- Global Voices በአማርኛ - https://am.globalvoices.org -

የአድዋ ድል በዓል ጦማሪዎችን አነቃቅቶ አለፈ

Categories: ኢትዮጵያ, ኤርትራ, ታሪክ, የንግግር ነፃነት, የዜጎች መገናኛ ብዙሐን, ዲጂታል አራማጅነት, ጦርነት እና ግጭት, ፖለቲካ, ውይይት ለተሻለች ዓለም

ጥቁር አፍሪቃውያን አውሮጵያውያንን ለመጀመሪያ ጊዜ በጦርነት ያሸነፉበት የአድዋ ድል 117ኛ ዓመት በዓል የካቲት 23/2005 በብሔራዊ ደረጃ ተከብሮ ውሏል፡፡ የበዓሉ አከባበር በብሔራዊ ደረጃ እዚህ ግባ በሚባል ዓይነት ሥነ ስርዓት ባይከበርም በርካታ ጦማሪዎች፣ አስተያየቶቻቸውን በመጻፍና በማኅበራዊ አውታር ገጾቻቸው ላይ በማስፈር የበዓሉን ለዛ ጠብቀው ለማለፍ ሞክረዋል፡፡

መቅደላ መኩሪያ የተባለ ጦማሪ The Victory of Adwa (የአድዋ ድል) [1] ባሰኘው መጣጥፉ የበዓሉ አከባበር ከዓመት ዓመት እየደበዘዘ መምጣቱ እንዳስቆጨው በጥያቄዎች ገልጧል፡-

‹‹… የአድዋ ድል በዓል ልናከብረው እና በደስታ ልናሳልፈው የሚገባ የገዛ በዓላችን አይደለምን? ሁላችንስ ብንሆን የነጻነታችን ባለዕዳዎች፣ የዛች ልዩ የማንም ጥገኛ አለመሆናችንን ያረጋገጥንባት ቀን ተጠቃሚዎች እና ለዚህች ታላቅ አገር ልዕልና ሲሉ ሕይወታቸውን የሰዉ አርበኞች ዕዳ የለብንም? ሁኔታችን ግን ቀኑ ከሌላው መደበኛ ቀን ምንም እንደማይለይ ነው፡፡ ጥያቄው እንዲህ መሆን አለበት ወይ? የሚለው ነው፡፡ ባንዲራዎቻችንን ለብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን፣ ለግንቦት 20 እና ለአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ እናውለበልባለን፤ ለዚህ በዓልስ የአዲስ አበባ አውራ ጎዳናዎች በአረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ተውበው ማየት አልነበረብንም? አድዋ የአፍሪካውያን ደስታ አይደለምን? ነው ወይስ አፍሪካዊም ኢትዮጵያዊም ባልሆነ ከተማ ውስጥ ነው የምንኖረው?…››

ካሳሁን ዓለሙ አድዋ ለኢትዮጵያ ምኗ ነው? [2] ባለው ጽሑፉ ባለፈው ዓመት የአድዋ ድል አከባበር ላይ የአድዋ ድል ለኔ ምኔ ነው/አይደለም በሚል ተነስቶ የነበረ ክርክርን አስታውሶ ይጀምራል፡፡ ጸሐፊው የጥያቄዎቹን መሠረት አንድ ባንድ ምላሽ ለመስጠት ሲሞክር ከአድዋ ድል በኋላ የተከሰቱት አስተዳደራዊ ችግሮች የድሉን ትርጉም እንደማይቀለብሱት ያትታል፡-

‹‹…በሌላ በኩል ዐፄ ምኒልክም ይሁኑ ሌሎች መሪዎች ለፈጠሩት ‹ጭቆናም ይሁን ሌላ መጥፎ ተግባር› የድሉን ታላቅነትና አስፈላጊነት አይቀለብሰውም፤ ባይሆን መጠየቅ ያለባቸው አግባባዊ ያልሆነ ነገርን በእሱ ታከው ከሠሩ በእዚያ ተግባራቸው ነው፡፡ በዚህም ቢሆን ለምሳሌ ዐፄ ምኒልክ ‹የአድዋን ድል ውጤት ለሕዝቦች መጨቆኛ አድርገውታል› ሲባል በምን ዓይነት መልኩ? የሚል ጥያቄ ይነሣል፡፡ ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች በመስፋፋታቸው ነው? ከተስፋፉ በኋላ በአስተዳደር ሥርዓት ሕዝቦችን ስለበደሉ ነው? ነው በሌላ? በመጀመሪያው ‹ባደረጉት መስፋፋት› ከተባለ ‹መስፋፋታቸው አስፈላጊ ነበር ወይስ አይደለም?› የሚል ጥያቄ ይከተላል፤ በአስፈላጊነቱ ላይ ከተስማማን ችግሩ ያላው ከመስፋፋቱ በኋላ ባለው የአስተዳደር ሥርዓት ነው ማለት ነው፡፡ በዐፄው መስፋፋቱ አስፈላጊነትና አግባብነት ካልተስማማን ግን ‹ምን ዓይነት ኢትዮጵያን ፈልገን ነበር?› የተከፋፈለች? የተከፋፈለች ኢትዮጵያስ እኛ በፈለግነው መልኩ ትገኝልን ነበር? ለምሳሌ ኦሮሚያን እንውሰድ ዐፄ ምኒልክ በመስፋፋት አሁን ያለችዋን ኢትዮጵያን አንድ አድርገው ባያስጠብቁልን ኖሮ አሁን የሚገኘው ኦሮሚያ በአንድነት ይገኝልን ነበር? ሌላ የውጭ ወይም የውስጥ ኃይልስ እኛ በምንፈልገው መልኩ ኦሮሚያን ሊያስገኝልን እንደሚችል ዋስትና ይኖረናል? ከሌለ በመጠኑም ቢሆን ምኒልክን ማመስገን የኦሮሞዎች ፋንታ ይሆናል፤ ይህ ለሌሎችም ብሔረሰቦች ይሠራል፡፡ በሌላ በኩል ‹ዐፄ ምኒልክ በኃይልም ይሁን በሰላማዊ ማግባባት ተስፋፍተው የኢትዮጵያን አንድነት ከማስጠበቁ ሌላ አማራጭስ ይኖራቸው ነበር?› ካለ ምን? ከሌለ ትንሹን ችግር ለትልቁ ጥቅም ማጥፊያ በማድረግ ማጣጣል የለብንም፡፡…››

ድሜጥሮስ ብርቁ የተባለ ጦማሪም ቦርከና በተሰኘው ጦማሩ ላይ We need an Adwa Mentality [3] (የአድዋ አስተሳሰብ ያስፈልገናል) የሚል ጦማር አስነብቦ ነበር፡፡ በጦማሩ ላይ ድሜጥሮስ አድዋ የኩራታችን መነሻ ሳይሆን መድረሻ መሆኑን እና ራስ ወዳድ ያልሆኑ በማኅበራዊ እሴታችን የተናፁ አርበኞች ያመጡልን ገድል መሆኑን ገልጧል፡፡ በተጨማሪም ስለአድዋዊ አስተሳሰብ እንዲህ ይላል፡-

‹‹… አድዋን እውን ያደረገው አስተሳሰብ ክብራችንን እና ነጻነታችንን በእውነተኛ ትርጉሙ መልሰን እንድናገኘው የግድ ያስፈልገናል፡፡ ሕወሓቶች፣ አብረዋቸው የሚሠሩት ወይም ሌሎች ይህንን የአድዋ አስተሳሰብ ያመጣሉ የሚል ውዥንብር ውስጥ አልገባም ምክንያቱም ራስ ወዳድነት በራሱ መንገድ ውስጥ ሱስ ያስይዛልና፡፡ ተስፋ የማደርገው ንፁሐን ዜጎች አሁን አሁን እንደ‹ዘመነኝነት› እየተቆጠረ ወዳለው ራስወዳዶቹን ማስመሰል እንዳይጀምሩና ወደግልፅ እና ጊዜያዊ ውጤት የሚያመራውን የከዳተኝነት እና ጥቅመኝነት መንገድ መርጠው እንዳይገቡ ነው፡፡ ተስፋ የማደርገው ራስወዳዶቹን የምር የሚወስዳቸው ትውልድ እንዳይመጣ ነው፡፡…››

የአድዋ ጦርነት ትዊፋታዊ ስዕል

የአድዋ ጦርነት ትዊታዊ ስዕል

አገልግል የተባለ ጦማር Post Adwa Thoughts [4] (የድኅረ አድዋ ዐሳቦች) በሚል ርዕስ የዚህ ዘመን አርበኝነት ጦርነት እንደማያካትት ገልጾ በዚህ ዘመን የአድዋ ውርስ ምንድን ነው ብሎ ይጠይቃል፡፡ ቀጥሎም በተለይ ጸሐፊው/ዋ ሰመራ ዩንቨርሲቲን ከጎበኙ በኋላ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች አገር ለቆ ከመውጣት የተሻለ ውርስ የላቸውም የሚል ስሜት እንደተሰማው አትቷል፡-

‹‹…ብዙዎቹ አዲስ አበባ ያሉ ጓደኞቼ ሽግግር ላይ ናቸው፤ ወይ ውጭ አገር ለማጥናት የሆነ የትምህርት ዕድል እየጠበቁ ነው፣ ወይም አንዱ መያድ ውስጥ ሥራ ለማግኘት እየሞከሩ ነው አሊያም ውጪ አገር ያለ የትዳር አጋራቸው ሊወስዳቸው አሊያም ሀብታም ሊያገቡ ተዘጋጅተዋል፡፡ ገንዘብ ካለው የተወለዱ አሉ አሊያም ወደውጭ ሄደው የተሻለ ኑሮ የሚያስመራቸውን ሥራ የመያዝ ዕድል ያላቸው አሉ፡፡ ሁሉንም ውጣ ውረድ አሸንፈው በሥራም ሆነ በራሳቸው ቢዝነስ የተሳካላቸውም አሉ፡፡ ነገር ግን ሌሎችም አሉ፡፡ ምንም ተስፋ የሌለው ሥራ እየሠሩ የሚኖሩም አሉ፡፡  አገር ለቀው የሚወጡ ኢትዮጵያውያንን እተች ነበር፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ቆይታዬ አመለካከቴን ቀየረው፡፡ ምናልባትም ለመኖር መሰደድ የግድ ይሆናል፡፡ ችግሩ ብዙዎች በመንገድ ላይ አልቀዋል፡፡…››

በዓሉን ሌሎችም በተለያየ መንገድ ሲያስቡት ነበር፡፡ ዮሐንስ ሞላ በጦማሩ የእጅጋየሁ ሽባባሁ (ጂጂ) ‹አድዋ› የተሰኘ ዜማ እየተነተነ [5] ጽፏል፡፡ ኤፍሬም እሸቴም አደባባይ በተሰኘው ጦማሩ ላይ አድዋ ምኑ ነው? [6] የሚል ግጥም አስነብቧል፡፡ ውብሸት ታደለ የተባለ የፌስቡክ ተጠቃሚም በዕለቱ የዐድዋው ድል መሪ ዐፄ ምኒልክ የዘሩት ፍሬ አልበቀለላቸውም በሚል የሚከተለውን ግጥም [7] አስፍሯል፡-

…አድዋ…

ገበሬው ምኒልክ ዕለቱ ጊዮርጊስ መሆኑን ዘንግቶ፣

በበዓል ቀን እርሻው በአድዋ መሬት ላይ ሐበሾችን ዘርቶ፣

ከአፈር የወደቁ፣ አፈር የለበሱ፣ ጠይም ፍሬዎቹ፣

ከአጥንት ስጋቸው ላይ ትውልድ እንዲበቅል በፍቅር ሟቾቹ፣

በአድዋ መሬት ላይ በበዓል ተዘርተው ትውልድ በቀለ፣

በጥላቻ አብሾ ሕሊናው የዞረ ለክፋት የማለ… ትውልድ በቀለ፡፡

ገበሬው ምኒልክ በዕለተ ጊዮርጊስ በበዓል ቀን ዘርቶ፣

አዝመራው ከሸፈ የዘራው ገብስ ዘር እንክርዳድ አፍርቶ፣

ሰው የዘራባት፣ የገበሬው ተስፋ፣ ድንግሊቷ አድዋ፣

አገር በሚገድል በመርዛማ ፍሬ ሞላ ጎተራዋ፣

ጊዮርስን ሽሮ ዘሩን በመዝራቱ፣

ምስኪኑ ገበሬ፣ ዋታቹ ምኒልክ፣ ይኼ ሆነ ምርቱ፡፡