ኡጋንዳ፤ ከአሥራዎቹ ዕድሜ ያልተሻገረች ሴት የአፍሪካ ትንሽዋ የፓርላማ አባል ሆነች

ፕሮስኮቪያ አሌንጎት ኦሮሚያት በ19 ዓመቷ የአፍሪካ በዕድሜ ትንሽዋ የፓርላማ አባል የሆነችው የኡሱክ ክልል ምርጫን በ11,059 ድምጽ ካሸነፈች በኋላ ነው፡፡ ብዙ የተነገረላት ይህች ወጣት በዚህ (የአውሮጳውያን) ዓመት መጀመሪያ ላይ በሞት የተለዩትን አባቷን በፓርላማ ትተካቸዋለች፡፡

አሌንጎት በፕሬዚደንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ የሚመራው የብሔራዊ ሬዚስታንስ ንቅናቄ አባል ናት፡፡ በምርጫው ተፎካካሪዎቿ የነበሩት እነ ቻርለስ ኦጆክ ኦሌኒ (በ5,329 ድምጽ)፣ ቻርለስ ኦኩሬ ከኤፍዲሲ (በ2,725 ድምጽ) እና ቺቺሊያ አኒያኮይት ከዩፒሲ (በ554 ድምጽ) ተሸናፊ ሆነዋል፡፡

Honourable Alengot Oromait. Photo used with permission of monitor.co.ug.

የተከበረችው አሌንጎት ኦሮሚያት፣ ፎቶው የተገኘው በmonitor.co.ug ፈቃደኝነት ነው፡፡

ብዙ ሰዎች ደስታቸውን ሊገልፁላት ወጥተዋል፤ ሌሎች ደግሞ በውሱን ልምዷና ዕድሜዋ ምክንያት በፓርላማ ጊዜዋ እንደማይሳካላት ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ አንዳንዶች ይህ በአፍሪካ የሚመጣው ለውጥ መጀመሪያ እንደሆነ እየተናገሩ ነው፤ እናም ይህ ከመጠንበላይ የጃጁ የአፍሪካ መሪዎችን አስወግዶ በወጣቶች ለመተኪያ እና ወደፊት ለመራመጂ ጊዜው ነው ይላሉ፡፡

የተከበረች አልንጎት መኖሪያ አካባቢ ከፍተኛ የውሃ፣ ኤሌክትሪክ ኃይል እና በአግባቡ የተጠረገ መንገድ ችግር አለበት፡፡ ለአሁን የኡሱክ ሕዝቦች በ19 ዓመቷ ወካያቸው የፓርላማ አባል ላይ ተስፋቸውን ጥለዋል፡፡ የመኖሪያ አካባቢዋን በአግባቡ እንደምትወክል ተስፋ አለ፡፡

የአሌንጎ ሰፈር በGoogle map፡-

ካርታውን አጉልተው ይመልከቱት

አንዳንድ የዜጎች መገናኛ ብዙሐን አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አስፍረዋል፡-

ሶላር ሲስትር እንደምታምንበት፣  የለውጡ ምሰሦ ወጣት ሴቶች ናቸው፡-

የወጣት ሴቶች የስልጣን ለውጥ! የ19 ዓመቷ ፕሮስኮቪያ አሌንጎት ኦሮማይት የኡጋንዳ ፓርላማ አባል ሆና ተመረጠች http://fb.me/28DoJ2IUr

ጆይ ዶረን ቢራ ደግሞ ወይዘሪት አሌንጎትን የፓርላማ ውስጥ መሰረታዊ ስርዓቶችን የሆነ ሰው እንዲያስተምራት ጠይቋል፡-

@JoyDoreenBiira፡- አሌንጎት ኦሮሚያት፣ አሁን የ19 ዓመት የኡጋንዳ ፓርላማ አባል ናት…. በጣም ጥሩ፡፡ ግን የሆነ ሰው ማወቅ ባለባት መሰረታዊ ጉዳይ ላይ “የቤት ውስጥ ትምህርት” ሊሰጣት ይችላል…

በኒው ቪዥን ድረአምባ ላይ አስተያየቱን ሲያሰፍር አጋምባዬ ፍራንክ መመረጧ ጥሩ መሆኑን ገልፆ ዴሞክራሲ እንዲህ መሆን አለበት ብሎ እንደሚያስብ ተናግሯል፡-

ዴሞክራሲ ደግነቱ ይኸው ነው፤ ሕዝቦች መረጧት

ላኮዶ ደግሞ አሁን ገንዘብ ስለሚኖራት ሃብታም እጮኛ የማግኘት እድሏን ተጠቅማ የአሁኑን ፍቅረኛውን እንዳትተወው ተማጽኗል፡-

የተከበርሽ፣ እባክሽን ቻፓቲ ይገዛልሽ የነበረውን የ19 ዓመት ፍቅረኛሽን እንዳትረሺው፤ የተወሰነ ያክል ለዚህ ረድቶሻል፡፡ ደሞ እንደ ሙሴ ያሉ የፓርላማው ጣሪያ እስኪረግፍ የሚያንኳርፉ ሰዎች እንዳያስደነግጡሽ አስታውሽ፡፡

ሞኒተር ድረአምባ ላይ ደግሞ፣ ንኩንቱ የሚጠይቀው  የፓርላማው ወንበር በማንኛውም ሰዓት ተወስዶ፣ ሥራ መፈለግ ልትጀምር ስለምትችል አዲሷ የፓርላማ አባል በትምህርቷ ላይ ትኩረት እንድታደርግ ነው፡-

ለተከበርሽው የፓርላማ አባል አንድ ብቻ ምክር አለኝ፡- አትጨነቂ፣ ተደሰቺ፡፡ ይህ በሕየወት ዘመንሽ ደምቀሽ የምትታዪበት ብቸኛው ጊዜ ሊሆን ይችላል! የሚቀጥለው ምርጫ ላይም ነይ… ማንያውቃል፡፡ የቀን ሥራሽንም አትዘንጊ… ማለቴ ትምህርትሽን፡፡ ማንም የቀድሞ የፓርላማ አባል ያለትምህርት ደረጃ በሚል CV ሥራ ሊሰጥሽ አይፈቅድም፡፡  ማንም የፓርላማ አባል መሆን ይችላል፣ ሁሉም ግን የተማረ አይደለም፡፡ እንኳን ደስ ያለሽ!!

ፕሮውማን ሰዎች ወይዘሪት አሌንጎትን እንደ ሕፃን እየተመለከቷት እንደሆነ ታስባለች፡፡ አዋቂ በመሆኗ ስለራስዋ ራስዋ እንድታስብ ለአስተያየት ሰጪዎቹ መክራለች፡-

ፐሮስኮቪያ ብዙ ምክር አያስፈልጋትም፡፡ እናንተ ሰዎች እንደሕፃን እያያችኋት ነው፡፡ የ19 ዓመት አዋቂ ናት፡፡ ትምህርት እቤት ውስጥ ነው የሚጀምረው፤ ለምንድን ነው ሁሉም ወንድ ደርሶ ወላጅዋ ሊሆን የሚሞክረው? ይህችን ታዳጊ ሴት ስለራሷ በአፅንኦት እንድታስብ ተዋት፡፡ ብዙ ወጥ አብሳይ የበዛ ይመስለኛል፡፡ ፕሮስኮቪያ በርግጥ የሚሼል ኦባማ ዓይነት ሞገስ አላት፡፡ ረዥም፣ አትሌቲክ፣ ቆንጆ እና በራስ የሚተማመን፡፡ የመጀመሪያዋ የአሜሪካ ጥቁር ቀዳማይ እመቤት ሚሼል እንዴት የመጀመሪያዋ ጥቁር ቀዳማይ እመቤት መሆን እንደምትችል ምክር አላስፈለጋትም፡፡ ፕሮስኮቪያ እንኳን ደስ ያለሽ!

ፕሮስኮቪያ አሌንጎት እ.ኤ.አ. መስከረም 20/2012 ቃለመሐላዋን ፈፅማለች፡፡ የመጀመሪያዋ በጣም ወጣት እና ሴት አፍሪካዊት የፓርላማ አባል ናት፡፡

1 አስተያየት

 • ኢተፋ ጉያሳ

  በመጀመሪያ ወ/ት አሌንጎትን እንኳን ደስ አለሽ ለማለት እፈልጋለሁ።
  እንደሚታወቀዉ ኢትዮጵያ ለሴቶች እኩልነት ከሚታገሉት አገሮች ቀዳሚ አገር ነች። ይህኑን ደግሞ በተግባር እያሳየች መሆኑን በትምህርት ቤቶች፣በዩኒቨርሲቲዎች፣በፓርላማ፣ በበተለያዩ መ/ቤቶች ያሉት የሴቶች ቁጥር መጨመር ማረጋገጫ ይሆናል። ሆኖም ግን ቁጥር ብቻ ሳይሆን ጥራት ላይም ማተኮር ያለብን ይመስለኛል።
  በአጠቃላይ ግን ከአሁን ቀደም ለሴቶች ስሰጥ የነበረዉ ግምት እጅግ በጣም ስህተት ስለነበረ መድረስ የነበረባቸዉ ቦታ ሳይደርሱ ቀርቷል፤ በተለይ ደግሞ የአፍርካ ሴቶች።የመጀመሪያ እድል መከልከል ነበር። ለነገሩ እድል የተነፈጉት ሴቶች ብቻ አይደሉም። ወንዶችም እድል እየተነፈጉ የሉበት ነዉ ያለዉ አፍርካ ዉስጥ። ሁሉም ሰዉ የሀገር ፍቅር እንዲኖረዉ በለበትነት እንዲሰማዉ ከተፈለገ ሁሉም በሃይማኖትይ፣ በቀለም፣ በብሄር፣ እንድሁም በጎሳ ሳይለይ እኩል እድል መሰጠት አለበት እላለሁ። አሁንም የእኛ ሴቶች ቢሆኑም የተሰጣቸዉን እድል ተጠቅመዉ ማንነታቸዉን ማስመስከር አለባቸዉ። ጥገኝነታቸዉን ነፃ ማዉጣት!
  አመሰግናሉ!

ንግግሩን ይቀላቀሉ

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

 • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
 • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.