የበይነመረብ ዘመቻ በኢትዮጵያ ስለ ሰላማዊ ሰልፍ እና ዴሞክራሲ

ዞን ዘጠኝ ተብሎ በሚጠራው የጦማሪዎች እና አራማጆች ኢ-መደበኛ ቡድን አስጀማሪነት በርካታ የኢትዮጵያ ማኅበራዊ አውታር ተጠቃሚዎች ከሚያዝያ 30 እስከ ግንቦት 2/2005 ድረስ የዘለቀ የበይነመረብ ዘመቻ አድርገው ነበር (የዘመቻው ጋዜጣዊ መግለጫ እዚህ አለ)፡፡ ዘመቻው ለቡድኑ ሦስተኛው ሲሆን፣ ‹‹ዴሞክራሲን በተግባር እናውል፤ የሰላማዊ ሰልፍ መብት ይመለስ›› የሚል መሪ ቃል ላይ ተንተርሶ መንግሥት ‹‹በቀጥታና በተዘዋዋሪ›› እያደረገው ነው የተባለውን እገዳ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የተፈቀደውን ‹‹ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ፣ የመሰብሰብና አቤቱታ የማቅረብ መብት›› ራሱ መንግሥት እንዲያከብረው የሚጠይቅ ዘመቻ ነበር፡፡ በዘመቻው የተለያዩ ጦማሮች የተጻፉ ሲሆን፣ በተወሰኑ ሰዓቶች ልዩነት አብዛኛው የዘመቻው ተሳታፊ የሚያጋራቸው አጫጭር ጽሑፎች ተለጥፈዋል፣ ተሳታፊዎች ለዘመቻው የተዘጋጀውን የፕሮፋይል ምስል እንዲቀይሩ ተጋብዘው እንደተጠየቁት አድርገዋል፣ የዘመቻውን ሒደት እንዲከታተሉ የዘመቻው የኹነት ገጽ ተፈጥሯል፣ ባለፉት ዓመታት ውስጥ የተከለከሉ ሰልፎች የጊዜ መሥመር ተዘጋጅቶ ታትሟል፤ በተጨማሪም በአንድ ደቂቃ ተኩል ቪዲዮ መብቱ ለዜጎች እንዲከበር ተጠይቋል፡፡ ከፌስቡክ በተጨማሪም በትዊተር ላይ #Demonstration4Every1 እና #Assembly4Every1 በሚሉ ኃይለ ቃሎች ተሳታፊዎች ሐሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

በአስተባበሪዎቹ ተሰናድተው ተሳታፊዎች ካሰራጯቸው ጽሑፎች መካከል የሚከተሉት ይገኛሉ፡፡

ስላልተጻፈው ሕግ አስቸጋሪነት፡-

ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ መብት እንደ አብዛኛዎቹ ዴሞክራሲያዊ አገሮች ሕገ መንግሥቱ ላይ መቀመጡ መልካም ነው። አፈፃፀሙም፣ ለክልሉ መስደተዳድር በማሳወቅ መሆኑ (በማስፈቀድ አለመሆኑ) ጥሩ ነው። ፖሊስ ለሰልፈኞቹ ደህንነት በሰልፉ ቦታም መገኘቱ ተገቢ ነው።

ችግሩ ያልተጻፈው ሕግ ተግባራዊ ሲሆን ነው። ችግሩ ፖሊስ ሰልፈኞቹን ለመጠበቅ ሳይሆን ለመበተን ሲወጣ ነው። ችግሩ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች ሰልፉን ለመበጥበጥ ሲሰማሩ ነው። ችግሩ የመሰብሰቢያ አዳራሾች ስብሰባዎችን በመፍቀዳቸው የንግድ ሥራዎቻቸውን የሚያውክ ችግር ሲሴርባቸው ነው። ችግሩ ሰልፈኞች በቆመጥ መደብደባቸው፣ መታሰራቸው እና መገደላቸው ነው።

ያልተጻፈው ሕግ ተሽሮ የተጻፈው ሕግ ይተግበር። ዴሞክራሲን በተግባር እናውል፣ የሰላማዊ ሰልፍ መብት ይመለስ!

መብት ይመለስ ስለማለት አስፈላጊነትና ትርጉም፡-Profile4

የሰላማዊ ሰልፍ መብታችን ይመለስ ስንል ምን ማለታችን ነው? መብት ተፈጥሮ የሚያድለን በመሆኑ መብቱን የሚቀሙን ይኖራሉ እንጂ የሚሰጡን አይኖሩም፣ ስንቀማ ይመለስልን ብለን እንጠይቃለን። ይህን ከምናደርግባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ራሱ ሰላማዊ ሰልፍ ነው።…

ስለሙሉ መብት መከበር፡-

[ዞን ዘጠኝ] እባላለሁ። አገሬ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓቷ ከዓመት ዓመት እየተሻሻለ እንዲሄድ እፈልጋለሁ፣ መብቴ ተቀናንሶ ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ እንዲጠበቅልኝ እፈልጋለሁ፣ ዜጎች ብሶት ሲኖርባቸው ብሶታቸውን ለመንግሥት ለመግለጽ የሚያስችላቸው የሰላማዊ ሰልፍ መብታቸውና ለችግሮቻቸው መፍትሔ ፍለጋ በጋራ ለመምከር የሚያስችላቸው የመሰብሰብ መብት እንዲከበርላቸው እፈልጋለሁ። ስለዚህም እላለሁ፡- የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ይከበር። ዴሞክራሲን በተግባር እናውል፣ የሰላማዊ ሰልፍ መብታችን ይመለስ!

ለምን መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ[en]፡-

Why I believe I have the right to Assemble and Associate?

I, [Kirubel Teshome], believe everyone is different and everyone has her or his own views. I believe, people should be able to get together to express their common opinion. I also believe honest dissent and associations should not be confused with disloyal subversion that would try to overturn the constitutional order. Such peaceful assemblies is one of the most important element to pave the way to democracy that is why I believe everyone has the right to participate in peaceful assemblies and peaceably demonstrate by way law enforcements should not violate the anyone’s right to do so.

ለምን የመሰብሰብና የመደራጀት መብት አለኝ ብዬ አስባለሁ?

እኔ፣ [ክሩቤል ተሾመ]፣ ሁሉም ሰው የተለየ እና ሁሉም ሰው የራሱ የሆነ አመለካከት አለው ብዬ አምናለሁ፡፡ ሰዎች፣ የጋራ አስተያየታቸውን መግለጽ እንዲችሉ አብረው መሆን መቻል አለባቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ግልጽ ተቃውሞና መደራጀት ከአማፂነት እና ሕገ መንግሥቱን ለመናድ ከሚደረጉ ጥረቶች ጋር መምታታት የለበትም ብዬ አምናለሁ፡፡ እንዲህ ዓይነት ስብሰባዎች ለዴሞክራሲ መንገድ ይጠርጋሉ ብዬ አምናለሁ፤ ለዚያም ነው ሁሉም ሰው በሰላማዊ ስብሰባዎች እና ሰላማዊ ሰልፎች የመሳተፍ መብቱ የሌላውን መብት እስካልተጋፋ ድረስ ሊከበርለት ይገባል ብዬ የማምነው፡፡

መሪዎች በዴሞክራሲ እንዲታወሱ ስለመጋበዝ፡-

መሪዎች ይመጣሉ፣ መሪዎች ይሄዳሉ። መሪዎች በሠሩት ሥራ ይታወሳሉ። በአገራችን ዴሞክራሲን በተግባር ማዋል እስካሁን መሪዎቻችንን እንደከበዳቸው ነው። በዴሞክራሲ ውስጥ ግልጽነት አለ፣ ግልጽ መንግሥታት ደግሞ ከሕዝባቸው የሚደብቁት ሕዝባቸውም የሚደብቃቸው ስለማይኖር ሰላማዊ ሰልፍ አይፈሩም። ሰላማዊ ሰልፍንና የመሰብሰብ ነጻነትን መንፈግ የኢዴሞክራሲያዊ መንግሥታት ባሕሪ ነው። ዴሞክራሲን እንጀምረው፣ እንለማመደው ከዚያም እንካንበታለን። ለዴሞክራሲ እንትጋ፣ እንሰብሰብና እንምከርበት፡፡ የመሰብሰብ መብታችን ይከበር፡፡የሰላማዊ ሰልፍ መብታችንም ይመለስ!

ስለሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ ጤናማ አስተሳሰብነት፡-

ሰላማዊ ሰልፍ በጤናማ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ የሚኖሩ ጤናማ ፍላጎት ያላቸው ዜጎች ብሶታቸውን የሚገልጹበት፣ መንግሥት ድምጻቸውን ሰምቶ ችግራቸውን የሚቀርፍበትን መፍትሔ እንዲያመጣ የሚያሳስቡበት ጤናማ መንገድ ነው። መንግሥታት ሰላማዊ ሰልፍን በማገድ ለዜጎቻቸው የሚያስተላልፉት መልዕክት ድምጻቸውን መስማት እንደማይፈልጉ፣ የሚመሩትን ሕዝብ ፍላጎት ሳይሆን የራሳቸውን የልብ ትርታ ብቻ እንደሚያዳምጡ እና ለሕዝባቸው ግዴለሽ መሆናቸውን ነው። በተለይ በኛ አገር አማራጭ ድምጾችን የሚያሰማ የፓርላማ አባል በሌለበት ሰላማዊ ሰልፍን መከልከል፣ ለመንግሥት ችግሮችን የሚሰማበትን ዕድል ያጠበዋል። ሰላማዊ ሰልፍን ማፈን፣ ዜጎች ስለመንግሥታቸው የሚያስቡትን ከማወቅ ያግዳል፡፡

ለመደማመጥ፣ ዴሞክራሲን በተግባር እናውል – የሰላማዊ ሰልፍ መብታችን ይመለስ!

 https://www.youtube.com/watch?v=S-Cw5RMok08

ከነዚህና ሌሎችም በተጨማሪ ተሳታፊዎች በራሳቸው እና የቡድኑ አባላትም ረዘም ያሉ ጦማሮችን ጽፈዋል፡፡ ማስረሻ ማሞ የተባለ የቀድሞው አዲስ ነገር ጋዜጣ ጋዜጠኛ እና የማኅበራዊ አውታር ተጠቃሚ ‹ኢትዮጵያዊ እንደመኾኔ ይህን ልነፈግ አይገባም!› በሚል ርዕስ የጻፈው ጦማር ላይ የሚከተለውን ብሏል፡-

…እኔ እሱ [በአንቀጽ 30 የተደነገገው] መብት በትክክል በኢትዮጵያ ውስጥ ይሠራል ብዬ እንዳስብ የኾንኩባቸው ሁለት ልዩ ቀናት ነበሩ። ሚያዝያ 29 እና ሚያዝያ 30።

ሚያዝያ 29 እኔን ብቻ ሳይኾን የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጭምር በመድረክ ላይ እንደ ሕጻን ልጅ አስቦርቋቸዋል። ከሕዝቡ ካልተቀላቀልኹ ብለው እስከማስቸገርም ደርሰው ነበር። “ይኼ የሕዝብ ማዕበል እያለ ነው እኛ ምርጫ የምናጭበረብረው?” አስባላቸው። እኔም ያንን ሲሉ አልፈረድኩባቸውም፤ ምንም እንኳ በ30 ብር ተገዝቶ የመጣ ሕዝብ የተሰለፈበት መኾኑን ባውቅም። ነገር ግን ስሜታቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ድረስ እንዲያ ያቅበጠበጣቸው ሰልፍ በ30 ብር ተገዛም አልተገዛም አስፈላጊ ነበር። መብት በብር ተግዝቶ ለሰላማዊ ሰልፍ ፍጆታ ሲውል እና ሳይውል ያለውን ልዩነት አጉልቶ ስለሚያሳይ።

በሚያዚያ 29 ሰልፍ አፌ ተከፍቶ ሳይዘጋ ሱናሚው በአንድ ቀን አዳር ተከሰተ። አሁን እንኳን ውጡልኝ ብሎ ብር የሚከፍል ቀርቶ በአግባቡ አደራጅቶ የሚመራ ኃይል የለም። በዚያ ላይ ማዕበሉ ለትንበያም የሚመች አልኾነም። በሚያዝያ 29 “አንተ እኮ ማዕበል ነህ” ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሞካሸው ሰላማዊ ሰልፈኛ “ይቺ ይቺን ለእኛ፣ ጥሬ ጥሬዋን ለጌኛ” የምትለዋን እያብሰለሰለ አድሮ “እኔ አንተ እንደምታስበኝ እና እንደምትገምተኝ ማዕበል አይደለኹም፤ ስፈልግ በርግጥ እኾናለሁ፤ ነገር ግን ዛሬ ማዕበል ብመስልህም፤ እውነተኛው ማንነቴ ሱናሚ ነው፤” ብሎ ከእውነተኛ የሰላማዊ ሰልፈኛ የሚጠበቅ ተግባሩን በጨዋነት አሳይቶ ተመለሰ። አውሎ ነፋስ የቀላቀለ እና ዶፍ ያጥለቀለቀው ሰላማዊ ዝናም ኾኖ።

አሁን አፌ ተዘግቷል። መደነቄንም አቁሚያለኹ። ግን እውን እና ሕልም መለየት እንዳቃተው በሕልሙ እንደሚጓዝ እንቅልፋም ደግሜ ደግሜ ጥያቄውን ለጓደኞቼ እያቀረብኩ ነበር። “እውን ነው፤ አትጃጃል” አሉኝ። ግን ይህ ሁሉ ሕዝብ ያለ በቂ ቅስቀሳ እና ያለ ክፍያ እንዴት ሊወጣ ቻለ? በአንድ ሐሳብ ተስማምቶ ያለምንም ችግር ለመመለስ የሚያስቸለውን ምክር በየቤቱ ለመወሰን የሚያችል ምን አጋጣሚስ ተገኘ? ይህን ዓይነቱን አስደናቂ ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግስ ምን ያህል ጥርነፋ እና አደረጃጀቶች ተከናወኑ? ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ መስጠት የሚችል ምንም ኀይል የለም። መልሱ የነጻነት ናፍቆት ነው፤ ለረጅም ዘመን የታመቀ እና በዝምታ ተውጦ የከረመ ድምጽ የሚሰማበት ሰላማዊ የተቃውሞ ውጤት ነው። ፈጽሞ ረብሸኝነትን፣ ፀበኝነትን እና ነውጠኛትን መከታው የማያደርግ ለሰላም ዘብ የቆመ የሕዝብ ድምጽ ነው። ይህን ሰላማዊ ሰልፍ ጋንዲ ራሱ ቢመለከት የሚቀና ይመስለኛል። ምን ዓይነት አእምሮ ያለው ሰው ነው ከጀርባ ኾኖ ዲዛይን ያደረገው ማለቱ አይቀርም።…

ገዛኸኝ ይልማ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚም በበኩሉ፣ ኤርትራውያን በቅርቡ የኤርትራን መንግሥት በመቃወም ያደረጉትን ሰላማዊ ሰልፍ በማስታወስ፣ ኢትዮጵያውያን ሰልፍ እንዲፈቀድላቸው ኤርትራዊ መኾን አለባቸው ወይበ በማለት ማስታወሻ አስፍሯል፡-

ኢሕአዴግ የኤርትራዊያን እንጂ የኢትዮጵያዊያን አባት አይደለም እንዴ ብዬ መጠየቅ እውነት ቢሆንም… የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ይከበር።…

ሰላማዊ ሰልፎች በመንግሥት ጥሪ የሚደረጉትን ያክል በዜጎች ፈቃድም እንዲሆን ማስተዋል ደሳለው የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚ ባጭሩ ጠይቋል፡-

ግን እሰከመቼ ለግንቦት 20 የኢሕአዴግን ድል ለማድመቅ ወይም መሪያችን ሲሞት ብቻ ያለውድ በግድ እንድንሰባሰብ እየተደረግን በሌላ ቀን ደግሞ ምንም ሰላማዊ ብንሆን መሰብሰ እንደወንጀል ይቆጠርብናል?

የመስብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ይከበር!!!

ኪራም ዮናስ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚም ዘመቻውን ከሚደግፍባቸው አራት ምክንያቶች ውስጥ የሚከተለውን በሦስተኝነት አስቀምጧል፡-

መሰለፍ ቅሬታን አሊያም ድጋፍን መግለጫ እንጂ ሁሌም መንግስትን ከስልጣን ማውረጃ መሳሪያ ተደርጎ መታሰቡ ዜጎች ቅሬታቸውን የሚገልፁበትን መንገድ አጥፍቶ የታፈነ ብሶታቸው አላስፈላጊ ምስቅልቅል እንዳያመጣ ስለምፈልግ ነው::

Development in Silence, Democracy’s unbecoming! (ልማት በፀጥታ፣ አግባብ ያልሆነ ዴሞክራሲ) በሚል ርዕስ በተለይ ለዞን ዘጠኝ በጻፈው ጽሑፍ ቴዎድሮስ ያለው የተባለ የበይነመረብ አራማጅ የመንግሥታት አፋኝነት ውጤቱ ዜጎችን ለውስጥ ለውስጥ አጀንዳ እንደሚያጋልጣቸውና ይህ ደግሞ ለሁሉም ወገን ኪሳራ መሆኑን በመግለጽ ጽሑፉን ደምድሟል፡-

Yes governments impatient with people’s power and dissent has pushed the people and drove them underground and some to the guerilla but the end of it all was a disaster where everyone claimed to be the sole owner of the truth and disregarded the wisdom in the people to best know their interest.

አዎ፣ የመንግሥታት የሕዝብን ኃይል መረዳት አለመቻል ተቃዋሚዎችን ለውስጥ ለውስጥ (ድብቅ) እንቅስቃሴ ገፍቷቸዋል፤ አንዳንዶቹንም ለሽምቅ ውጊያ ዳርጓቸዋል፡፡ ነገር ግን የዚህም ውጤት ኪሳራ ነበር፡፡ ሁሉም የእውነታው ባለቤት ነኝ የሚልበት እና ሕዝቡ የገዛ ጥቅሙን እንደሚያውቅ ከግምት ውስጥ ያላስገባ ነበር፡፡

የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብቶች በሚል በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በተለይ ለዞን ዘጠኝ በተጻፈ ሌላ ጽሑፍም ላይ መብት ሰጥቶ ተገባራዊነቱን መከልከል ‹‹እንዳያማህ ጥራው፣ እንዳይበላ ግፋው›› የሚሉት ዘዴ ነው ብለዋል፡-

በሥራ ላይ አለ የሚባለው በ1987 ዓ.ም. የወጣው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 30ና 31 የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት፣ የመደራጀት መብት ይደነግጋሉ፤ ነገር ግን ሁለቱም አንቀጾች ግን እያሉ መፍረሻውን ወይም ማርከሻውን አብረው ይገልጻሉ፤ እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላ ግፋው ነው፡ይህ ዘዴ በአጼ ኃይለ ሥላሴም ሆነ በደርግ ሕገ መንግሥቶች ውስጥየሚታይ ነበር፡፡

የመሰብሰብና ሰላማዊ ሰልፍ የመውጣት መብቶች የሕዝቡን ስሜትና ፈቃድ ለማወቅ ለሚፈልግ መንግሥት የእነዚህ መብቶች በተግባር መዋል በጣምፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም መንግሥትንና ሕዝብን ያቀራርባሉ፤ የእነዚህ መብቶች መታፈን የሚያሳየው::

[…]

በኢትዮጵያሕዝቡ ቤቱ ሲፈርስ፣ መሬቱን ሲነጠቅ፣ ከኑሮው እየተፈናቀለ ሲባረር፣ ፍትሕ ሲጠፋ፣ ክብሩንና ኩራተን ተገፎ በያገሩ ሲሰደድናውርደት ሲደርስበት ተሰብስቦ ለመወያየት መብት የለውም፤ በተናጠል እንባውን እያፈሰሰ ወደ አምላኩ ማመልከት ልማድ ሆኗል፤ በአገዛዙ ወንበር ላይ የተቀመጡት እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ሕዝብ ግፍ የማያይ፣ ጩኸቱንም የማይሰማ ይመስላቸዋል፤ አግዚአብሔርግን ሁሉንም ይመዘግባል፤ ለንስሐ የሰጣቸው ጊዜ ሲያበቃ ፍርዱን ለእያንዳንዱ ይሰጣል፤ ያን ጊዜ ኃይልም፣ ሀብትም፣ ሥልጣንም የሕዝብ ይሆናል፡፡

ዘላለም ክብረት የተባለ የ ቡድኑ (ዞን ዘጠኝ) አባል ጸሐፊ ደግሞ ‹‹መብት በአደባባይ›› የሚል ርዕስ በሰጠው ጽሑፉ፣ ሰላማዊ ሰልፍ (ከወሲብ ያልተናነሰ) ተፈጥሯዊ ፍላጎት መሆኑን ገልጾ መንግሥትም ያንን የሰው ፍላጎት የሟሟላት ግዴታ እንዳለበት ተናግሯል፡-

…መንግሥትስ ሚናው ምን ሊሆን ይገባል? የሚለው ጥያቄም ወሳኝ ነው፡፡ በመጀመሪያ መንግሥት የብዙኃኑን ሕግ ለማስጠበቅ፤ የህዳጣኑን መብት ደግሞ ለማክበር ነው የተቀመጠው ካልን፤ ከብዙኃኑም ሆነ ከህዳጣኑም ወገን ሰላማዊ በሆነ መንገድ  ሰልፍ እወጣለሁ የሚልን አካል ባለመከልከል ግዴታውን መወጣት ይኖርበታል፡፡ የዘመናዊ ሕገ መንግሥቶች መሠረት የሆነው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት በመጀመሪያው ማሻሻያው ይሄን ግዴታ በፌደራሉ መንግሥት ላይ ይጥላል፡፡ ሰዎች ምንም ዓይነት ስብሰባ ለማድረግ በሰላማዊ መልኩ መሰብሰባቸውን እና ጉዳታቸውን ለመግለጽ የሚያደርጉትን ማንኛውንም ዓይነት ሰላማዊ የአቤቱታ መግለጫ መንገድ የሚከለክል ሕግ መንግሥት ማውጣት አይችልም ብሎ ያፀናዋል፡፡…

[…]

በተጨማሪ፤ በሰላማዊ መንገድ የመሰለፍ እና የመሰብሰብ መብትን ከማስከበር አንፃር ከመንግሥት የሚጠበቅ አዎንታዊ ግዴታም (Positive obligation) አለ፤ የዜጎችን ደኅንነት እና ፀጥታ ማስከበር፡፡ ይህ ግዴታ በዋነኛነት የሚመነጨው ከመንግሥት-ዜጎች ማኅበራዊ ውል (Social Contract) ነው፡፡ መንግሥት የዜጎች ተወካይ ሁኖ ሲቀመጥ፤ ዋነኛው ሥራው የዜጎችን ፀጥታ እና ደኅንነት ማስከበር ነው፡፡ እናም ዜጎች በሰላማዊ መንገድ የመሰለፍ እና የመሰብሰብ መብታቸውን ሲጠቀሙ መንግሥት ደኅንነታቸውን ማስከበር ይኖርበታል፡፡ ይህ ግዴታ በኹለት መንገድ ጠቃሚ ሆኖ ይገኛል፤ የመጀመሪያው በሰላማዊ መንገድ አደባባይ የወጡትን ዜጎች (ምን አልባትም ህዳጣኑን) ደኅንንት ከመጠበቅ አኳያ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሰልፉላይ ያልተሳተፉ ዜጎችን (ምን አልባትም ብዙኃኑን) ከምንም ዓይነት የደኅንነት ስጋት ነጻ ማድረግ ነው፡፡ ስለዚህም በሰላማዊ መንገድ የመሰለፍ እና የመሰብሰብ መብትን ከማስጠበቅ አኳያ የመንግሥት ግዴታዎች በኹለት ትይዩ ይቀመጣሉ፤ መብቱን የሚፃረር ሕግ ባለማውጣት እና የመብቱ ተጠቃሚዎችን ከለላ በመስጠት፡፡….

የዘመቻው አዘጋጆች ከዘመቻው ተሳታፊዎችና ተመልካቾች ለሚቀርቡላቸው ተደጋጋሚ ጥያቄዎች የሰጡትን መልስ እዚህ ማግኘት ይቻላል፡፡

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.