ኢትዮጵያ፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባል ለመሆን ትመጥናለች?

በህዳር 12 2012 እ.ኤ.አ. የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባላት ሆነው ከተመረጡ አራት የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ኢትዮጵያ አንዷ  ነች፡፡ ለመጪዎቹ ሶስት አመታት  የተመረጡ ሌሎች ሀገራት አርጀንቲና፣  ብራዚል፣  ኮትዲቯር፣  ኢስቶኒያ፣  ጋቦን ፣ ጀርመን፣  አየርላንድ ፣ ጃፓን፣  ካዛኪስታን፣  ኬንያ ሞንቴኔግሮ፣  ፓኪስታን፣ የኮሪያ ሪፐብሊክ፣ ሴራሊዮን፣  የተባበሩት አረብ ኢመሬት፣ አሜሪካና ቬንዙዌላ ናቸው፡፡

ነገር ግን የኢትዮጵያ ለሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መመረጥ ብዙዎቹን ኢትዮጵያውያንን አላስደሰተም፡፡ኢትዮጵያዊው  ምፀተኛ አቤ ቶክቻው ይህን ምርጫ አስመልክቶ ይህን ጻፈ፡፡

በሐምሌ 13 2012 እ.ኤ.አ ከሌሌች 23 አራማጆች ጋር ተከሶ 18 ዓመት ተፈርዶበት በእስር የሚገኘው ኢትዮጵያዊው ጦማሪ እና ጋዜጠኛ አስክንድር ነጋ የፎቶ ምንጭ፡- FreeEskinderNega.com

ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት ሰብአዊ መብት ኮሚሽን አባል ሀገር ሆና ተመረጠች። የትኛዋ ኢትዮጵያ!? የትኛው ሰብአዊ መብት!? የትኛው የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን!?  እኔ የምለው ኢትዮጵያዊው የዩልኝታ ባህላችን ያለው ህብረተሰቡ ዘንድ ብቻ መሆኑ በጣም አሳሳቢ ችግር አይመስላችሁም? እንዴ መንግስት እኮ ይሉኝታ ቢኖረው ኖሮ “ተመድ የሰባዊ መብት ኮሚሽን አባል አድርጌ መርጨሀለሁ!” ሲለው… “አረ በህግ አምላክ እኔ አልሆናችሁም ሀገር ተሳስታችሁ ነው! ወይ ደግሞ ባታውቁኝ ነው የመረጣችሁኝ…!” ማለት ነበረበት። ነገር ግን መንግስቴ “ምን ይሉኝ” ያልፈጠረበት ነውና አሜን ብ ሎ መቀበሉ ሲገርመን፤ ጭራሽ በአደባባይ “እንዲህ ነን እኛ ሰብአዊ መብት ጠባቂዎች” ተብሎ ተነገረን!

በደረሰበት ጫና ከሀገር የተሰደደው ጋዜጠኛ እና ጦማሪ ዘሪሁን ተስፋዬ  በፌስቡክ ገጹ ይህን ለማመን የሚከብድ ‘የኢትዮጵያ መመረጥ’ እንዲህ ሲል ገልጾታል፡፡

እስቲ ልነሳና ልበል አልቸም አልቸም
እሷ የኔን ነገር ትተዋለች መቼም” የሠፈራችን አዝማሪ።

አንዲህ ነገር ዓለሙን የተዉ ግለሰቦች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት ሲያጋጥሙ አዝማሪውን ተቀብሎ ማንጎራጎሩ ሳይቀል አይቀርም። ስለኢትዮጵያ መንግሥት ሰብዓዊ መብት ረገጣ አንዳንዴ እኛን ባለጉዳዮቹን በሚያስደንቅ ኹኔታ የዓለም ዓቀፉ ማኅበረሰብ ሲያቀነቅን “ወይ ጉድ ለካንስ እነዚህ ሰዎች የልብ አውቃ ኖረዋል” ብለን ተስፋ እናደርጋለን። አንድ ቀን የለውጡ አካል ሆነው የነጻነታችንን እንቀዳጃለን ብለንም ልባችን በሐሴት ትሞላለች። እናም የጋዜጠኝነት ሙያችንም የረዳንን ያህል “የማቃጠር ሥራ” እንሠራለን። አልፎ አልፎም “መንግሥት በቃሊቲ 50 ንጹሃን ዜጎችን አጎረ” ብለን ስናውጅ፤ “አይ መረጃችሁ አልተሟላም እኛ የደረሰን 120 ሰዎች ነው” ብለው ከነስም ዝርዝራቸው ሲያሳዩን እንደመምና አሁንም ተስፋ እናደርጋለን-ከኛው ከጭቁኖቹ ጋር ናቸው ብለን።
ሌሎች የማይጠቀሱ ጉዳዮች ተደራርበው ትላንት የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ይህቺን በሰብዓዊ መብት አያያዝ “የማትጠረጠር” አገር አባል አድርጎ ሲመርጥ ግን የሠፈሬን አዝማሪ ማስታወስ ግድ አለኝ። በእውነት እነዚህ የመብት ተሟጋቾች እና ተቋማት ተስፋ ሊያስቆርጡን እየሞከሩ ነው? ወይስ በየትኛውም መስፈርት አገርን ለማስተዳደር ብቃቱ የሌለው ቦዘኔ መንግሥት ምን አልባት አባል ሲሆን የጠባይ ለውጥ ያመጣ ይኾን ብለው? አሁን አሁን “እየተፎጋግርን” ያለን ያህል ተሰማኝ።
ክፋቱ አሁንም የእነሱን ድጋፍ የምንፈልግ መሆናችን፤ “የለማኝ ስልቻ ቢንከባለል ከለማኝ ደጅ” እንዲሉ።

 

 

 ሌላው ያገባኛል ያለው የበየነ መረብ ቀበኛ ዮሐንስ ሞላ ይህን ጻፈ፡፡

እማር በሰር ጫሪም፣ ጒቸ ገግት ቧሪም፡፡” የጉራግኛ ተረትና ምሳሌ (ወማካ) ነው፡፡ ወደ አማርኛ ሲመጣ “አህያ ላይ ስጋ ጭነው፣ ጅብን ሸኝ አሉት፡፡” ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ይህ ሲሆን ውጤቱ ግልፅ ነው፡፡ ጅቡ አህያዋ ላይ የተጫነውን ስጋ ሁሉ ይበላዋል፡፡ ምናልባት አህያዋንም ጠግቦ ካቆያት ነው እንጂ እርሷንም በጊዜ ይበላታል፡፡

ትናንት ማምሻውን በእንቅልፍ ልቤ አንብቤው…. ‘ህልም ነው!… ቅዠት ነው!’ እያልኩ ተኝቼ፣ ዛሬ ስነቃ እውን ሆኖ የደገመኝና እስካሁን ድረስ በአህምሮዬ ላይ ተተክሎ ቀኔን ያጠቆረብኝና፣ እያቃጨለብኝ ያለውን ኢትዮጵያ የተመድ የሰብዓዊ መብት ካውንስል አባል የመሆን ወሬ ጉዳይ ከዚህ ተረትና ምሳሌ የተሸለ ምን ይገልፀው ይሆን?!

 

ጃዋር ሞሓመድ ኢትዮጵያ የምክር ቤቱን ወንበር እንዴት የራሷ ማድረግ እንደቻለች ዝርዝር ትንታኔውን አስፍሯል፡፡ ዳንኤል ብርሃነ ግን የኢትዮጵያን የምክር ቤት አባልነት ከሚቃወሙት ጋር አይስማማም፡፡[EN]

I see no anomaly with Ethiopia being elected to the UN Human Rights Council.

Both Ethiopia and the Council have good Constitutions.

They both have capacity (political, financial, etc) limitations implementing it.

Perfect match.

የኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግስታት ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መመረጥ ምንም ጥመት አላየኹበትም፡፡ ሁለቱም፤ ኢትዮጵያም ምክር ቤቱም ጥሩ ሀገ መንግስት አላቸው፡፡ ሁለቱም ለትግበራ የአቅም (ፖለቲካዊ፣ የገንዘብ ወዘተ.  . .)  ውስንነት አለባቸው፡፡ ፍጹም ጥምረት!

ኢትዮጵያ  የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያካሄዳሉ ብለው ከሚከሷቸው የአፍሪካ ሀገሮች አንዷ  ስትሆን በተጨማሪም በርካታ ተቃዋሚዎች፣ አራማጆችና ጋዜጠኞች በወህኒ የሚሰቃዩባት ናት፡፡

2 አስተያየቶች

ንግግሩን ይቀላቀሉ

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.