ኢትዮጵያ፤ በእስር ላይ ያለውን ጦማሪ እስክንድር ነጋን ማስታወስ

ሐምሌ 6/2004 የኢትዮጵያ ፌዴራል ፍርድ ቤት ጦማሪው እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሌሎችንም 23 የተቃውሞ ተግባር የፈፀሙ ሰዎችን ለ18 ዓመታት እና ሌላ መጠን ያለው የእስር ፍርድ ከአሸባሪነትጋ በተያያዘ በይኖባቸዋል፡፡

እስክንድር ነጋ የተቃውሞ ሐሳቦቹን መተንፈሻ ለማግኘት የመስመር ላይ ጦማሪ የሆነ ጋዜጠኛ ሲሆን መጨረሻ ጊዜ ከታሰረ አንድ ዓመት ሞላው፡፡ መስከረም 4/2005 የታሰረበት አንደኛ ዓመት ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ማኅበረሰብ በፌስቡክ ላይ አስታውሶታል፡-

መስፍን ነጋሽ እንዲህ ጻፈ:-

እስክንድር ነጋ በልጁ ፊት ወደእስር ቤት ከተወሰደ አንድ ዓመት ሞላው፡፡ ቀኑን ጋዜጠኞች እና ሌሎችም የሕሊና እስረኞች እንዲፈቱ እየጠየቅን እናስበዋለን፡፡ ዛሬ በያላችሁበት ሻማ አብሩ፡፡ እስክንድር ነጋ እና ሌሎችም ነፃ እንዲወጡ እንፈልጋለን!

የታሰረው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ እና ጦማሪ እስክንድር ነጋ፡፡ ፎቶ FreeEskinderNega.com

ጃዋር ሞሐመድ በእስክንድር ነጋ ባለቤት ሰርካለም ፋሲል የኢትዮጵያ መንግስት እስክንድርን እና ሌሎችም የፖለቲከኛ እስረኞችን እንዲፈታ በቃለአብ ታደሰ የሰፈረ ማስታወሻ አጋርቷል፡-

ኋላ ላይ በሐሰት ተመስክሮበት 18 ዓመት የተፈረደበት እስክንድር ነጋ ወደ እስር ቤት ከተወረወረ ዛሬ ድፍን አንድ ዓመት ሞላው፡፡

ከዚህ በታች በእስክንድር ነጋ ባለቤት እና የሙያ አጋር ሰርካለም ፋሲል በሰፈረው ማስታወሻ መሰረት፣ ሲያዝ የ6 ዓመቱን ልጁን ከትምህርት ቤት እያመጣ ነበር፡፡ በጉልበት ከልጁ ነጥለው ወሰዱት፡፡ የሚያስገርመው ነገር ታዲያ፣ ይሄ ሲሆን እና ልጅ የአባቱን በካቴና መጠርነፍ እና መንገላታት በማየት እየጮኸ መሬት ላይ የሚንከባለለውን ልጅ አሳሪዎቹ በቪዲዮ ለመቅረፅ መሞከራቸው ነው፡፡ ማንም የደነገጠውን ልጅ ለማባበል አልሞከረም፡፡

ከዚያን ጊዜ ወዲህ፣ ይሄ ትንሽ ልጅ ሁሌ የሚያወራው ስለፖሊስ ነው፡፡ ፖሊሶቹ እንዴት አባቱን እንደወሰዱበት ይናገራል፡፡ በማንኛውም ሰዓት የሚመጡበት ይመስለዋል፡፡ በጣም እየፈራቸው ነው፡፡

ሰርካለም እንዲህ ስትል ትጠይቃለች፣ “አሁን አሸባሪው ማን እንደሆነ ንገሩኝ?”

ይህ አንድቀን እንደሚመጣ እያሰበ ከነበረው እስክንድር ይልቅ፣ ክስተቱ መምጣቱን የማያውቀው ልጅ ላይ ምን ዓይነት የስነልቡና ችግር ሊያስከትልበት እንደሚችል ስጋቷን ትናገራለች፡፡ ከመታሰሩ በፊት እስክንድር ሁሌም ከቤት ሲወጣ በዚያው ፖሊሶች ያስቀሩኛል በሚል ስጋት እየተሰናበታቸው ይወጣ እንደነበር አስታውሳለች፡፡

እስክንድር ነጋን እና ሌሎችም ከ30,000 በላይ በኢትዮጵያ እስርቤቶች የተዘነጉ የፖለቲካ እስረኞችን ፍቱ፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች “iCare” (እኔ ያገባኛል) የሚል እና ሁሉም አባላቱ የፕሮፋይል ምስላቸውን በአንድ ማስታወሻ የሚቀይሩበት፣ በኢትዮጵያ ባንዲራ ምስል የተቀለመ የፌስቡክ ቡድን፡-

አንዱ የቡድኑ አባል ነብዩ ኃይሉ እንዲህ አለ:-

እያንዳንዷን ቀን [በተለይም መስከረም 4] የመለስ ዜናዊን ጭራቅ፣ እርኩስ፣ ክፉ አምባገነንነት ያስታውሰኛል፡፡ ፈጣሪ ይመስገን መለስን ዳግም አላየውም፡፡ ነገር ግን እነዚህ ለምንም የማይበጁ ‹ኢሕአዴግ›ኦች እስክንድር ነጋ፣ አንዱዓለም አራጌን እ ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞች መፍታት አለባቸው፡፡ ይህ የምር ይመለከተኛል! ነፃነት ያስፈልገናል፡፡ በመሰረቱ ሁላችንም በትልቅ እስር ቤት ውስጥ እየኖርን ነው፡፡

ዞን ዘጠኝ የተባለ የዘጠኝ ጦማሪዎች የጋራ ጦማር ኩነቱን ሪፖርት ሲያደርግ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ያለውን ፍላጎት  ገልጧል፡-

ኢትዮጵያውያን የፌስቡክ ተጠቃሚዎች የረጅም ጊዜ ጦማሪውና የነፃነት ተሟጋቹ እስክንድር ነጋ ወደ እስር ቤት የገባበትን አንደኛ ዓመት የፕሮፋይል ፎቶዋቸውን (በዚህ ምስል) በመቀየር እያስታወሱት ነው፡፡ ዞን ዘጠኝ እንደ የሕዝብ ውይይት እና የነፃነት ደጋፊነቷ እስክንድር ነጋንና ሁሉንም የሕሊና እስረኞች መንግስት እንዲፈታ ትጠይቃለች፡፡

 

የኢትዮጵያ መንግስት ከመስከረም 2004 ጀምሮ የመስመር ላይ ተግባራት ማጥለሉን አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡  እንደ የጋዜጠኞች ጠባቂው ኮሚቴ (CPJ) ከሆነ፣ እ.ኤ.አ. ከ2011 ጀምሮ መንግስት 11 ነፃ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪዎችን በፀረ-ሽብር ሕግ ከሷል፡፡ ከነዚህ ተከሳሾች ውስጥ፣ ከሶማሊ አማጺ ቡድን ጋር ተባብራችኋል በሚል 11 ዓመት የተፈረደባቸው ሁለቱ ስዊድናዊ ጋዜጠኞች ይገኙበታል፡፡

እስክንድር ነጋ ሐሳብን በነፃ ለመግለፅ መብት በአደገኛ የመገናኛ ብዙሐን ድባብ ውስጥ ባደረገው ተጋድሎ የአሜሪካ ባርባራ ጎልድ ስሚዝ (ፔን)የመጻፍ ነፃነት ሽልማት  አሸናፊ ነው፡፡

 

ንግግሩን ይጀምሩት

አዘጋጅ፣ እባክዎ መግቢያ »

መመሪያዎች

  • ሁሉም አስተያየቶች በገምጋሚ ይታያሉ. አስተያየትዎን ከአንድ ጊዜ በላይ አይላኩ አለዚያ እንደ ስፓም ይታብዎታል.
  • እባክዎ ሌሎችን በአክብሮት ያናግሩ. ጥላቻ የሚያንጸባርቁ፣ ተሳዳቢ እና ግለሰብን የሚያጠቁ አስተያየቶች ተቀባይነት የላቸውም.