ዶላር እየቆረጠሙ ራቁት ዳንስ በመሸታ ቤትም ሆነ በግለሰብ አፓርትመንት የሚደንሱ ቆነጃጅት ያሉባት ሃገር ናት፣

[…]

እንግዲህ ሁሉም የዚህች አገር ሰዎች ናቸው:: እየመረጡ መኩራት እየመረጡ ማፈር አይቻልም:: ቤቲ የሰንበት ተማሪዎችን ወክላ አይደለም የሄደችው:: እራሷን ሆና ነው:: መብላት መጠጣት ጤነኛ ሰው ሁሉ የሚያደርገውን ነገር ማድረግ ነው የሾዉ ዓላማ:: በቤቲ አፈርን የምትሉ ሁሉ ምክንያታችሁን ጠይቁ:: ሕፀፅ ይበዛዋል ብይናችሁ፡፡››

 

ኃይሉ ጌታቸው [8] የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ በበኩሉ ቤቲ ኢትዮጵያን ትወክላለች በሚል ‹‹የወግ አጥባቂዎች›› ክርክር ልጅቷ ላይ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስ ያለውን ስጋት ገልጽዋል [9]፡-

‹‹ቤቲ ኢትዮጵያ ውስጥ የተወለድች ግለሰብ ነች እንጂ ኢትዮጵያ ቤቲ ውስጥ አልተፀነሰችም!
ከዓመታት በፊት በምድረ ፒያዛ፣ ጥንዶቹ ወጣቶች እንደቀልድ ራሳቸውን በወሲብ ውስጥ በሞባይል ቀድተው እንደሰደድ እሳት የተዛመተው ምስል አሳዛኝ ታሪክ አስከትሎ አልፏል። ልጅቷ በአካባቢው ማኅበረሰብ የደረሰባትን ጫና መሸከም አቅቷት እራሷን አጠፋች። አሁንም big brother afirca ላይ እየተሳተፈች ባለችው በቤቲ ላይ እየትሰነዘረ ያለው የሞት ገመድ በእሷ ዙሪያ ብዙዎችን ሊጠልፍ ይችላል።የኢትዮጵያ ወግ አጥባቂ ነኝ ባዮች፣ መለኮስ እንጂ ማጥፋቱን የሚያውቁበት አልመስልህ ብሎኛል፡፡ ይሄ ቁልል ፊደል ሊገመድ እንደሚችል መረዳት መቻል አለብን።

ዓለም ስትታመስ እና የብዙዎች ነፍስ እንደ ገለባ ብን ብሎ የረገፈው፣ እየረገፈም ያለው በነዚህ ወግ አጥባቂ ነን ባዮች እሳቤ ምክንያት ነው። ምክንያቱም መሠረታቸው ሰፊው ደንቆሮ ሕዝብ እና ረዥም ምላሳቸው ነው!››

 

ፀዲ ለማ [10] የተባለች ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ በሰጠችው አስተያየት [11] ደግሞ በግለሰቦች ጉዳይ ላይ የምሁራዊ ውይይት ብስለት እንደሚያንሰን ጠቁማለች፡-

‹‹የቤቲ ስብራት (The Betty fiasco): አሁንም የግለሰቦች ግላዊ ምርጫ ብሔራዊ ውክልና ይኑረው አይኑረው በሚለው ጉዳይ ላይ ምሁራዊ ሥነ-ምግባራችን ጎዶሎነቱ ነው የታየው፡፡  ቤቲ፣ ራሷን ነው የሆነችው፤ በዚያ ላይ ቤቲ ማለት የራሳቸውን ምርጫ በየዕለቱ ሰከንዶች የሚፈቅዱ ሌሎች ሚሊዮንን ሴቶች ማለት ነች፡፡ ጥያቄው ‹ለምን ቤቲ የወል እሴቶቻችንን እንድትበይንልን ፈለግን?› የሚለው ነው፡፡ ለምንስ ድርጊቷን (እኔም ራሴን በማልበይንበት፣ ነገር ግን የግሏ ነው ብዬ የምተወውን ድርጊቷን) እንደ አንዲት ወጣት፣ በትዕይንቱ ላይ ለመሳተፍ እንደፈቀደች አፍላ ሴት – ሰው የመሆንን ድንበር እስከ የመጨረሻው የምንዱባን ጥግ ድረስ ለመግፋት እንደሞከረች ሴት ለምን አንወስዳትም?››

መማር ዘላለም [12] በሚል የፌስቡክ ተጠቃሚ ስም የሚታወቅ ሰው ግን ቤቲ ኢትዮጵያን አልወከለችም በሚለው አይስማማም፡፡ ነገር ግን ተመልሳ ወደአገር ቤት ስትመጣ ሊደርስባት ስለሚችለው መገለል ከወዲሁ መስጋቱን ገልጧል [13]፡፡ እስካሁን እየተሰነዘረባት ያለው ትችትም ተገቢ እንዳልሆነ ተከራክሯል፡-

‹‹…ቤቲ የፈጸመችው ድርጊት ምቾት አልሰጠኝም፣ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ወክላ ሄደችም/አልሄደችም፤ ማንኛውም ሰው በየሄደበት ሀገር በተዘዋዋሪም ቢሆን የሀገሩ አምባሳደር ነው ብየ ስለማምን፡፡ ከዚህም ባሻገር በትልቅ የቲቪ ሚዲያ የኢትዮጵያን ባንዲራ ለብሳ ኢንተርቪው ስታደርግ ነበር፣ ጋዜጠኞችም፣ ተመልካቾቹም ሲጠሯት ‹Betty from Ethiopia› እያሉ መሆኑም ልብ ይሏል፡፡ ስለዚህ የምር ለመናገር ተሸማቅቂያለሁ፤ እንዲያውም አሁን እማ ብታዩኝ ተሸማቅቄ… ተሸማቅቄ አውራ ጣት አክያለሁ… አብዛኛው ሰውም እንደኔ ደብሮታል፤ አዎ ቤቲ ይህን ማድረግ አልነበረባትም፡፡ ይህን ነገር የማድረግ መብቷን ግን ፈፅሞ ልጋፋት አልችልም፤ መብቷን አከብራለሁ፡፡ ሆኖም ግን ይቺ ልጅ በጣም አሳዘነችኝ ክፉኛ በሐበሻ አፍ ውስጥ ገብታለች፤ ወደሀገሯ በተመለሰች ጊዜ የሚገጥማት ወሬና ግልምጫ ሳስበው የእውነት አዘንኩላት፤ በወሬ አመድ ማድረግ የሚችል ጀግና ሕዝብ እኮ ነው ያለኝ፡፡ እኔ ግን ይቺ ልጅ ከዚህ ቀደም ጓደኛዬ፣ አብሮ አደጌ፣ የሥራ ባለደረባዬ ሁና ቢሆን ኖሮ ከዚህ ቀደም እሰጣት ከነበረው ፍቅር ቅንጣት ታክል አልቀንስባትም፡፡ አሁንም ቢሆን መንገድ ላይ ድንገት ባገኛት ዘወር ብዬ ላላያት ቃል እገባለሁ… ባአካባቢዬም አየሃት ቤቲን? ያቸውልህ እያት… የሚለኝ ሰው ካለም ጆሮውን እቆነጥጠዋለሁ፡፡ ሰዎች፣ እኛ እሷን እንዲህ የመተቸት መብት እንዳለን ሁሉ እሷም እንዲህ የማድረግ መብት እንዳላት አትዘንጉ፣ … ሁሉም ሙጫ ሙጫ አምባገንን ነው እኮ በየቤቱ፤ በስመ ወግ ባሕላችን ተነካብን ብለን የማንንም መብት መጋፋት አንችልም፡፡ እናንተ እንዲህ ከሆናችሁ ከጋሽ መንግሥቴ በምን ትሻላችሁ? መንግሥቴ እኮ በምንም በምንም ሰበብ ነው መብቴን እየተጋፋው ያለው፡፡››

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ በማጣቀስ ቤቲ ላይ እየደረሰባት ያለው ውግዘት ከተመሳሳይ ድርጊት ነጻ በሆኑ ሰዎች እንዳልሆነ የተከራከረች [14]ው ደግሞ ሕይወት ወንድማገኝ [15] የተባለች ሌላ የፌስቡክ ተጠቃሚ ነች፡-

‹‹በጣም ከምወዳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ውስጥ በዝሙት ምክንያት በድንጋይ እንድትወገር የተፈረደባትን ሴት ኢየሱስ ‹‹ከናንተ ኃጢያት የሌለበት እሱ የመጀመሪያውን ድንጋይ ይወርውርባት›› ብሎ አድኗታል፡፡ እውነትም፣ ማንም እጁን አላነሳባትም፡፡

እኔ ሌሎቻችንም ይህንን ሐሳብ በሌሎች ላይ ከመፍረዳችን በፊት እንድናስብበት እመኛለሁ፡፡››

 

ሌሎች ደግሞ ችግሩ ያለው ከቤቲም ከተቺዎችም ሳይሆን ከስርዓቶች እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ የፀረ-ሉል ሴራ የተሰኘ ጦማር የ‹ወንድም ጋሼ አፍሪካ› ፕሮግራም ራሱ ሰብኣዊነትን ለማጥፋት የተዘጋጀ [16] ነው ሲል፤ ሲስ ሒው [17] የተባለ ሰው ደግሞ በአገር ውስት ባሕላዊ እሴቶቻችንን የሚያበረታታ ነገር እንደሌለ የታዘበውን አስፍሯል [18]፡-

‹‹…ትርኢቱ እጅግ ጋጠወጥ ሲሆን በተለያየ ዘመን ባቀረባቸው ትርኢቶች የተለያዩ ለፕሮግራሙ በከፍተኛ ወጪ ማስተዋወቅያ እንደሚነገርለት ሳይሆን ክብረ ነክ የሆኑ ድርጊቶች፣ እራቁት መታየት፣ ስካር፣ ወንዶችና ሴቶች እራቁታቸውን ፍል ውሃ ውስጥ ተዘፍዝፎ መታየትና አብሮ መታጠብ ወዘተ. የተለመዱት ናቸው፡፡ ይህ እንዲሁ ሁኖ የአገራችን ኤፍ ኤም ሬድዮ ፕሮግራሞች በሚከፈላቸው ዳጎስ ያለ ገንዘብ ስለ ፕሮግራሙ ጥሩ ማውራት እንጀራቸው ነው፡፡ አክብረን አንብበን ወዳጆቻችንም እንዲያነቡ የምንመክራቸው የህትመት ውጤቶችም ስለዚህ ክብረ ቢስ ፕሮግራም በተከበረው ወረቀቶቻቸው ላይ ውደሳ ያጎርፉለታል፡፡ ከዚህ በፊት ባለማወቅ ከሆነ እንዲህ የተደረገው ለቀጣይ ፕሮግራሙ በኢትዮጵያ ደረጃ እንዲታገድ አበርትተው እንዲታገሉ እንጠይቃለን፣ እንዲህ ካልሆነ ግን በአንባቢው ዘንድ ክብርን እንዳይጠብቁ እንንገራቸው፡፡ ክብረ ቢስ ድርጊቶች በሚከበሩ ሚድያዎች መገኘት የለባቸውምና፡፡ ሁሉም የየራሱ ቦታ አለው፡፡ የዚህ ትርኢት አደጋም አለክብሩና አለቦታው መቀመጥ መቻሉ ነው፡፡

እንዲህ የመሰሉ የእውነተኛ ክስተቶች ትርኢት ወይም ሪያሊቲ ሾው ግማሽ  ክ/ዘመን በላይ እድሜ ያስቆጠሩ ሲሆን ከሁሉ አነጋጋሪው ይህ ዓለም አቀፋዊው ወንድም ጋሼ  የተሰኘው ሪያሊቲ ሾው ነው፡፡ ሪያሊቲ ሾው ለፕሮፖጋንዳ የተመቸ ነው፣ ማሸነፍ ከፈለጉ የትርኢቱ መሪ ፍልስፍናዎችን ማንጸባረቅ ይጠበቅባቸዋልና ተወዳዳሪዎቹ ለዚህ ሲሉ የማይሆኑት ነገር የለም፡፡…››

 

‹‹…ሚዲያዎቻችንን፣ ዩንቨርስቲዎቻችንን፣ ትምህርት ቤቶቻችንን፣ የትምህርት ሥርዓታችንን፣ እና የትምህርት መሣሪያዎቻችንን ተመልከቱ፤ የትኞቹ ናቸው ባሕላዊ እሴቶቻችንን እና ቅርሶቻችንን እንድናከብር የሚያስተምሩን? ወጣቱ ትውልድ ቤቲ እና ሃኒ የሚያደርጉትን ነገር ያደንቃል፡፡ ፖለቲከኞቻችን ሳይቀሩ የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግን እና የሆሊዉድ ፊልምን እየተከታተሉ ስለ ማኅበራዊ እሴቶች እና መብቶች ከማይጠይቁዋቸውጋ ነው የሚወግኑት፡፡…››

ሌሎች ደግሞ ቤቲ ወደቀጣዩ ዙር እንዳታልፍ ካሁኑ የፌስቡክ ገጽ [19] ከፍተው ቅስቀሳውን ጀምረዋል፡፡