ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያውያን የቡድናቸውን ማሸነፍ በጉጉት እየተጠባበቁ ነው

የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ቡድን ለየአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሱዳን አቻው ጋር እሁድ ጥቅምት 4 ቀን 2004 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታድየም ውስጥ ያካሄዳል፡፡ኢትዮጵያውያንም ቡድናቸው ከአመታት በኋላ የማጣሪያው ጫፍ ላይ መድረስ “ወደ ውድድሩ እንገባ ይሆን?” የሚል ጉጉት ፈጥሮባቸዋል፡፡በመጀመሪያው ጨዋታ የደረሰበት ሽንፈት እንኳ ተስፋ አላስቆረጣቸውም፡፡ የተለያዩ ባለሐብቶችም ከወዲሁ ለቡዱኑ አባላት ሽልማት እንደሚሰጡ እየተናገሩ ሲሆን  በስደት ያሉ ኢትዮጵያውያን ሳይቀር ይህን ጨዋታ አዲስ አበባ ስታዲየም ተገኝተው መከታተልን ተመኝተዋል፡፡

 በስደት የሚገኘው የአዲስ ነገሩ ጋዜጠኛ ዘሪሁን ተስፋዬ እንዲህ ሲል ምኞቱን ገልጿል

 እሁድን በአዲስ አበባ ብገኝ ተመኘሁ። በስታዲዬማችን ኳስ ካየሁ አስር ዓመታትን አስቆጠርኩ፤ ዛሬ ግን ተስፋ የተሞላው ፍርሃት ሲሰማኝ ብገኝ ብዬ ተመኘሁ። ልቤ ይመታል . . . ነገ አንዳንች ታሪክ ሳይፈጠር አይቀርም።

ይህ የቡደኑ ያልተቋጨ ጉዞ የተለያዩ ሚዲያዎችንም ትኩረት ስቧል፡፡ በሳምንት ሁለት ጊዜ የሚታተመው ሪፖርተር ጋዜጣ በመካነ ድሩ የቡድኑን ደጋፊዎች አነጋግሮ ብሔራዊ ቡድኑ ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ዕድሉ በእጁ ላይ ነው ብለው መናገራቸውን ዘግቧል፡፡

 ኢዮብ አለነ የባንክ ባለሙያ ሲሆን፣ በአዲስ አበባ ስታዲየም ላለፉት አሥር ዓመታት ቋሚ ተመልካች ነው፡፡ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ በተጨማሪ የአውሮፓን ውድድሮች በስፋት የሚከታተለው ኢዮብ፣ በእግር ኳስ ለማሸነፍ የሥነ ልቦና የበላይነት ወሳኝ ነው ይላል፡፡ ‹‹ተጫዋቾቻችን መደናገጥ ሳያሳዩ በዘጠና ደቂቃ ውስጥ በእልህና በወኔ ከተጫወቱ ድሉ የእኛ ነው፤›› ይላል፡፡ እሱ እንደሚለው የሕዝቡን ድጋፍ፣ የሜዳ ባለቤትነትን፣ በተለይ ደግሞ የአዲስ አበባን ከፍታ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ተረጋግጠው ከተጫወቱ ድሉ የብሔራዊ ቡድኑ ነው፡፡”

 

 የሀገሪቱን  የስፓርት ጋዜጠኝነት ሙያ አንድ እርከን ከፍ ያደረገው ፍስሐ ተገኝ በሩቅ ሀገር ሆኖ  የተወደደ ትንታኔውን በቶታል433 ሰጥቷል፡፡

 ምንም እንኳን የእግርኳስ ውጤት በአብዛኛው በጨዋታዎች እለት በሚፈጠሩ ክስተቶች ላይ ጥገኛ ቢሆንም ታሪክ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ያደላል። የሱዳን ብሄራዊ ቡድን ከሜዳው ውጪ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ባደረጋቸው ያለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች በአንዱም ያላሸነፈ ሲሆን በአጠቃላይ ሁለቱ ቡድኖች ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ባደረጓቸው ሶስት የማጣሪያ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ሶስቱንም ጨዋታዎች አሸንፋ ሰባት ጎሎችን ተጋጣሚዋ ሱዳን ላይ ስታስቆጥር፤ የተቆጠረባት አንድ ጎል ብቻ ነው።ለመሆኑ በአዳነ ግርማ፣ ሳልሀዲን ሰኢድ እና አዲስ ህንጻን በመሳሰሉት ተጨዋቾች የሚመራው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ለሶስት አስርት አመታት ያህል ሀገሪቷን ወክለው የተጫወቱት ኮከቦች ማግኘት ያልቻሉትን በአፍሪካ ዋንጫ የመካፈል እድል ያገኙ ይሆን? አብረን የምናየው ይሆናል።”

 ይህ በእንዲህ እንዳለ ቡድኑ ጫወታውን በድል ካጠናቀቀ የመንግስት ደጋፊዎች  ሀገሪቱን ሁለንተናዊ ዝቅጠት ውስጥ ከተው በሞት ከተወሰዱት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ ጋር ለማያያዝ ከንቱ ጥረት ማደረግ ይጀምራሉ የሚል ስጋት ኢትዮጵያውንን አሳስቧል፡፡

 የአከባቢ ጥበቃ ባለሙያው ኪሩቤል ተሾመ በፌስቡክ ገጹ እንዲህ ሲል ምሬቱን ከወዲሁ ገልጿል፡፡[EN]

An evil thought crossed my mind and I said God forbid! If team Ethiopia wins on sunday and dedicate the glory to late PM I my have a stroke and hence miss the awesome joy the day should be..seriously! God forbid!”

እኩይ ሐሳብ በህሊናዬ ዥው አለብኝ፤  ለእግዚአብሔርም ይህን አትፍቀድ አልኩት፡፡እሁድ የኢትዮጵያ ቡድን ካሸነፈና ድሉ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር ክብር  ከዋለ በዚህ ምክንያት  ልቤ ቀጥ ስለምትል ይህ ልዩ አስደሳች ቀን ሊያልፈኝ ነው. . . የምሬን ነው!  እባክህ እግዜር ይህን ከልክል!”

ይህን የመንግስት ሚዲያዎች እና ባለስልጣናት አዝማሚያ የተረዳው የአለም ድምጾቹ ዘላለለም ክብረት “እስኪ እናያለን” ብሎ መልዕክቱን በአሽሙር አስተላልፏል፡፡

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ዋንጫ ከተጀመረ ጀምሮ 3 መንግስታትን አይታለች (የፊውዳሉን፣ ወታደራዊው እና ልማታዊውን ፡) ) ከነዚህ ሶስት መንግስታት ውስጥ ለአፍሪካ ዋንጫ ያላለፈችው በልማታዊው መንግስት የስልጣን ዘመን ብቻ ሲሆን፣ ባለፉት 2 መንግስታት ግን ከማለፍም በላይ ዋንጫ እስከ ማንሳት ደርሳ ነበር፡፡ በልማታዊው መንግስት ዘመን ግን ምነው ይህ አልሆነም ብየ ብጠይቅ ያለፈውን ስርዓት ናፋቂ እባል ይሆን?

ባለፈው ጠሚ መለስ የሞቱ ወቅት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፕሬዘደንት አቶ ሳህሉ ገ/ወልድ ‹‹ጠሚ መለስ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ትልቅ አስተዋፅኦ ከማበርከታቸውም በላይ፤ ኳስ ህፃናት ሲጫወቱ ሲያዩ ልጅነታቸው እየመጣባቸው ኳስ ይነካኩ ነበር፣ እኛንም ከጎናችሁ ነኝ አይዟችሁ ይሉን ነበር›› ሲሉ ብሰማ ጊዜ ጓድ መንግስቱ ናቸው እንዴ የሞቱት ?እስክል ድረስ አስገረሙኝ፡፡

የሆነ ሆኖ በጠሚ መለስ የስልጣን ዘመን የአፍሪካ ዋንጫ ብርቃችን ነበር፡፡ እንግዲህ የኳስ አኬራችን መልዓከ ሞት ጠሚውን ሊወስድ ሲመጣ መልሶልን ከሆነ እሰየው፡፡”

3 አስተያየቶች

ንግግሩን ይቀላቀሉ

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.